ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚያግዙ ድጋፎችን በተቀናጀ መልኩ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

አዳማ ፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የሚያግዙ ድጋፎችን በተቀናጀ መልኩ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው የኢንዱስትሪ ደህንነትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳለጥ በሚቻልበት ሂደት ላይ በአዳማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየመከረ ይገኛል ።

የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ ከ3ሺህ በላይ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ገብተዋል።

በተጨማሪም ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች በ''ኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ ድጋፍ ተደርጎላቸው ማምረት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከነበረበት 48 በመቶ ወደ 56 በመቶ ማደጉን ኃላፊው አስረድተዋል።

በበጀት ዓመቱ ከ300ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉንና በዚህም ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ምርት በአገር ውስጥ ማምረት ተችሏል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት በሰጠው ትኩረትና በተቀናጀ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የፋይናንስ፣ የመሰረተ ልማት በተለይ የሃይል አቅርቦት፣ ውሃ፣ መንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮች በመቃለላቸው ውጤቱ መመዝገቡን ተናግረዋል።

ክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት 30 ሺህ ባለሃብቶችን ለማስተናገድ ተዘጋጅቷል ያሉት አቶ አህመድ፣ ለዚህም 80ሺሀ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን ኃላፊው ገልጸዋል ።

በበጀት ዓመቱም ሊያጋጥሙ የሚችሉ የፋይናንስና የመሰረተ ልማት አቅርቦት በተለይ የብድር አገልግሎት፣ የሃይል አቅርቦትና ተያያዥ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመመለስ ይሰራል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በአገር ውስጥ በስፋት ለማምረት ከመታቀዱም ባለፈ፤ ወደ ሥራ የሚገቡ የኢንቨስትመንት ተቋማትም ይደገፋሉ ሲሉም ገልጸዋል።

የቢሮው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሆሾ ከድር በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት መድረኩ የተዘጋጀው የብድር አቅርቦቱን ለማሳለጥ ነው።

መድረኩ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ለኬሚካልና ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊ የብድር አቅርቦት ከወዲሁ በማመቻቸት በተፋጠነ መንገድ ወደ ሥራ ለማስገባትና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይ የኢንቨስትመንት ንቅናቄ ውስጥ ባለድርሻ አካላት ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የብድር፣ የግብዓት፣ የሃይልና የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር በጋራ ለመፍታት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በግንባታ ላይ የነበሩ፣ የብድርና የአቅርቦት እጥረት ገጥሟቸው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ችግሮቻቸውን በጋራ መፍታት እንደተቻለ አቶ ሆሾ ተናግረዋል።

በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሥራ አቁመው የነበሩ 114 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውንም ተናግረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም