በክልሉ የህዝብና የመንግስት ሃብት ላይ ዝርፊያ የፈፀሙ አካላትን በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ጌታቸው ረዳ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የህዝብና የመንግስት ሃብት ላይ ዝርፊያ የፈፀሙ አካላትን በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ጌታቸው ረዳ
መቀሌ ፤ነሐሴ 04/2016(ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል በህዝብና በመንግስት ሃብት ላይ ዝርፊያ የፈፀሙ አካላትን በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለተግባሩም ህዝቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጠየቁ።
የመቀሌ ከተማ አስተዳደር በሁለት ቢሊዮን ብር የሚሰራው "አሸንዳ ስኩዌር የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት"ን አስመልክቶ ከከተማው ነዋሪዎች የውይይት መድረክ አካሄዷል።
መድረኩን የታደሙት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ከነዋሪዎች በልማትና በፀጥታ እንዲሁም በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ጌታቸው በወቅቱ እንደገለፁት፤ በህገ-ወጥ እንቅስቃሴ የሚሳተፍ የመንግስት ሃላፊም ሆነ ነጋዴ ተጠያቂ የሚደረግበትን ሁኔታ ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ግብረ-ሃይል ተቋቁሟል።
በዚህም የህዝብና የመንግስት ሃብት ዘርፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ አካላት በህግ እንዲጠየቁ የተጀመረው እንቅስቃሴ ፍሬያማ እንዲሆን ህዝቡ ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ጋር በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ በሰው መነገድ፣ በማዕድን ዘረፋና በሌሎች የህዝብና የመንግስት ሃብት ላይ ዘረፋ የፈፀሙ ማናቸውም አካላትን የህግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ህዝቡ ተደራጅቶ ሲያደርግ የነበረውን አካባቢውን የማልማትና ፀጥታውን የመጠበቅ ሥራ አሁንም አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በህገ-ወጥ ተግባር ተሰማርቶ የተገኘ ማንኛውም ሰው ያለ አግባብ የዘረፈውን ንብረት እንዲመልስና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ እንደሚሰራና ህዝቡም ለተግባሩ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ነው ያሳሰቡት።
ህዝብ ያልተሳተፈበት የልማትና የፀጥታ ስራ ስኬታማ ሊሆን እንደማይችል የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፤ ሁሉም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን እንዲሰለፍም ጠይቀዋል።