ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ በህገወጥ ተግባር የተሰማሩ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ  በህገወጥ ተግባር የተሰማሩ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያስቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ፣ የክረምት ተግባራትና ሌሎችም ሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

2016 ዓ.ም በርካታ ስኬታማ ተግባራት እንደተከናወኑበት ያነሱት ዶክተር ለገሰ፥ በቱሪዝም፣ በበጋ መስኖ የግብርና ስራ፣ በኢትዮጵያ ታምርት በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል።

በኮሪደር ልማት የተጀመሩ ስራዎችም ሀገርን የሚያኮሩና ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል።

ዓመቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮቶችን በአይበገሬነት በመቋቋም ቀጣይነት ያለው እድገትን ያስመዘገበበት እንደሆነም አመላክተዋል።

በቅርቡ የተጀመረው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ  ማሻሻያ ትግበራም የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያጸና ነው ብለዋል።

የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መፍጠር፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ማሻሻል፣ የዘርፎችን ውጤታማነትና ተወዳዳሪነት ማሳደግና የመንግስትን የማስፈጸም አቅምን ማጎልበት ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

ማሻሻያው በአምራች ኢንዱስትሪ የተሰማሩና በግብርና የሚተዳደሩ ዜጎች የጥረታቸውን ዋጋ የሚያገኙበት ከመሆኑም በላይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው ከፍተኛ ድርሻ እንዲያበረክት ያስችላል ነው ያሉት።

ማሻሻያው ሁለን አቀፍ ዕድገትን ለማረጋገጥ፣ የልማት ፕሮጀክት ውጤታማነት ለማሳደግ፣ የመንግስት ገቢን ለማሻሻል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ማሻሻያው በታቀደለትና በተቀመጠለት አቅጣጫ መሰረት እየተተገበረ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ሆኖም ተገቢ ያልሆኑ አዝማሚያዎች እየታዩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ የማሻሻያውን አስፈላጊነት በመረዳትና በሀገራዊ ስሜት የተለመደውን የንግድ እንቅስቃሴ ያለምንም ማስተጓጎል እያካሄደ ነው ብለዋል።

ሆኖም ህገወጥነትንና የራስን ስግብግብ ፍላጎት በሌሎች ላይ በመጫን መበልፀግን ዓላማ ያደረጉ የንግዱ ማህብረሰብ አባላት ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ እንደሁም ምርትን ለመደበቅ መሞከራቸውን ገልጸዋል።

ይህ ድርጊት ምንም ዓይነት መሰረታዊ ምክንያት የሌለውና ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው ብለዋል።

በመሆኑም መንግስት የጀመረውን ቁጥጥር በማጠናከር የህግ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በቀጣይነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለም በአፅንኦት ጠቅሰዋል።

መንግስት የወሰደው የማሻሻያ እርምጃ የንግዱ ማህበረሰብ ሲጠይቀው ለነበረው ጥያቄ ምላሽ የሰጠ በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ ከህገወጥ ተግባር ሊቆጠብ ይገባል ብለዋል።

የምርት እንቅስቃሴን የሚገድቡ ጉዳዮችን በመከታተል የመፍታት ስራ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

አያይዘውም መንግስት በዓመቱ ህግና ስርዓትን ለማረጋገጥና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ ሰፋፊ ስራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።

ነፍጥ ያነገቡ ሃይሎች ወደ ውይይት እንዲመጡ ሁሉንም የሰላም በሮች ክፍት አድርጎ ጥሪ ማድረጉንና ድርድሮችንም ማድረጉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸው፥ በዚህም ከምርት ተስተጓጉለው የነበሩ አካባቢዎች ወደመደበኛ ህይወት መመለሳቸውን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም