የመሬት መንሸራተትን በዘላቂነት ለመከላከል ተቋማት በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የመሬት መንሸራተትን በዘላቂነት ለመከላከል ተቋማት በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፦ የመሬት መንሸራተትን በዘላቂነት ለመከላከል ተቋማት መረጃን መሰረት በማድረግ በቅንጅትና በትብብር መሥራት እንደሚገባቸው ተመላከተ።
በተዳፋታማ አካባቢ የሚጥል ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብና የበረዶ መቅለጥ፣ የመሬት መሸርሸርና መንቀጥቀጥ፣ እሳተ-ገሞራና የከርሰ-ምድር ውኃ መጠን ለውጥ እንዲሁም በሌሎች ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ጥምረት የመሬት መንሸራተት መንስኤዎች ናቸው።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1998 እስከ 2017 ባሉት ተከታታይ ዓመታት የመሬት መንሸራተት ከ18 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈት እንዲሁም 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ዜጎችን ደግሞ ለተለያዩ ጉዳት ዳርጓል።
49 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ክፍል ለከፍተኛ፣ መለስተኛና አነስተኛ የመሬት መንሸራተት ተጋላጭ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።
በባለፈው ሐምሌ 2016 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈና ከሞት የተረፉትን በማፈናቀል አሳዛኝ ክስተት መድረሱ ይታወሳል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ-ፊዚክስ፣ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኤልያስ ሌዊ (ዶ/ር)፤ የመሬት መንሸራተት በአየር ንብረት መዛባትና በአካባቢ ጥበቃ ጉድለት በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግር የሚከሰት አደጋ ነው ይላሉ።
የመልክዓ-ምድር አቀማመጥ፣ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ፣ የአለት መፈረካከስ፣ የማዕድን ቁፋሮ፤ ልማዳዊ አስተራረስ እንዲሁም በጥናት ላይ የተመሠረተ ልማት አለመኖር የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የመሬት መንሸራተት አደጋ መንስኤዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህ መነሻነትም በኢትዮጵያ ለመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት በዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችልን አደጋ ለመከላከል ጥናትና ምርምር መሠረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረተ የአጭር፣ መካከለኛና የረዥም ጊዜ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲን በመተግበር ለዘላቂ የሥነ-ምኅዳር ጥበቃ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
ተዳፋታማ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችም የላይኛውን የመሬት ገጽታ ደግፎ የሚይዘውን የመሬት ገጽታ በመንከባከብ በመሬት መንሸራተት የሚደርስን የአደጋ ተጋላጭነት መቀነስ እንደሚኖርባቸው መክረዋል።
በጊዜያዊነትም በተዳፋታማ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ከባድ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት በመሬት መንሸራተት አደጋ እንዳይጠቁ ለማድረግ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ-ፊዚክስ ስፔስ ሳይንስ አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ ጌትነት ሜዋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የመሬት መንሸራተት አደጋን ለመከላከል ተዳፋታማ የመሬት ገጽታዎችን በደን በመሸፈን ከመኖሪያነትና ከእርሻ ሥራ ነፃ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ዜጎች በተዳፋታማ አካባቢ ከመኖር መራቅ እንደሚገባቸውና ከባድ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት በመሬት መንሸራተት አደጋ እንዳይደርስባቸው የአካባቢውን ሁኔታ በመረዳት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው መክረዋል።
የመሬት መንሸራተትን በዘላቂነት ለመከላከል ተቋማት መረጃን መሰረት በማድረግ በቅንጅትና በትብብር መሥራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው በነሐሴና በመስከረም ወራት የሚኖረውን የዝናብ መጠን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ወራት በሚኖረው ከመደበኛ በላይ ዝናብ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት ሊከሰት ይችላል ብለዋል።
በመሆኑም አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፤ በመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለአብነትም በደቡብ ኢትዮጵያ በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት የበርካታ ዜጎችን ሕይወት መቅጠፉንና ከአደጋው የተረፉትም መፈናቀላቸውን አንስተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ከሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት ጎን ለጎን የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች በተደራጀና በባለሙያ ጥናት ቦታ በመለየት የማሸሽ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የክልልና የዞን አመራሮች የሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ ወገናዊ አለኝታቸውን እያሳዩ መሆኑን ተናግረዋል።