ቀጥታ፡

በአዳማ ''የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ'' ስልጠና ከ110 ሺህ በላይ ሰልጣኞች ይሳተፋሉ

አዳማ፤ ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፦ በአዳማ ከተማ ''የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ'' ስልጠና ላይ ከ110 ሺህ በላይ ታዳጊዎች እንደሚሳተፉ የከተማው ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽህፈት አስታወቀ።

የአዳማ ከተማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የስማርት አዳማ ኢንሼቲቭ አስተባባሪ ኢንጂነር ሙክታር ጄይላን ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው የኮደርስ ስልጠናውን ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል።

ስልጠናው ትውልዱን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተዋወቅ የተሻለ እውቀት ያለው የሰው ኃይል ለመፍጠር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም በከተማው በሶስት ዙሮች በሚሰጠው ስልጠና ከ110 ሺህ በላይ ታዳጊዎች በስልጠናው እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።

ስልጠናውን ለማሳካትም ጽህፈት ቤቱ በፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቤተ ሙከራዎችን ለስልጠናው የማመቻችት እንዲሁም ኮምፒዩተሮችን የማሟላት ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።


 

የአዳማ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በሪሶ ዶሪ በበኩላቸው ጽህፈት ቤቱ ታዳጊ ወጣቶች የስልጠናው ተሳታፊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የዲጂታል ልህቀትን ለማረጋገጥ የተዘጋጀውን ስልጠና መጀመሩን ጠቅሰው፣ ከ100 በላይ የሚሆኑ የከተማው ርዕሳነ መምህራንና የጽህፈት ቤቱ  አመራር  አባላት ስልጠናውን እንደሚያስተባብሩም ገልጸዋል።

በዕቅዱም መሰረትም ከሰባተኛ ክፍል በላይ የሚማሩ የከተማው ታዳጊ ወጣቶች የስልጠናው አካል መሆናቸውንም አስታውቀዋል።        

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም