ኮሚሽኑ በሐረሪ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ማካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በሐረሪ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን ማካሄድ ጀመረ
ሀረር፤ ነሀሴ 4/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሐረሪ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወከሉ ተመራጮች እና ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ ውይይት ማካሄድ ጀምሯል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ በክልሉ ከሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ የህብረተሰብ ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዶክተር ተገኝወርቅ ጌቱ፣ ኮሚሽኑ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደት መጀመሩን ገልጸው፤ በሐረሪ ክልልም ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ስድስት ቀናት የማሰባሰቡን ተግባር እንደሚያከናውን ተናግረዋል።
ተሳታፊዎችም መከባበርና መደማመጥን መሰረት ባደረገ መልኩ ተነጋግረው አጀንዳዎቻቸውን እንዲያቀርቡም ኮምሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ግጭቶችና አለመግባባቶች በውይይትና በምክክር የመፍታት ልምድን እናሳድጋለንም ብለዋል።
ከዛሬ ጀምሮ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የመንግስት አካላት፣ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እና ሌሎች ተወያይተው የአጀንዳ ሃሳባቸውን እንደሚያዘጋጁ እና እንደሚያቀርቡ ተመላክቷል።