ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ይደረጋሉ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ይደረጋሉ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 4/2016(ኢዜአ)፦በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሶስት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ይካሄዳሉ።
ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተጠባቂው የወንዶች ማራቶን ፍጻሜ ይከናወናል።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ አትሌት ታምራት ቶላና አትሌት ደሬሳ ገለታ።
አራተኛውን የኦሊምፒክ ተሳትፎ የሚያደርገው ቀነኒሳ በኦሊምፒክ ተሳትፎው 3 የወርቅና 1 የብር ሜዳሊያ በማግኘት በኢትዮጵያ የውድድሩ ተሳትፎ ታሪክ በርካታ ሜዳሊያዎችን ያመጣ አትሌት ነው።
እ.አ.አ በ2019 በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ41 ሴኮንድ ያሸነፈበት ጊዜ የርቀቱ የዓለም ሶስተኛ ፈጣንና የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው።
ቀነኒሳ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በተካሄደው የለንደን ማራቶን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ15 ሴኮንድ ሁለተኛ በወጣ ጊዜ እድሜው ከ40 ዓመት በላይ የሆነ አትሌት በማራቶን ያስመዘገበው የምንጊዜውም ፈጣን ሰዓት በሚል ተመዝግቦለታል።
ሌላኛው ተወዳዳሪ ታምራት ቶላ በኦሊምፒክ ሲሳተፍ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። እ.አ.አ በ2016 በሪዮ ዴጄኔሮ በተካሄደው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል።
እ.አ.አ በ2023 በአምስተርዳም ማራቶን 2 ሰዓት ከ3 ደቂቃ ከ39 ሴኮንድ የግል ምርጥ ሰዓቱን አስመዝግቧል።
ታምራት ለውድድሩ በተጠባባቂነት ተይዞ የነበረ ቢሆንም አትሌት ሲሳይ ለማ ከውድድሩ ውጪ በመሆኑ ሲሳይን ተክቶ ይወዳደራል።
የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ ተሳትፎ የሚያደርገው አትሌት ደሬሳ ገለታ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም በስፔን በተካሄደው የሲቪያ ማራቶን 2 ሰዓት ከ3 ደቂቃ ከ27 ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።
በአትሌቲክስ ስፖርት ለረጅም ዓመታት በድል ያሸበረቀ ታሪክና የስኬት ጉዞ ያላቸው ቀነኒሳ በቀለና ኬንያዊው አትሌት ኤሉድ ኪፕቼጌ የሚያደርጉት ፉክክር በተመልካቾች በከፍተኛ ጉጉት ይጠበቃል።
የ39 ዓመቱ ኪፕቼጌ እ.አ.አ በ2022 በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ09 ሴኮንድ የግል ምርጥ ሰዓቱንና የማራቶን ወንዶች ሶስተኛው የዓለማችን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።
በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። በ31ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በተመሳሳይ በማራቶን አንደኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ለ21 ዓመታት የዘለቀው የቀነኒሳና ኪፕቾጌ ፉክክር በዛሬው ውድድር ሊቋጭ ይችላል ሲሉ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ግምታቸውን እያስቀመጡ ነው።
ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ላይ የወንዶች የ5000 ሜትር ፍጻሜ ይካሄዳል። በውድድሩ አትሌት ሐጎስ ገብረሕይወት፣ አትሌት ቢኒያም መሐሪና አትሌት አዲሱ ይሁኔ ይወዳደራሉ።
አትሌት ሐጎስ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በኖርዌይ ኦስሎ በተከናወነው ዳይመንድ ሊግ 12 ደቂቃ ከ36 ደቂቃ ከ73 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል። አትሌቱ የገባበት ጊዜ በርቀቱ የዓመቱ የዓለም ፈጣን ሰዓት ነው።
ሐጎስ በኦሊምፒክ የተሳተፈው እ.አ.አ በ2012 በለንደን በተካሄደው 30ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነበር። እ.አ.አ በ2016 በሪዮ ዴጄኔሮ በተደረገው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ5000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል።
በኦሊምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎውን የሚያደርገው አትሌት ቢኒያም መሐሪ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ በተካሄደ ውድድር 12 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ከ10 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።
ሌላኛው ተወዳዳሪ አዲሱ ይሁኔ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በኖርዌይ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 12 ደቂቃ ከ49 ሴኮንድ ከ65 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው።
በተያያዘም ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ላይ የ1500 ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል። አትሌት ጉዳፍ ፀጋይና አትሌት ድርቤ ወልተጂ ይሳተፋሉ።
ጉዳፍ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በቻይና ዢያሜን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 3 ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ ከ30 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ የወጣችበት ጊዜ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷ ሆኖ ተመዝግቧል። የገባችበት ሰዓት በርቀቱ የዓመቱ ፈጣን ሰዓት ነው።
ጉዳፍ ትናንት በተካሄደው የ10000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ስድስተኛ እንዲሁም በ5000 ሜትር ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።
ድርቤ ወልተጂ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ኢውጅን በተካሄደ ውድድር 3 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ ከ75 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዘግባለች።
በፍጻሜው የኢትዮጵያ አትሌቶች ከኬንያውያኑ አትሌቶች ፌዝ ኪፕዬጎንና ሱዛን ሎካዮ ኢጆሬ ጋር የሚያደርጉት ፋክክር የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ እስካሁን 2 የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት 67ኛ ደረጃን ይዛለች።