ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አትሌቶች በ10000 ሜትር ድል አልቀናቸውም

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016(ኢዜአ)፦በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10000 ሜትር ፍጻሜ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ድል ሊቀናቸው አልቻለም።

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ 30 ደቂቃ ከ45 ሴኮንድ ከ21 ማይክሮ ሴኮንድ ስድስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ጉዳፍ በ5000 ሜትር ፍጻሜ ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። አትሌቷ ነገ በ1500 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ላይ ትወዳደራለች።

የመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋን ያደረገችው አትሌት ፎትዬን ተስፋይ 30 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ ከ93 ማይክሮ ሴኮንድ ሰባተኛ ወጥታለች።

ሌላኛዋ የኢትዮጵያ አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ 30 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ከ57 ሴኮንድ 10ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ፅጌ በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ርቀት ሮጣ ውድድሯን ሳታጠናቅቅ ቀርታ ነበር።

ኬንያዊቷ አትሌት ቢትሪስ ቺቤት 30 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድ ከ25 ሴኮንድ ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቃለች። ቺቤት የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ናት።

ቺቤት በዘንድሮው ኦሊምፒክ በ5000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወቃል።

የ24 ዓመቷ አትሌት ከኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በኋላ በኦሊምፒክ በሁለቱም ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ሁለተኛ ሴት አትሌት ሆናለች።

ጣልያናዊቷ አትሌት ናዲያ ባቶክሌቲ 30 ደቂቃ ከ43 ሴኮንድ ከ35 ማይክሮ ሴኮንድ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሁለተኛ ወጥታለች። በርቀቱ የአገሯን የርቀቱን ክብረ ወሰን ሰብራለች።

በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው አትሌት ሲፋን ሀሰን 30 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ ከ12 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች። ሲፋን በ5000 ሜትር በተመሳሳይ የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወቃል።

አትሌቷ በርቀቱ የራሷን የዓመቱን ፈጣን ሰዓትም አስመዝግባለች።

በፍጻሜው ውድድር 25 አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን ኤርትራዊቷ ራሔል ዳንኤልና ኔዘርላንዳዊቷ አትሌት አሌሲያ ዛርቦ ውድድሩን ሳያጠናቅቁ ቀርተዋል።

ኢትዮጵያ በ2 የብር ሜዳልያዎች 67ኛ ደረጃን ይዛለች።

አሜሪካ፣ቻይና፣አውስትራሊያ፣ጃፓንና ታላቋ ብሪታንያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም