ቀጥታ፡

ጎንደርና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች ለራስ-ገዝነት አስተዳደር የሚያግዛቸውን ዝግጅት እያደረጉ ነው

 አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016 (ኢዜአ)፦ ጎንደርና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች ለራስ-ገዝነት አስተዳደር የሚያግዛቸውን የሰነድ ዝግጅትና የፋይናንስ ምንጭ የማስፋት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ገለጹ።   

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዩኒቨርሲቲዎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ያለመ "የራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋሚያ" አዋጅ ቁጥር 1294/2015 በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም ማጽደቁ ይታወሳል።

በዚህም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያው ራስ-ገዝ ተቋም በመሆን በ2017 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን በራሱ መስፈርት አወዳድሮ እንደሚቀበል አሳውቋል። 

የትምህርት ሚኒስቴር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ራስ ገዝ ይሆናሉ ብሎ ከለያቸው ስምንት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ጎንደርና ሐረማያ ዩኒርሲቲዎች ይገኙበታል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ራስ ገዝ አስተዳደር ለመመሥረት የአገር ውስጥና የውጭ ተመክሮዎችን በመቀመር የተለያዩ ሰነዶች እየተዘጋጁ ነው። 

የራስ ገዝነት ጥያቄ ለማቅረብ የሚያስፈልግ ሰነድ ተዘጋጅቶ በዩኒቨርሲቲው ሴኔት መጽደቁን ገልጸው፤ ተቋማዊ ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ሁነቶች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

የአካዳሚክ ነፃነትን ያሟላ ጥናትና ምርምር ማድረግ የሚያስችል የፋይናንስ ምንጭ ለማግኘት የራስ ገዝነት አስተዳደር በሚሰጠው መብት መሰረት ኃብት ማፍራት የሚያስችል ኢንተርፕራይዝ እንደሚቋቋምም ገልጸዋል። 


 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀማል የሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው በትምህርት መርኃ ግብሮች፣ በተማሪዎች አገልግሎት፣ በላብራቶሪ እንዲሁም በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል። 

በአገር አቀፍና በጎረቤት አገራት ደረጃ ተፈላጊነት ያላቸው የትምህርት መርኃ ግብሮችን በመገምገም የፋይናንስ ምንጮችን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 


 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ በበኩላቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከ90 በመቶ በላይ በጀታቸው በመንግሥት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸው፤ ተቋማቱ ለራስ ገዝነት የሚያበቃቸውን የፋይናንስ ምንጭ ማጠናከርና ሌሎች ዝግጅቶች ማድረግ እንዳለባቸው አስረድተዋል። 

ራስ-ገዝነት የአካዳሚክና የፋይናንስ ነጻነት በመስጠት የመንግሥት ዩኒቨርስትዎች በፈጠራ፣ ምርምር፣ ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ ለማሳካት ያግዛል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም