ቀጥታ፡

የዓባይ የምግብ ዘይት  ፋብሪካ ምርቱን ለህብረተሰቡ  በተመጣጣኝ ዋጋ  በማቅረብ አርአያ መሆኑ ተገለጸ

ባህር ዳር፤  ነሐሴ 3 ቀን 2016 (ኢዜአ)፡-  በባህርዳር ከተማ  የሚገኘው የዓባይ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ  ገበያውን በማረጋጋቱ ተግባር ላይ የድርሻውን በመወጣት አርአያ መሆኑን  የከተማው አስተዳደር  ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለጹ። 

ፋብሪካው በቀን 100 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት በማምረት ላይ መሆኑ ተመልክቷል።


 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ ጎሹ እንዳላማው የፋብሪካውን እንቅስቃሴ ከተመለከቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በከተማው ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ምግብና ምግብ ነክ ፋብሪካዎች ተስተውለዋል።

ሆኖም በባህር ዳር ከተማ የሚገኘው የዓባይ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ በሃላፊነት እየሰራ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

ፋብሪካው በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ ያለው ምርትም የገበያ ዋጋን በማረጋጋት ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ነው ብለዋል።

ፋብሪካው እያከናወነው ያለው የምግብ ዘይት አቅርቦትም ከወቅታዊ ሁኔታው ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን የዋጋ ጭማሪ በማረጋጋት የከተማውን የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሰክን ያግዛል ሲሉም ገልጸዋል።

ማሻሻያውን ተከትሎ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ ህብረተሰቡም በማገዝ ሚናውን እንዲወጣም አሳስበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ለህብረተሰቡ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርሱ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ በተረጋጋ አግባብ ግብይቱን ማካሄድ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዓባይ ምግብ ዘይት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ አማረ መንገሻ በበኩላቸው፤ ፋብሪካው በቀን 100 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት በማምረት ላይ እንደሚገኘ ገልጸዋል።


 

ምርቱንም ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የማከፋፈል ስራ እያከናወነ መሆኑን አመልክተው፤ ባለ አምስት ሊትር ዘይት በ900 ብር ለተጠቃሚው ቀጥታ እንዲደርሰው ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ፋብሪካውን አኩሪ አተር፣ ሱፍ፣ ኑግና ተልባ የመሳሰሉ የአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች በግብአትነት የሚጠቀም መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይ የምርት አቅርቦቱን ከአማራ ክልል ባለፈ በመላ ኢትዮጵያና ወደ ውጭ ለመላክ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከ205 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ስራ እንደገቡ ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም