ቀጥታ፡

አዲሱን የኤርፖርት ከተማ ፕሮጀክት ግንባታ ለማስጀመር  ዛሬ የተደረሰው የውል ስምምነት ትልቅ እርምጃ ነው- አቶ መስፍን ጣሰው 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱን የኤርፖርት ከተማ  ፕሮጀክት ግንባታ ለማስጀመር ዛሬ የተፈራረመው የውል ስምምነት  ትልቅ እርምጃ ነው  ሲሉ  የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አዲሱን "የኤርፖርት ከተማ" ፕሮጀክት ግንባታ ዝርዝር ዲዛይን ከሚሰራ "ዳር " ከተሰኘ ዓለም አቀፍ  ኩባንያ ጋር ዛሬ የውል ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና የዳር ኩባንያ የኢትዮጵያ፣ የኡጋንዳና የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ  ዳይሬክተር ታሪቅ አልካኒ  ፈርመዋል።

አየር መንገዱ እያስመዘገበ ያለውን ፈጣን ዕድገት ለማስተናገድ  በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ  "አቡ ሴራ" በተሰኘ ስፍራ "የኤርፖርት ከተማ" ለማስገንባት የሚያስችለውን የዝግጅት ምዕራፎች ሲያከናውን ቆይቷል።


 

አቶ መስፍን እንደገለጹት፣ ይህ የኤርፖርት ከተማ ፕሮጀክት  በአፍሪካ የመጀመሪያውና ግዙፉ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል ብለዋል።

ነገር ግን የተያዘው በጀት እንደ አሰፈላጊነቱ እየታየ ሊሻሻል እንደሚችል ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፎች የሚገነባ ሲሆን  የመጀመሪያው የፕሮጀክት ግንባታም በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ የሚያስችል መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል ።

ሁለተኛው የፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ  ደግሞ ኤርፖርቱ በዓመት አጠቃላይ ከ100 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን  የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

የኤርፖርት ከተማው 35 ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን 4 መንደርደርያ ይኖረዋልም ብለዋል ።

በዚህም ኤርፖርቱ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ከ270 በላይ አውሮፕላኖችን የማቆም አቅም ያለው ነው ብለዋል።

አየር መንገዱ ይህን ግዙፍ የኤርፖርት ከተማ ለመገንባት ዝርዝር የዲዛይን ስራውን ዓለም አቀፍ ልምድ ያካበተው ዳር ኩባንያ እንዲሰራ መወሰኑንም ገልጸዋል።

በዚህም፣ አዲሱን የኤርፖርት ከተማ ፕሮጀክት ግንባታ ለመጀመር  ዛሬ የተደረሰው የውል ስምምነት ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የዳር ኩባንያ የኢትዮጵያ፣ የኡጋንዳና የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዳይሬክተር ታሪቅ አልካኒ፤  የኤርፖርት ከተማ ፕሮጀክት ግንባታ ዲዛይኑን ለመሥራት እድል በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

 ኩባንያው የዲዛይን ስራውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ አጠናቆ እንደሚያስረክብ  አመላክተዋል።

ዳር ዓለም አቀፍ ኩባንያ ከዲዛይን ስራ ውጭ በሱፐር ቪዥን ስራም ይሳተፋል ተብሏል።

የኤርፖርት ከተማ ፕሮጀክቱ፤ በውስጡ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል፣ የካርጎ ማዕከል፣ ሆቴሎች፣ ከቀረጥ ነፃ የግብይት ሥፍራና የተለያዩ ዘመናዊ  መሰረተ ልማቶችን የሚያካትት ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እ.አ.አ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን 25 ቢሊየን ዶላር ለማድረስ እንዲሁም በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም