የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አዲስ ከተሾሙት የጄ ኤስ አይ ካንትሪ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ 

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016 (ኢዜአ)፦ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ  የጄ ኤስ አይ ፕሮጀክቶችን በአንድ አስተሳስሮ መምራት በሚቻልበት ዙሪያ  ከጂ ኤስ አይ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ተደርገው ከተሾሙት ዶክተር ቢኒያም ደስታ ጋር ተወያዩ።

የጄ ኤስ አይ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር መሰየሙ በጤና ሚኒስቴር እና ጄኤስአይ መሃል ያለውን የቆየ ትብብር እና ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ጄ ኤስ አይ ከጤና ጋር በተያያዘ እናቶች እና ህጻናት፣ የጤና ኤክስቴንሽን፣ የጤና መረጃ፣ የጤና ተቋማትን መልሶ ማቋቋም፣ አርብቶ አደር ማህበረሰቦችን መደገፍ እና ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶችን በኢትዮጵያ እየተገበረ እንደሚገኝ እና ወደፊትም አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ጤና ሚኒስቴር ከጄኤስአይ ጋር በትብብር መተግበር እንደሚፈልግ ዶክተር ደረጀ አስረድተዋል፡፡ 

ድርጅቱ እስካሁንም በጤናው ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ 

የጂኤስ አይ ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርጋሪት ክሮቲ በበኩላቸው ድርጅቱ በ23 ሃገራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ አዲስ የተሰየመው የጄ ኤስ አይ ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር የድርጅቱን የተለያዩ ፕሮጀክቶች በአንድ በማስተባበር በተቀናጀ መልኩ ለመተግበር ይረዳል ብለዋል፡፡ 

አዲስ የተሾሙት የድርጅቱ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ቢኒያም ደስታ ጄ ኤስ አይ ላለፉት 30 አመታት በኢትዮጵያ ከ60 በላይ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ድርጅቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡ 

የክልል ጄ ኤስ አይ ቢሮዎችም በአንድ ቢሮ ስር ተጠቃለው ስራቸውን እደሚያከናውኑ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ 

የዩ ኤስ ኤ አይ ዲ ኢትዮጵያ የጤና ጥራት አጠባበቅ የፓርቲ ምክትል ሀላፊ የኔአለም ታደሰ በበኩላቸው ድርጅታቸው ከጄኤስአይ ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የጤና ስርአት ለማሻሻል እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በጤና ስርአቱ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች የሚሰጠውን እንክብካቤ ለማሻሻል የደህንነት እና የጥራት ስትራቴጂ ነድፎ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ዩኤስኤአይዲ ይረዳል ማለታቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም