የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል ባለኃብቱ ገቢውን በማሳወቅ በወቅቱ ግብሩን የመክፈል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል - አቶ አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል ባለኃብቱ ገቢውን በማሳወቅ በወቅቱ ግብሩን የመክፈል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል - አቶ አህመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016(ኢዜአ)፦በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ማሻሻያ የኢኮኖሚውን እድገት ለማስቀጠል ባለኃብቱ በወቅቱ ግብሩን በመክፈል ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ተናገሩ።
የገቢዎች ሚኒስቴር ከመካከለኛ ግብር ከፋዮች ጋር በታክስ ሕግ ተገዥነትና በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴና የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የኢትዮጵያን እድገትን በዘላቂነት የማረጋገጥ ጥቅል ዓላማ አለው።
ከዚህ ውስጥ ገቢን በማሳደግ ወጪን በራስ አቅም የመሸፈን ዓላማ እንዳለው ገልጸው ለዚህም ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይም ግብር ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለውን ምጣኔን ለማሻሻል ግብር ከፋዮች ገቢን በአግባቡ በማሳወቅና የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል አገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ለዚህም መንግሥት ገቢን ዘመናዊ በሆነ የአሰራር ሥርዓት በተገቢው መንገድ ለመሰብሰብ በትኩረት እንደሚሰራና መንግሥት ግብር የሚሰውሩ ላይም ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ግብራቸውን በአግባቡና በወቅቱ ለሚከፍሉ ባለኃብቶች ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።
በዘንድሮ ዓመት በግብር የሚሰበሰበውን ገቢ ከፍ ለማድረግ ትኩረት መደረጉን ጠቅሰው ይህንን ለማሳለጥ የሚያስችል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት የጋራ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ተናግረዋል።
የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው ባለፉት አምስት ዓመታት የሚሰበሰበው ገቢ እስከ ሦስት እጥፍ የሚደርስ እድገት የታየበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በ2010 ዓ.ም የተሰበሰበው ገቢ 170 ቢሊየን ብር እንደነበር አስታውሰው በ2016 የተሰበሰበው ገቢ ከ500 ቢሊየን ብር በላይ ብር መድረሱን አብራርተዋል።
የገቢ አፈጻጸም እድገት እያሳየ ቢሆንም ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት አኳያ ያለው ድርሻ ዝቅ ያለ በመሆኑ ይህንን ለማሻሻል ከግብር ከፋዩ ጋር መምከር አስፈልጓል ነው ያሉት።
በቀጣይ በታክስ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉና በአዲስ መልክ የሚገቡ ግብር ከፋዮች የታክስ ሕጉን አክብረው ግብራቸውን እንዲከፍሉ፣ ዲጂታል የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን ለማጠናከርና የዳበረ የታክስ የሥራ ባህል ለማምጣት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በውይይት የተሳተፉ ግብር ከፋዮችም የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው አገሪቱ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ እንድታገኝ የታክስ መሰረት ማስፋት ላይ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።