ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ "የኤርፖርት ከተማ" ፕሮጀክት ግንባታ ዲዛይን ከሚሰራ ኩባንያ ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አዲሱን "የኤርፖርት ከተማ" ፕሮጀክት ግንባታ ዝርዝር ዲዛይን ከሚሰራ "ዳር " ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ጋር ዛሬ የውል ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው እና የዳር ኩባንያ ዳይሬክተር ታሪቅ አልካኒ ፈርመዋል።

አየር መንገዱ እያስመዘገበ ያለውን ፈጣን ዕድገት ለማስተናገድ በቢሾፍቱ ከተማ አቅራቢያ "አቡ ሴራ" በተሰኘ ስፍራ "የኤርፖርት ከተማ" ለማስገንባት የሚያስችለውን የዝግጅት ምዕራፎች ሲያከናውን ቆይቷል።

አቶ መስፍን እንደገለጹት፣ ይህ የኤርፖርት ከተማ ፕሮጀክት በአፍሪካ የመጀመሪያውና ግዙፉ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር በጀት የተያዘለት ሲሆን፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ ተገንብቶ ይጠናቀቃል ብለዋል።

ነገር ግን የተያዘው በጀት እንደ አሰፈላጊነቱ እየታየ ሊሻሻል እንደሚችል ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፎች የሚገነባ ሲሆን የመጀመሪያው የፕሮጀክት ግንባታም በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ የሚያስችል መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል ።

ሁለተኛው የፕሮጀክት ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ ኤርፓርቱ በዓመት አጠቃላይ ከ100 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።

የኤርፖርት ከተማው 35 ስኩየር ኪሎ ሜትር ላይ የሚያርፍ ሲሆን 4 መንደርደርያ ይኖረዋልም ብለዋል ።

የዳር ዓለም ኩባንያ ዳይሬክተር ታሪቅ አልካኒ በበኩላቸው፤ አዲሱን የኤርፖርት ከተማ ፕሮጀክት ግንባታ ዲዛይን ለመገንባት እድል በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

በዚህም ኩባንያው የዲዛይን ስራውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ አጠናቅቆ እንደሚያስረክብ ገልፀዋል።

ዳር ዓለም አቀፍ ኩባንያ ከዲዛይን ስራ ውጭ በሱፐር ቪዥን ስራም ይሳተፋል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በውስጡ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል፣ የካርጎ ማዕከል፣ ሆቴሎች፣ ከቀረጥ ነፃ የግብይት ሥፍራና የካርጎ ሎጂስቲክስ ማዕከል እንደሚኖረውም ይጠበቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም