ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአፋር ክልል ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል- ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

ሠመራ፤ነሐሴ  3/2016(ኢዜአ)፦ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአፋር ክልል ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ አስታወቁ።

በአፋር ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ  የዳያስፖራ ቀን በሠመራ ከተማ ተከበረ። 


 

በበዓሉ ከተለያዩ የዓለም አገሮች የመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉ ሲሆን የክልሉን ሁለንተናዊ የልማት አቅም የሚያመለክት ገለፃ በርዕሰ መስተዳድሩ ጽህፈት ቤት ተደርጓል።

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በዚሁ ወቅት የክልሉ ዳያስፖራ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ለማክበር በመሰባሰባቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በክልሉ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ተጠቅመው እንዲያለሙ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን አስፈላጊ ድጋፍም እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል።

በሚኖሩበት አገርም የኢትዮጵያን ብሎም የአፋርን ታሪክ፣ ባህልና ወግ በማስተዋወቅ ሚና እንዲጫወቱ ርዕሰ መስተዳድሩ ጠይቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዳያስፖራው በሚኖሩባቸው አገሮች ኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊነት በማንፀባረቅ እያበረከቱት ላለው አስተዋጽኦ  ምስጋና አቅርበዋል።

የአፋር ክልል ዳያስፖራ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ገአስ አህመድ በበኩላቸው ጽህፈት ቤቱ ዳያስፖራው በአገሩ ልማት ለማሳተፍ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በሠመራ ሎጊያ ከተማ የጋራ ቤቶች መሥሪያ 100 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አወል የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ለቤቶቹ መሥሪያ ያዘጋጀውን ካርታ ለአፋር ክልል ዳያስፖራ ጽህፈት ቤት ማስረከባቸውንም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ተወካይ አቶ  ወንድወሰን ግርማ  እንዳሉት ዳያስፖራው የክልሉን የተፈጥሮ ፀጋና የመልማት አቅም በመጠቀም ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።


 

አገልግሎቱ የክልሉ ዳያስፖራ ለአገሩ ልማትና ዕድገት በሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግም አንስተዋል።

 ዳያስፖራዎቹ በቀጣይ ቀናትም የተለያዩ የልማት ስራዎችን እንደሚጎበኙ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም