የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በግብርና ምርት ማሳደግያ ግብዓት አቅርቦት ውጤታማ ተግባራት አከናውነዋል -የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በግብርና ምርት ማሳደግያ ግብዓት አቅርቦት ውጤታማ ተግባራት አከናውነዋል -የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን
አዳማ፤ ነሐሴ 3/2016 (ኢዜአ)፡- የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በግብርና ምርት ማሳደግያ ግብዓት አቅርቦት ረገድ ውጤታማ ተግባራት ማከናወናቸውን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ገለጸ።
የፌዴራልና የክልሎች የህብረት ስራ ዘርፍ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዕቅድ ክንውንና የ2017 ዓ.ም የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሽሰማ ገብረስላሴ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በግብርና ምርት ማሳደግያ ግብዓት አቅርቦት ላይ በትኩረት ሰርተዋል።
በተለይ ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ ፀረ አረም ኬሚካሎችና ለሜካናይዜሽን እርሻ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን ለአባል አርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ረገድ በበጀት ዓመቱ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አካል የሆነው የህብረት ስራ ማሻሻያ ሪፎርም ለመተግበርም አበረታች ስራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።
ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የንቅናቄና ህብረት ስራ ማህበራት ያሉበትን ቁመናና ሁኔታዎች የመለየት የሱፐርቪዥን ስራ በ12 ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳድሮች መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም ማህበራቱ አሁን ባሉበት ሁኔታ ብቁ፣ ተወዳዳሪና የአባላቱን ጥቅም ማስጠበቅ ላይ ክፍተት እንዳለባቸው የተገመገመ ሲሆን፤ይህንን ለማስተካከል በተያዘው የበጀት ዓመትም ሪፎርሙ በወጥነት እንዲተገበር ይደረጋል ብለዋል።
በሌላ በኩል የህብረት ስራ ማህበራቱ ሸቀጦችን በስፋት በማቅረብ ገበያን በማረጋጋትም የተሻለ የተሰራበት በጀት ዓመት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባለፈ ከአሰራር፣ከፋይናንስ አቅማቸውና ከተወዳዳሪነት አንፃር አሁን ያሉበትን ሁኔታ ከመሰረቱ መለወጥና ወደ ዲጂታል እንዲገቡ በትኩረት ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመት ሪፎርሙን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎች እየተሰናዱ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ተወዳዳሪነታቸውና ሁሉን አቀፍ የፋይናንስ አቅማቸው እንዲጎለብት በማድረግ ሪፎርሙ ትልቅ አስታዋጽኦ አለው ብለዋል።
በኮሚሽኑ የህብረት ስራ ማስፋፊያ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ድሪባ በቀለ፣ ሪፎርሙን ወደ ትግበራ ከመግባት አኳያ የክልሎች አፈፃፀም የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ቤንሻንጉልና አማራ ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ አስተዳደር የተሻለ የሪፎርም የአተገባበር ሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
በተለይም በዘርፉ ያለው አሰራር ለማዘመን የሚያስችሉ ሶፍትዌሮች ማበልጸግ ረገድ እየወሰዱ ያሉት እርምጃ ሪፎርሙን ለማሳካት አመላካች የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በህብረት ስራ ማሻሻያ ሪፎርም በበጀት ዓመቱ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆኑ፤ኮሚሽኑን ሪፎርሙን ለመተግበር በርካታ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው ተመልክቷል።