ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ በኮሙኒኬሽንና ሚድያ ዘርፍ የኢትዮጵያን ሀሳቦች ለዓለም የማስተዋወቅ ስራ በስፋት ይሰራል - የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት  

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016(ኢዜአ)፦ በተያዘው በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ የኮሙኒኬሽን ስርአቱን ከማጠናከር ባለፈ የኢትዮጵያን ሀሳቦችና አቅሞች ለዓለም የማስተዋወቅ ስራ በስፋት እንደሚሰራ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ ገለጹ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት የተቋሙን አቅም ሚያጠናክሩ ሰፋፊ ስራዎች ማከናወኑንም ተናግረዋል።

አገልግሎቱ የስራዎቹን አድማስ በማስፋት በዐበይት ሀገራዊ ኹነቶች ላይ ሰፊ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል።

የኮሙኒኬሽን መዋቅሩንና የመገናኛ በዙሃንን አቅም የሚያሳድጉ ተግባራት መከናወናቸውንም ነው የተናገሩት።

ለአብነትም ለህዝብና ለንግድ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና አመራሮች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን አንስተዋል።

ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቋሚ የግንኙነት ስርአት በመዘርጋት መረጃዎችን በመደበኛነት ተደራሽ የማድረግ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

በተጨማሪም መገናኛ ብዙሀንን በማስተባበር በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከናወኑ የልማት ስራዎች የሚዲያ ምልከታ መደረጉን ጠቁመዋል።

በ2017 በጀት ዓመት ሀገራዊ አቅሞችን በማውጣት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

በተጨማሪም የኮሙዩኒኬሽን ስርአቱን የማጠናከርና አድማሱን የማስፋት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የተጽእኖ አድማስን በማሳደግ በአፍሪካ ብሎም በዓለም መድረኮች የኢትዮጵያን ሀሳብና አቅም  የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሀን ሁሉንም ተደራሽ ያደረጉ የይዘት ስራዎችን ታች ድረስ ወርደው እንዲያከናውኑ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም