ቀጥታ፡

በኦሊምፒክ ለኢትዮጵያ በ10000 ሜትር ሴቶች ሜዳሊያ ያስገኙ አትሌቶች ከደራርቱ ቱሉ እስከ ለተሰንበት ግደይ 

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ የተሳተፈችው እ.አ.አ በ1956 በሜልቦርን በተካሄደው 16ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነው።

በፓሪስ እየተካሄደ ያለውን ጨምሮ በ15 የኦሊምፒክ መድረኮች ተሳትፎ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክስና ውሃ ዋና ስፖርት 38 ስፖርተኞች አሳትፋለች። እስካሁን በአትሌቲክስ ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን አግኝታ 63ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ዛሬ ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ57 ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ የምትጠበቅበት የ10000 ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ይከናወናል። አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ፣ አትሌት ፎትዬን ተስፋይና አትሌት ጽጉ ገብረሰላማ ይወዳደራሉ።

ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች በኦሊምፒክ  በ10000 ሜትር ርቀት ስኬታማ የሚባል ታሪክ አላቸው።

በስፔን ባርሴሎና እ.አ.አ በ1992 በተካሄደው 25ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የወቅቱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በ10000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት አዲስ ታሪክ ሰራች።

ደራርቱ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ በርቀቱ ወርቅ ያመጣች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌትም ሆናለች። 

በተጨማሪም ለአፍሪካ በኦሊምፒክ የመጀመሪያውን ወርቅ ያመጣች ሴት አትሌት በመሆንም ታሪክ ሰርታለች።

በውድድሩ ደራርቱ ከደቡብ አፍሪካዋ አትሌት ኤላና ሜየር ጋር በመጨረሻው ዙር የነበራት ፉክክር ሁሌም የሚታወስ ነው።

በወቅቱ በውድድሩ ላይ ተሳትፋ የነበረችው አትሌት ትዕግስት ሞረዳ 18ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

እ.አ.አ በ1996 በአሜሪካ አትላንታ በተካሄደው 26ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10000 ሜትር ኮማንደር አትሌት ጌጤ ዋሚ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።

አትሌት ደራርቱ ቱሉ በውድድሩ 4ኛ የወጣች ሲሆን አትሌት ብርሃኔ አደሬ 18ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ሲድኒ ላይ እ.አ.አ በ2000 በተካሄደው 27ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10000 ሜትር ፍጻሜ ደራርቱ ቱሉ 30 ደቂቃ ከ17 ሴኮንድ ከ49 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የኦሊምፒክ ክብረ ወሰን በመስበር የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። 

ኮማንደር አትሌት ጌጤ ዋሚ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች። አትሌት ብርሃኔ አደሬ 12ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

አቴንስ ላይ እ.አ.አ በ2004 በተከናወነው 28ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርቀቱ አትሌት እጅጋየሁ ዲባባ የብር እንዲሁም አትሌት ደራርቱ ቱሉ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በፍጻሜው አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ 4ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

እ.አ.አ በ2008 በቤጂንግ በተካሄደው 29ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በ10000 ሜትር ሴቶች በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።

በውድድሩ የጥሩነሽ ታላቅ እህት አትሌት እጅጋየሁ ዲባባ 12ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። አትሌት መስታወት ቱፋ ውድድሯን ሳታጠናቅቅ ቀርታለች።

ጥሩነሽ በ5000 ሜትርም የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።

በለንደን እ.አ.አ በ2012 በተካሄደው 30ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ጥሩነሽ አሁን በርቀቱ በድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። በ10000 ሜትር በሁለት ተከታታይ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ሴት አትሌት መሆን ችላለች።

በውድድሩ ላይ አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔና አትሌት በላይነሽ ኦልጅራ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃን ይዘው ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

እ.አ.አ በ2016 በሪዮ ዴጄኔሮ በተካሄደው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አትሌት አልማዝ አያና በ10000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች። አትሌት ገለቴ ቡርቃ 8ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።

ከሶስት ዓመት በፊት በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አትሌት ለተሰንበት ግደይ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ የነሐስ ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝታለች።

በዛሬው የ10000 ሜትር ውድድር የምትሳተፈው አትሌት ፅጌ ገብረሰላማ በወቅቱ ውድድሩን አቋርጣ ወጥታለች።

ሌላኛዋ በፍጻሜው ላይ ተሳትፋ የነበረችው አትሌት ፀሐይ ገመቹ በሰራችው ጥፋት ከውድድር ውጪ መሆኗ የሚታወስ ነው።

በዛሬውስ የ10000 ሜትር ውድድር ኢትዮጵያ እንደከዚህቀደሞቹ የኦሊምፒክ ውድድሮች ድል ይቀናት ይሆን?

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም