ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው ያሉ በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ሂደት የሚያፋጥን ነው - ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው ያሉ በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የምታደርገውን ሂደት የሚያፋጥን ነው ሲሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ተናገሩ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ከአለም የንግድ ድርጅት አክሴሽን ዲቪዥን ዋና ዳይሬክተር ማይካ ኦሺካዋ ጋር የኢትዮጵያ የአለም የንግድ ድርጅት አባልነት የድርድር ሂደትን አስመልክቶ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ጥያቄ ካቀረበች ረዥም ጊዜ ያስቆጠረች መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት በአሁኑ ወቅት እየተገበራቸው ያሉ በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የድርድር ሂደቱን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደሚያግዝ ነው የጠቆሙት።

በቀጣይ ለሚካሄደው 5ኛው የስራ ቡድን ስብሰባ ላይ የሚቀርቡ ሰነዶች ወደ ተግባር የገቡ በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ያካተተ እንዲሆን ከድርጅቱ ባለሙያዎች ጋር ሰነድ በመከለስ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ አብራረተዋል፡፡

የአለም የንግድ ድርጅት አክሴሽን ዲቪዥን ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የኢትዮጵያ የአባልነት ጥያቄን ካጓተቱ ምክንያቶች መካከል በቅርቡ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ማሻሻያው የድርድር ሂደቱን እንደሚያፋጥን እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡

አያይዘውም የዓለም ንግድ ድርጅት ያለ ኢትዮጵያ ተሳትፎ ሙሉ አይሆንም ያሉት ዳይሬክተሯ ድርድሩን በአጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ድርጅቱ ቴክኒካል ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም