ቀጥታ፡

 የመማር ማስተማር ተግባሩን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው -ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ

ጋምቤላ፤ ነሐሴ 3/2016 (ኢዜአ)፦ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የጀመራቸውን የለውጥና የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የመማር ማስተማር ተግባሩን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ከፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ “መምህራን የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል” በሚል በአንዳንድ የግል ሚዲያ የተናፈሰው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑንም ዩኒቨርሲቲው ገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ድሪባ ኢቲቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲው የነበሩበትን የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማቃለል የመማር ማስተማር ስራውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሪፎርም ስራዎችን እያከናወነ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ካለፈው ህዳር 2016 ዓ.ም ጀምሮ እያከናወነ ባለው የሪፎርምና የለውጥ ተግባር የነበሩ ክፍተቶችን ለመሙላት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ በዘርፉም ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በዩኒቨርሲቲው ከቤተ ሙከራ፣ ምቹ የመማሪያና ማደሪያ ክፍሎች፣ ከቤተ መፃህፍት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታወቀዋል።


 

በፋይናንስ አገልግሎት ረገድም በሚታዩ ውስንነቶች ከመምህራንና ሌሎች ተገልጋዮች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ አዲስ የሰው ኃይል ቅጥር ባለመፈቀዱ ምክንያት በዚህ ዘርፍ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ያለመቻሉን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የፋይናንስ አገልግሎቱን ለማሻሻል የአቅምና የቅንነት ችግር ያለባቸውን ባለሙያዎች በሌሎች በመተካት የተገልጋዮችን ቅሬታ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እውነታው ይኸ ሆኖ እያለ አንዳንድ የግል ሚዲያዎች የዩንቨርሲቲው መምህራን ያቀረቡትን የአገልግሎት ይሻሻል ጥያቄን የስራ ማቆም አድማ አድርገዋል በሚል ያስተላለፉት የተሳሳተ  መረጃ አግባብነት የሌለውና ከእውነት የራቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ለ2017 የትምህርት ዘመን ሁሉንም ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ያሳተፈ የዝግጅት ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል። 

"በተለይም ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ ግንባታዎች ፈጥነው እንዲጠናቁ እየተደረገ ካለው ጥረት ጎን ለጎን እድሳቶችና ግቢ የማስዋብ ስራዎች ያለመታከት እየተከናወኑ ይገኛሉ" ብለዋል ዶክተር ድሪባ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም