ኢትዮጵያ ስደተኞች በተጠለሉባቸው ሥፍራዎች የጀመረችውን የችግኝ ተከላ በአጭር ጊዜ በማሳካት ተምሳሌትነቷን ታሳያለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ስደተኞች በተጠለሉባቸው ሥፍራዎች የጀመረችውን የችግኝ ተከላ በአጭር ጊዜ በማሳካት ተምሳሌትነቷን ታሳያለች - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃና ምቹ አካባቢ ለመፍጠር የጀመረችውን ታሪካዊ የችግኝ ተከላ በአጭር ጊዜ በማሳካት ተምሳሌትነቷን ዳግም እንደምታሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ኢትዮጵያውያን ለሰብዓዊነትና ለተገፉ ወገኖች ካላቸው ፅኑ ክብር የተነሳ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራቸው ለሚሰደዱ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላ የመስጠት የረጅም ዘመን ታሪክ አላቸው።
ይህን የኢትዮጵያንና የመንግሥቷን አኩሪ ተግባር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይመሰክሩላታል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ26 አገራት የተሰደዱ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስጠለል መሰረታዊ የማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ እያደረገች ትገኛለች።
በዚህ ሥራዋ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ተቀባይነትና ክብር የተጎናጸፈች ሲሆን ጎን ለጎንም ስደተኞች በተጠለሉባቸው አካባቢዎች የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ታህሳስ በጄኔቫ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የስደተኞች ኮንፈረንስ ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች 100 ሚሊዮን ችግኝ በአራት ዓመታት ለመትከል ቃል ገብታ ነበር።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎትና አጋር ተቋማት ይህንን ዓለም አቀፋዊ ቃል ገቢራዊ ለማድረግ ዛሬ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ይፋዊ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር አከናውነዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ የአየር ንብረት ለውጥ የተፈጥሮ ሚዛን በመዛባት በረሃማነት፣ ድርቅና ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን እያስከተለ ነው።
ኢትዮጵያ የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ለአካባቢ ጥበቃ ሥራ ትኩረት መስጠቷን አንስተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርም የተመናመነውን የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ማሳደጉን ገልጸዋል።
"የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ኃሳብ በተጀመረው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እስካሁን ከ5 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን ነገ የሚወስኑት የዜጎቿ የዛሬ ተግባርና የመሪዎቿ ቁርጠኝነት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በአረንጓዴ አሻራ የጀመርነው ሥራ ዓለም አቀፍ እውቅና ተችሮታል ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚደርሰውን የተፈጥሮ ሃብት ጉዳት ለመቀነስ 100 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ወደ ሥራ መግባታችን ታሪካዊ ተግባር ነው ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አክለውም ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምትመች አገር የመሆኗን ያህል ስደተኞች አካባቢያቸውን እንዲንከባከቡ የተጀመረው ሥራ የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም 100 ሚሊዮን ችግኞችን ከአራት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመትከል የኢትዮጵያን ተምሳሌታዊ ተግባር ዳግም ማሳየት እንደሚገባ አንስተዋል።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሐሰን፤ በዘንድሮው የክረምት ወቅት ስደተኞች በተጠለሉባቸው አካባቢዎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው 5 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ መጀመሩን ገልጸዋል።
ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ከስደተኞች ጋር በመሆን ችግኞችን በመንከባከብ ለፍሬ ለማብቃት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የጀመረችውን ኢኒሼቲቭ ውጤታማ እንዲሆን አጋር ድርጅቶችና ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሹዋ ታባህ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምቹ አገርን በዘላቂነት ለመገንባት የሚጠቅም አስደናቂ ኢኒሼቲቭ ነው ብለዋል።
ስደተኞች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የተጀመረው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም አገሪቱን የሚያስመሰግን ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ካናዳም ከኢትዮጵያ ጋር በአካባቢ ጥበቃና በስደተኞች ጉዳይ ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር ገልጸዋል።