ቀጥታ፡

የቴሌኮሙኒኬሽን ገበያው ለውድድር ክፍት መደረጉ የዘርፉን መሰረተ ልማትና ተጠቃሚዎች ቁጥር አሳድጎታል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት የቴሌኮሙኒኬሽን ገበያውን ለውድድር ክፍት በማድረጉ የዘርፉ መሰረተ ልማት፣ ተጠቃሚዎች እና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ገለጸ፡፡ 

የኮሙኒኬሽን አገልግሎት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ያለውን ገንቢ ሚና ታሳቢ በማድረግ ዘርፉ የሚመራበት የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን በኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 1148/2011 መቋቋሙ ይታወሳል።

በዚህም በኢትዮጵያ በውድድር ላይ የተመሰረተ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት አቅርቦት እንዲኖር እና ነፃ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው ተቆጣጣሪ ተቋም እንዲመሰረት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ እንዳሉት፤ ባለስልጣኑ የቴሌኮም ፈቃድ ይሰጣል፤ የኮሙኒኬሽን ዘርፉን የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ይቆጣጠራል።

በዚህም በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የቴሌኮም ፈቃድ እንዲሁም የኢ ኮሜርስ ስርዓቱን የሚያቀላጥፉ የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል።

ለአብነት በበጀት ዓመቱ ከ4 ሺህ በላይ የተለያየ አይነት ሞዴል ያላቸው የቴሌኮም መሳሪያዎች ከውጭ እንዲገቡ ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።

በቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል ፍትሐዊ የገበያ ውድድር መኖሩን ለማረጋገጥ የገበያ ጥናት መደረጉንም ጠቁመዋል።

መንግስት ለኮሙኒኬሽን አገልግሎት በሰጠው ትኩረት ከለውጡ በኋላ በተለያዩ ቁልፍ የብቃት መለኪያ መሳሪያዎች እምርታ አምጥቷል ብለዋል፡፡

በተለይም የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ገበያ ውድድር ክፍት መደረጉ የተጠቃሚዎችንና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደጉን ገልጸዋል።

በዚህም ኢትዮ ቴሌኮም በመላ ሀገሪቱ 1 ሺህ 500 ታወር መዘርጋቱንና ደንበኞቹም ከ37 ሚሊዮን ወደ 76 ሚሊዮን ማሻቀባቸውን ጠቁመዋል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በበኩሉ ከ10 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን መመዝገቡን ገልጸው፤ በኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮም መካከል ጤናማ የገበያ ውድድር መፈጠሩን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ በዘርፉ በዘረጋው የኮሙኒኬሽን አገልግሎት የቁጥጥር ሥርዓት ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡንም ተናግረዋል።

የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጥራት ለማረጋገጥ በ2016 በጀት ዓመት ሶስት የተለያዩ ኔትወርኮችን መቆጣጠር የሚያስችል መሳሪያ ሥራ ላይ መዋሉን ገልጸዋል።

ይህም የድምጽ፣ የኢንተርኔት፣ የጽሁፍና መሰል የቴሌኮም አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን መቆጣጠር የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም የኮሙኒኬሽን ዘርፉን ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ነድፈው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም