ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  በምርት ዘመኑ  ከሚለማው መሬት   989 ሺህ 402 ሄክታሩ  በዘር ተሸፈነ

አሶሳ ፤ ነሐሴ 3/2016(ኢዜአ):-  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተያዘው  የምርት ዘመን ከሚለማው  መሬት ውስጥ 989 ሺህ 402 ሄክታሩ በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። 

የቢሮው ሃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ በ2016/2017 የምርት ዘመን  አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል። 

ከዚህም እስካሁን 989 ሺህ 402 ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን አስታውቀዋል።


 

በምርት ዘመኑ ከሚያስፈልገው 203 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ 82 በመቶ ወደ አርሶ አደሩ መድረሱን አስረድተዋል።  

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመሬት ለምነት እና ዘላቂ ልማት ያለውን ጠቀሜታ የክልሉ አርሶ አደሮች  በተግባር እየተረዱ መመጣታቸውን ጠቅሰው፤  በምርት ዘመኑ ከሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል በላይ አዘጋጅተው እየተጠቀሙ እንደሆነ አብራርተዋል። 

እንዲሁም የአርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እያደገ መምጣቱን አመልክተው፤ በምርት ዘመኑ እስካሁን ከለማው መሬት 150 ሺህ ሄክታር የሚጠጋው መሬት በትራክተር መታረሱን በአብነት ጠቅሰዋል።

በምርት ዘመኑ እስካሁን በ168 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም እርሻ  እንደተሸፈነ ሃላፊው አስረድተዋል።:

የቅባት፣ የጥራጥሬ፣ የብርዕ እና ሌሎች ሰብሎችም በዘመኑ የሚለማው የሰብል ዓይነት እንደሆነ ሃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ አሶሳ ዞን የኡራ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ታጀዲን መሃመድ፤  በወረዳው እስካሁን ከ65 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተርና ለውዝ ሰብል መልማቱን ገልጸዋል። 

ግብዓት በወቅቱ በማቅረብ አርሶ አደሩ ምርታማ እንዲሆን ካለፈው የመኸር ምርት ዘመን የተሻለ ርብርብ መደረጉን ጠቁመዋል። 

ከኡራ ወረዳ አርሶ አደርች መካከል አቶ በርኬሳ መስፍን በሰጡት አስተያየት፤ ባለፈው የመኸር እርሻ በሄክታር 85 ኩንታል በቆሎ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል። 

በዚህ የምርት ዘመን ደግሞ የተሻለ ውጤታማ ለመሆን ምርጥ የበቆሎ እና ማሽላ ዘር እንዲሁም ማዳበሪያ ተጠቅመው ያለሙት የሰብል ቡቃያ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አመልክተው፤ ምርታማ ለመሆን የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ2016/2017 የምርት ዘመን  ከለማው መሬት   45 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም