ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤታማ እንዲሆን ገቢን ዘመናዊ በሆነ የአሰራር ስርአት ለመሰብሰብ በትኩረት ይሰራል - አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ  ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ ውጤታማ እንዲሆን ገቢን ዘመናዊ በሆነ የአሰራር ስርአት በተገቢው መንገድ ለመሰብሰብ በትኩረት እንደሚሰራ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድሽዴ ተናገሩ።

የገቢዎች ሚኒስቴር ከመካከለኛ ግብር ከፋዮች ጋር በታክስ ህግ ተገዥነትና በማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ይገኛል። 

በውይይት መድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የማዘመንና እድገትን በዘላቂነት የማረጋገጥ ዓላማ ያለው ነው። 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ ቢመጣም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሳይደረግ መቆየቱ የራሱን ተጽእኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።


 

በቅርቡ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ገቢን በማሳደግ ወጪን በራስ አቅም የመሸፈን ዓላማ ያለው ነው ብለዋል። 

በተጨማሪም ታክስ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለውን ምጣኔ ማሻሻል እንዲሁም ምርታማነትን በማሳደግ የወጪ ንግድ አቅምን ማጎልበት የሪፎርሙ ትኩረት መሆኑን ጠቁመዋል። 

የሪፎርም ፕሮግራሙ የአገሪቱን የዕዳ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስና የፋይናንስ ስርአቱን ለማዘመን የሚያግዝ  መሆኑን ገልጸዋል።   

በኢትዮጵያ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር የግሉ ዘርፍ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የገለፁት። 

በመሆኑም ለሪፎርም ፕሮግራሙ ትግበራ ውጤታማነት ምርታማነትን ማሳደግና ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

ለዚህም በተለይ ግብር ከፋዮች ገቢን በአግባቡ በማሳወቅና የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል አገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል። 

መንግስት ገቢ በወቅቱና በትክክለኛ መልኩ እንዲገባ በማድረግና ግብር የሚሰውሩ ላይም ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ህግ የማስከበር ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርምን ለማሳካት ሁሉም ግብር ከፋይ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባና ገቢን ዘመናዊ በሆነ የአሰራር ስርአት በተገቢው መንገድ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

ለዚህም መንግስት ገቢን ዘመናዊ በሆነ የአሰራር ስርአት በተገቢው መንገድ ለመሰብሰብ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው ባለፉት አምስት ዓመታት የሚሰበሰበው ገቢ እስከ ሶስት እጥፍ የሚደርስ እድገት የታየበት መሆኑን ተናግረዋል። 


 

በ2010 የተሰበሰበው ገቢ 170 ቢሊየን ብር እንደነበር አስታውሰው በ2016 የተሰበሰበው ገቢ 512 ቢሊየን ብር መሆኑን አብራርተዋል። 

የገቢ አፈጻጸም እድገት እያሳየ ቢሆንም ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት አኳያ ያለው ድርሻ ዝቅ ያለ በመሆኑ ይህንን ለማሻሻል ከግብር ከፋዩ ጋር መምከር አስፈልጓል ነው ያሉት። 

በቀጣይ በታክስ ስርዓቱ ውስጥ ያሉና በአዲስ መልክ የሚገቡ ግብር ከፋዮች የታክስ ህጉን አክብረው ግብራቸውን እንዲከፍሉ፣ ዲጂታል የታክስ አስተዳደር ስርዓትን ለማጠናከርና የዳበረ የታክስ የስራ ባህል ለማምጣት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም