ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚጠበቁበት የ10ሺህ ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ዛሬ ይደረጋል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 3/2016 (ኢዜአ)፦በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ ማምሻውን የሚደረገው የ10ሺህ  ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ተጠባቂ ነው።

ውድድሩ 80 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታደ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ57 ደቂቃ ላይ ይከናወናል።

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ፣ አትሌት ፅጌ ገብረሰላማና አትሌት ፎትዬን ተስፋይ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።

ጉዳፍ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ኢውጂን በተካሄደ ውድድር 29 ደቂቃ ከ05 ሴኮንድ ከ92 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

አትሌቷ በ5000 ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። ነገ በሚካሄደው የ1500 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ላይም ትወዳደራለች።

ጉዳፍ በኦሊምፒክ ውድድር ስትሳትፍ የዘንድሮው ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ከ3 ዓመት በፊት በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ5000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።

የረጅም ርቀት ሯጯ ፅጌ ገብረሰላማ በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ካሊፎርኒያ በተካሄደ ውድድር 29 ደቂቃ ከ48 ሴኮንድ ከ34 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን ማስመዝገብ ችላለች። 

ፅጌ በኦሊምፒክ ስትሳተፍ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ10ሺህ ሜትር ሮጣ ውድድሯን ሳትጨርስ መቅረቷ የሚታወስ ነው። 

በኦሊምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን የምታደርገው አትሌት ፎትዬን ተስፋይ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም በስፔን ኔርጃ ከተማ በተካሄደው የኦሊምፒክ የማጣሪያ ውድድር 29 ደቂቃ ከ47 ሴኮንድ ከ71 ማይክሮ ሴኮንድ የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።


 

በ10000 ሜትር የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ኬንያዊቷ አትሌት ቢትሪስ ቺቤትና በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው አትሌት ሲፋን ሀሰን የኢትዮጵያ አትሌቶች ዋነኛ ተፎካካሪ ናቸው።


 

ቺቤት በ5000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወቃል።

በፍጻሜው ውድድር 25 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

ኢትዮጵያ እስካሁን በኦሊምፒኩ ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት 63ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። 

አሜሪካ፣ ቻይና፣ አውስትራሊያ፣ ፈረንሳይና ታላቋ ብሪታኒያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም