የሽግግር ፍትሕ ለምን? ወደየት? - ኢዜአ አማርኛ
የሽግግር ፍትሕ ለምን? ወደየት?

በአየለ ያረጋል (ኢዜአ)
መንደርደሪያ....
‘ፍትሕ’ ረቂቅ ጽንሰ ሃሳብ ነው-የተቀደሰ። ከሰው ልጅ ዘፍጥረት ይቀዳል። ተፈጥሯዊም፣ ኑባሬያዊም አንድምታ አለው። የሥነ ምግባር፣ የሥነ ሕግ እና የሥነ ሥርዓት መልክና ልክ ማንጸሪያ ነው። በአምላካዊ አስተምህሮ የተደነገገ፣ በሰብዓዊ እሳቤ በጣሙን የተፈለገ፣ የግብረ-ዕኩይ ማርከሻ፣ የብሩሕ ፍኖት ማሰሻም ጭምር ነው። “ፍትሕ አይጓደል፤ ደሃ አይበደል” እንዲል ሀገሬው በትውፊቱ፣ ፍትሕ ለሰው ልጆች የተስተካከለ ኑሮ፣ ለቀና የሕይወት ጎዳና፣ ከተሰናከለ ትናንት ማካካሻ፣ ወደ ተሻለ ነገ መሻገሪያ ድልድይ ነው። በቀል የሚያሽር፣ ሠላምና አብሮነት የሚያጸና፣ ሕይወት የሚያስተምር፣ የተዛነፈ ድርጊት በአመክንዮ መዝኖ የሚያቃና፣ ዕኩልነትና ክብርን ያጣመረ፣ የፍርድ ሚዛንን ያዘለ፣… ጽንሰ ሃሳብ ነው። የፍትሕ አስተኔ እና ክዋኔ የተለያየ መልክ ሊኖረው ይችላል። እሳቤው ግን ይኸው ነው። በዚህ ፅሁፍ ከፍትሕ አስተኔዎች መካከል የ‘ሽግግር ፍትሕን” (የሽግግር ወቅት ፍትሕን) ይቃኛል።
የሽግግር ፍትሕ ምንነት እና ታሪካዊ ዳራ
የሽግግር ወቅት ፍትሕ ትርጓሜ ከስያሜው ይነሳል። በማኅበረሰብ የሥርዓት እና የዘመን ምዕራፍ ሽግግር ወቅት የሚተገበር እና በዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ ተቋማት እንዲሁም በአገራት መንግሥታት ሰነዶች ተቀራራቢ ትርጓሜና አንድምታ የተሰጠው ፅንስ ሃሳብ እና እርምጃ ነው። ይኸውም በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ግጭትን ጨምሮ በአያሌ መነሻዎች በደል፣ ሰቆቃ፣ ጭቆና፣ ግፎች እና ሌሎች መልከ ብዙ የሠብዓዊ መብት ጥሰትን ያስተናገዱ ወገኖች እንዲካሱ፣ በዳዮች እንዲክሱ እና ዕርቅና ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ማስቻል የሚል ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ሰነዶች እንደሚያስረዱት የሽግግር ወቅት ፍትሕ ሂደት ከበደልና ጭቆና ተላቆ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ወሳኝ አማራጭ ነው። የተሻለ ነገ ለመገንባት በተንሸዋረረ ትናንት ላይ ፍትሕና ተጠያቂነት ማስፈን ሁነኛ ስንቅ ነው። በተለይም በመደበኛ የሕግ ሥርዓት መዳኘት ላልቻሉ፤ በታሪክ አጋጣሚ ለተፈጸሙ አይነተ ብዙ ችግሮች በዘላቂነት ዕልባት ለመስጠት አይነተኛ መሣሪያ ተደርጎ ይወሰዳል።
የዓለም አቀፉ የሽግግር ፍትሕ ማዕከል “አገራት በድሕረ ግጭት፤ በመደበኛ የፍትሕ ሥርዓታቸው አጥጋቢ ወይም በቂ ዳኝነት ወይንም ፍትሕ ላልተሰጣቸው ከፍተኛ፣ የተደራጁና በርካታ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች ምላሽ የሚሰጡባቸው መንገዶች” ይላቸዋል። ይኸውም ዘላቂ ሠላምና ልማት ዕውን ይሆን ዘንድ ቅድሚያ ‘የበደለ ክሶ፣ የቀማ መልሶ’ አይነት የሦስተኛ ወገን ዳኝነት እንደሚያሻ ያስረዳል። የተመድ ከፍተኛ የሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ደግሞ “ከአቅም በላይ ለሆኑና ልዩ ባሕሪይ ባላቸው የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ” በማለት ያብራራል።
በተመሳሳይ የአፍሪካ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲም በተለይ አፍሪካዊ አገራት በቅኝ ግዛት፣ በአፓርታይድ፣ በባርነት፣ በእርስ በእርስ ግጭቶችና መሰል አስከፊ የታሪክ በደሎች ፈውስ ለማግኘት ሲባል የሽግግር ፍትሕ ሂደት ገቢራዊ ስለመደረጉ ያትታል። ይህም ለተፈፀሙ ጥፋቶች ዕውቅና መስጠት፣ የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና ዘላቂ ሠላምና ደህንነት የማረጋገጥ ግቦች የያዙ ናቸው።
በአፍሪካ የሽግግር ወቅት ፍትሕ ፖሊሲ ላይ እንደተጠቀሰው የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ዓላማዎች ዕውነትን መፈለግና ማወቅ፣ ተጎጂዎችን መልሶ ማቋቋም፣ የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና የደረሰው በደል ዳግም እንዳይከሰት ዘላቂ የማሻሻያ መፍትሔ/እርምጃ መውሰድ ነው። ከሠብዓዊ መብቶች አኳያ የሽግግር ወቅት ፍትሕ ከአጀንዳ 2063 ግቦች ጋር እንደሚጣጣም የፖሊሲ ሰነዱ ያስረዳል።
በሌላ በኩል የሽግግር ፍትሕ ለጉዳት ሰለባዎች ዕውቅና ከመስጠት ባሻገር በሠብዓዊ መብት መከበርና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ብሎም በሕዝቦች መካከል ዕርቅ ለመፍጠር ያግዛል።
የሽግግር ፍትሕ ሂደት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት (በፈረንጆች የዘመን ቀመር ከ1939-1945) ወቅት በአውሮፓ የተፈጸሙ ሥርዓታዊ ግፎችን መነሻ በማድረግ እንደተጀመረ ታሪክ ያስረዳል። ለአብነትም የጀርመን ናዚ መሪዎች በጦርና በዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተከሰው ታሪካዊ ውሳኔ አግኝተዋል። በጃፓን የተቋቋመው የቶኪዮ ወታደራዊ ችሎትም በተመሳሳይ ለሽግግር ፍትሕ እሳቤ መጠንሰስ እርሾ ሆኗል። በአውሮፓዊያን አቆጣጠር 1945 በግሪክ፣ በ1983 በአርጀንቲና መሰል የፍርድ ሂደቶች ተከናውነዋል። የሽግግር ፍትሕ በ1970 እና 1980ዎቹ በሠብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ በማተኮር ዓለም አቀፍ የሠብዓዊ መብት የሕግ ማዕቀፎች እንዲወጡ አድርጓል። በካናዳ፣ በአውስትራሊያና በኒውዚላንድ ነባር የኅብረተሰብ ክፍሎች ለተፈፀመባቸው ጭቆና በዚህ ሂደት ምላሽ ለመስጠት ተሞክሯል። የሽግግር ፍትሕ ተሞክሮዎች አገራትን ከነበሩበት ቀውስ ወደ ተሻለ ሠላም በማምጣት፣ መረጋጋት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲያሰፍኑ አግዟል። ኮሎምቢያን፣ ደቡብ አፍሪካን፣ ዩጋንዳና ሴራሊዮንን ዋቢ ማድረግ ይቻላል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የአፍሪካ ሕብረት ‘ማኅበረሰቡ ያለፉ መጠነ ሰፊ ጥሰቶችን፣ ክፍፍሎችን እና አለመመጣጠኖችን ለማስወገድ፤ ፍትሕ ለማስፈን እና እርቅ ለማውረድ፤ ለደኅንነትም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሥርዓት ግንባታ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት’ የሚል ትርጓሜ ሰጥተውታል። ለዚህም መደበኛ ወይም ኢ-መደበኛ (ባሕላዊ) የፖሊሲ እርምጃዎች የሚወሰዱበትና ተቋማዊ አሠራሮች የሚተገበሩበት ሂደት እንደሆነ የተቋማቱ ሰነዶች ይገልጻሉ።
ሂደቱ ዕውነትን ማፈላለግ እና ይፋ ማውጣት፣ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ ለተጎጂዎች ማካካሻ መስጠትና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ የሚሉ መሰረታዊ ስልቶችን ይከተላል። በዋናነትም የተፈጸሙ ጥሰቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ ዋስትና መስጠት ናቸው።
የሽግግር ፍትሕ ከአምባገነን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸገጋሪያ ምቹ መደላድል ይፈጥራል። ላለፉ ቁርሾዎችና ላልሻሩ ቁስሎች መፍትሔ ያበጃል። ለችግሮች መፍቻ የዳኝነት ሥርዓት ያነብራል። በባህል ዕርቆች የተሟላ ካሳ ያሰጣል። ተጠያቂነትን ያሰፍናል። ቁርሾን ፈቶ፣ የሕግ ተጠያቂነትን አረጋገጦ፣ በዜጎችና በመንግሥታት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሰምርና ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲገነቡም ያስችላል።
በሽግግር ፍትሕ ሂደት ውጤታማነት የዕውነት አፈላላጊ ኮሚሽኖች ተቋቁመው ይተገበራሉ። ለምሣሌ በ1983 (እ.ኤ.አ) በአርጀንቲና፣ በ1990 (እ.ኤ.አ) በቺሊ እንዲሁም በ1995 (እ.ኤ.አ) በደቡብ አፍሪካ የተቋቋሙ የሐቅ አፈላላጊዎቸ በአርዓያነት ይጠቀሳሉ።
የሽግግር ፍትሕ በኢትዮጵያ
የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ በኢትዮጵያ ጎልቶ መሰማት የጀመረው ከፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት በኋላ ነው። በተለይም በ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ እንዲወጣ እንቅስቃሴ ተጀመረ። በሌላ በኩል የሠብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት (የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ) በተደጋጋሚ ድሕረ ጦርነት የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ እንዲደረግ ምክረ ሃሳብ ሲያቀርቡም ተደምጠዋል።
ያም ሆነ ይህ ግን እንደ አገር ኢ-ፍትሃዊነት በዕርቅና ይቅርታ መፍትሔ ለመስጠት በቅድሚያ አስቻይ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት ታምኖበት የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጭ ሰነድ የማዘጋጀት ቀዳሚ እርምጃ መስመር ያዘ። በወርኃ ጥር 2015 ዓ.ም በፍትሕ ሚኒስቴር ስር የተቋቋመ ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ተደራጅቶ ወደ ሥራ ገባ። የባለሙያዎቹ ቡድን ከመላ አገሪቱ ተወካዮች ጋር ውይይቶች አካሄደ፤ ግብዓት አሰባሰበ። ከ15 ያላነሱ የዝግጅት ወራትን ፈጅቶ ረቂቅ ፖሊሲውን አዘጋጀ። በቅድመ-ፖሊሲ ማርቀቅ ሂደቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ እና የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ የዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማት ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በሚያዚያ 2016 ዓ.ም ረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ስራ ላይ እንዲውል በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቋል። ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የትግበራ ምዕራፍ ማስጀመሪያ መርሐ ግብርም ተካሂዷል። የፖሊሲው ዓላማም የኢትዮጵያን ዓውድ ያገናዘበ፣ የተቀናጀ እና የተናበበ የሽግግር ፍትሕ ሂደት በመተገበር ዘላቂ ሠላም፣ ዕርቅ፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ የሚረጋገጥበትን መደላድል መፍጠር ነው። ፖሊሲው ከትናንት የተሻገሩ ተደራራቢና መጠነ ሰፊ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ያልጠሩ ትርክቶች እና በደሎችን በዕውነት፣ በዕርቅ፣ በምሕረት፣ በፍትሕ ላይ የተዋቀረ እና በግልፅ ፖሊሲ የሚመራ ሁለንተናዊ የሽግግር ፍትሕ ስልትን አካታች፣ በሆነ መንገድ እንዲተገበሩ ግብ ይዟል።
የፖሊሲውን አስፈላጊነት በተመለከተ በመግቢያው ላይ “የሽግግር ፍትሕ ትግበራው በዓለም አቀፍ እና አህጉር−አቀፍ ሰነዶች ላይ የተመላከቱ መርሆዎችን በተከተለ አግባብ የሚካሄድበትን አሰራር ለማረጋገጥ፣ በአጠቃላይ ወጥነት ያለው፣ ግልጽ፣ ተጠያቂነት እና ፍትሕን የሚያሰፍን የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ሂደትን ለመምራት እንዲቻል ይህን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል” ይላል።
የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ በተለያዩ ወቅቶች ካነጋገራቸው የባለሙያዎች ቡድን አባላት መካከል ማርሸት ታደሰ (ዶክተር)፤ የሽግግር ፍትሕ ለፖለቲካና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውጤታማነት ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል። የሽግግር ፍትሕ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ በደሎችና ቁርሾዎችን በዕውነት፣ በፍትሕና በዕርቅ በመሻገር ዘላቂ ሠላምና ፍትሕ ለማስገኘት ያግዛል ሲሉ ያነሳሉ። የሽግግር ፍትሕ ሰነዱ ዓላማ ምሕረት መስጠትን፣ የሕግና ተቋማት ማሻሻያ ማድረግን፣ ማካካሻ መስጠትን፣ ዕውነት ማፈላለግ እና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሆነም እንዲሁ። ኢትዮጵያ በአምባገነናዊ ሥርዓት ውስጥ የደረሰባትን ቁስል፣ በደልና የሠብዓዊ መብት ጥሰት በሽግግር ፍትሕ እንድትፈታም ነባራዊ ሁኔታዋን የዋጀ የሽግግር ፍትሕ መተግበር ያሻታል።
ሌላው የባለሙያዎች ቡድን አባል አዲስ ጌትነት በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች የማኅበረሰቡን ማኅበራዊ መስተጋብር እየሸረሸሩ የአገር ሕልውናን ሲፈታተኑ ተስተውለዋል ይላሉ። የፖሊሲ ሰነዱም ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ችግሮችን በሽግግር ፍትሕ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚረዳ ይናገራሉ።
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው አንኳር ይዘቶች
የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሦስት ክፍሎችን አቅፏል። የፖሊሲው ዓላማ፣ መርሆዎች፣ የተፈጻሚነት ወሰንና መሰል ጉዳዮች ጠቅላላ በሚል በክፍል አንድ ተካተዋል። ስለ ወንጀል ተጠያቂነት፣ ዕውነትን ማፈላለግ፣ ዕርቅ፣ ምሕረት፣ ማካካሻ፣ ተቋማዊ ማሻሻያና ስለ ፖሊሲው ትግበራ የጊዜ ወሰንና መሰል ነጥቦች ደግሞ የፖሊሲ ጉዳዮችና አቅጣጫዎች በሚል በሁለተኛው ክፍል ተብራርተዋል። በሦስተኛው ክፍል ደግሞ የመንግሥት እና የባለድርሻ አካላት ሚና እና የድጋፍ ሥርዓትን ይዳስሳል።
የፖሊሲው አጠቃላይ ዓላማ “የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውድ መሰረት ያደረገ፣ የተቀናጀ እና የተናበበ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚመራበት እና የሚተገበርበትን ሥርዓት በመዘርጋት ዘላቂ ሠላም፣ ዕርቅ፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ የሚረጋገጥበትን መደላድል መፍጠር ነው” ይላል።
የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ “የወንጀል ምርመራ በማካሄድ እና ክስ በመመስረት አጥፊዎች ተጠያቂ የሚሆኑበትን ሥርዓት የሚዘረጋ ይሆናል” በማለት ያብራራል። ምርመራና ክስ የሚከናወነው ‘በጉልህ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ብቻ ያተኮረ’ እንደሚሆንም እንዲሁ።
በዚህ ረገድ ፖሊሲው “ጉልህ የሠብዓዊ መብት ጥሰት ማለት መጠነ ሰፊ፣ ስልታዊ፣ ወይም ተከታታይነት ባለው ሁኔታ፣ ዓለም-አቀፍ የሠብዓዊ መብት ሕጎችን፣ ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግን ወይም የሠብዓዊነት ሕግን በመጣስ የሚፈጸም/ጥሰት ሲሆን በወንጀሉ ዓይነት እና በደረሰው የጉዳት መጠን መሰረት ተደርጎ የሚለይ ሌላ ወንጀልን ያካትታል” ሲል ይተረጉመዋል።
ክስ የሚመሰረትባቸውን አጥፊዎች ማንነት በተመለከተም “ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች አንጻር በሁሉም አጥፊዎች ላይ ምርመራ ማካሄድ እና ክስ መመስረት ተመራጭ አካሄድ አይሆንም…. በከፍተኛ ደረጃ ተሳትፎ ባላቸው አጥፊዎች ላይ ብቻ ይሆናል” ሲል ያትታል።
የወንጀል ምርመራ እና ክስ የሚከናወንበትን ተቋማዊ አሰራር በተመለከተ ደግሞ ክስና ምርመራው የሚከናወነው ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ራሱን ችሎ በሚቋቋም ልዩ ዐቃቤ ሕግ ተቋም ሲሆን የፍርድ ሂደቱም በመደበኛው ፍርድ ቤቶች ስር “የተለየ የራሱ አደረጃጀት የሚኖረው ልዩ ፍርድ ቤት የሚደራጅ ይሆናል” በሚል ይገልጸዋል። “በአገር ውስጥ የማይገኙ ከፍተኛ ደረጃ የወንጀል ተሳትፎ ያላቸው አጥፊዎች ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ከሚገኙበት አገር ተላልፈው እንዲሰጡ ለማድረግ ተገቢ ስራ ይሰራል” በማለትም ያክላል።
ከወንጀል ተጠያቂነት፣ ተፈጻሚነት ወሰን አኳያም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከጸደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ አስቀምጧል።
ፖሊሲው “ዕውነትን የማፈላለግ፣ ይፋ የማውጣት እና የዕርቅ ተግባራት ከተጽዕኖ እና ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ በሚቋቋም አዲስ የዕውነት አፈላላጊ ኮሚሽን አማካኝነት እንዲከናወኑ ይደረጋል” ሲል ያትታል። በፖሊሲው መሰረት በጉልህ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች ከፍተኛ ተሳትፎ ያላቸው አጥፊዎች የምሕረት ተጠቃሚዎች አይሆኑም።
ከማካካሻ አኳያ በሠብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ኢ-ፍትሐዊ አሰራሮች ምክንያት ተጎጂ የሆኑ ግለሰቦች እና ማኅበረሰቦች የጉዳቶችን ዓይነት እና መጠን መሰረት በማድረግ የማካካሻ ሥርዓት እንደሚተገበር ይገልጻል።
የትግበራ ሂደቱ ልዩ ትኩረት ለሚሹ እና ለጉዳት ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ለሴቶች፣ ለሕፃናት፣ ለወጣቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋዊያን እና ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ ፍላጎት እና ጥቅም ትኩረት በሚሰጥ አግባብ እንደሚከናወንም እንዲሁ።
ከባሕላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች አኳያም “በሽግግር ፍትሕ ሂደት ከሌሎች የሽግግር ፍትሕ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እውነትን በማፈላለግ፣ ዕርቅ በማስፈን፣ በማካካሻ እና በምሕረት መስጠት ተግባራት እንዲሁም ማኅበረሰባዊ ሠላም ለማስፈን በሚደረጉ ስራዎች ማዕቀፍ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ይደረጋል” ይላል።
ፖሊሲው የመንግሥትና የባለድርሻ አካላትን ሚና በተመለከተ የሽግግር ፍትሕ ስልቶቹን በተቀናጀ መንገድ በመደጋገፍ እና በትብብር ለመተግበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚኖራቸውን ተሳትፎና ሚና በግልጽ አመላክቷል። ፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ የመንግሥት ተቋማት “የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚቋቋሙ ወይም የሚደራጁ ተቋማት ሊያጋጥማቸው የሚችል የሰው ኃይል፣ የበጀት እና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን ለመቅረፍ የሚያስችል እገዛ ማድረግ አለባቸው” በማለት ደንግጓል።
መንግሥትዊ ካልሆኑ ተቋማት መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚና ከሽግግር ፍትሕ ሥርዓት አተገባበር ጋር በተያያዘ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ሚና የሚኖራቸው አካላት ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ያትታል። ለምሣሌ ከጉዳዩ ጋር ጥብቅ ትስስር ካለው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር በተያያዘ “የሽግግር ፍትሕ የትግበራ ሂደትና አገራዊ ምክክሩ ተመጋጋቢ በሆነ መልኩ ተግባራዊ የሚሆኑበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል።” ይላል ፖሊሲው።
የሽግግር ፍትሕ . . .
የሽግግር ፍትሕ ከዓለም አቀፋዊ ጽንሰ ሃሳብና ግቡ አኳያ ለኢትዮጵያ የሚኖረው አስፈላጊነት አያጠራጥርም። ለምን ቢሉ በኢትዮጵያ ከትናነት እስከ ዛሬ የእርስ በእርስ ግጭት፣ ጦርነት እና መልከ ብዙ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተስተናገዱ መሆኑ እሙን ነውና። በታሪክ አጋጣሚ አይነተ ብዙ በደልና ሰቆቃዎች ተፈጽመዋል። ኢትዮጵያ የቁርሾ እና የቂም በቀል አዙሪት አልተለያትም። ፖለቲካዋ በጨቋኝና ተጨቋኝ ስሁት ትርክት የተለወሰ ነው። ስለዚህ በደሎችን ለማከም፣ ሠላምና ዴሞክራሲ የሰፈነበት ሥርዓት ለመገንባት የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ቅንጦት ሳይሆን መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነ የማኀበራዊ ጉዳይ ምሁራን ይናገራሉ። የተራዘሙና የተሻገሩ ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታት፣ በሕዝቦች መካከል መተማመንን መፍጠር፣ ለተፈጸሙ መጠነ ሰፊ የመብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች ምላሽ መስጠት፣ ፍትሕን ማስፈን እና ዕርቅን መተግበር አንዱ አማራጭ ነው።
በተለይ ከትናንት ችግሮች እያመረቀዙ ለሌላ ግጭትና ደም መፋሰስ የሚዳርጉ ቁስሎችን በዚህ አገባብ ማከም ግድ ይላል። ያለፉ አገራዊ በደሎችንና ቁርሾዎችን የአገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታና ባሕሪይ ባገናዘበ አግባብ ኢ-ፍትሃዊነትን በፍትሕ፣ በእርቅና በይቅርታ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ሲናገሩ ይደመጣል። ዘላቂ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ያመጣልና።
በእርግጥ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የበዳይ ተበዳይን አዙሪት ለመስበር የሽግግር ፍትሕ አንዱ ተመራጭ ሥልት መሆኑን ጠቅሷል። የመንግሥት ቁርጠኝነት መኖሩ ደግሞ ለሽግግር ፍትሕ ትግበራውና ሂደቱ መሳለጥ እንደሚበጅ ይታመንበታል።
በተለያዩ ጊዜያት በሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነትና ትግበራ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡ የሥነ-ልቦና፣ የታሪክና የባሕል ባለሙያዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች የየራሳቸውን ምልከታ ያነሳሉ። የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ዋና ፀሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ የፍትሕ ጉዳይ በሃይማኖታዊ አስተምህሮ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው፣ የዕርቅና የምሕረት ምንጭ እንደሆነ ይናገራሉ።
የሥነ-ልቦና ባለሙያዋ ሠብለ ኃይሉ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ያላባሩ ግጭቶችና ቀውሶች አንዱ መንስኤ ቀደም ሲል በአገሪቷ ለተፈጸሙ ጥፋቶች ዕልባት ባለመሰጠቱ እንደሆነ ያነሳሉ። የሽግግር ፍትሕ ለማካሄድ መወሰኑ ከግለሰብ እስከ አገር ወሳኝ ሚና በማንሳት፣ በሽግግር ፍትሕ ሂደት ችግሮችን በማከም መሻገር ይገባናል ይላሉ።
የቀድሞ የዕርቀ ሠላም ኮሚሽን አባል ልዑል በዕደማርያም መኮንን እና የኢትዮጵያ አገር ሽማግሌዎች መማክርት ጉባዔ አባል ፕሮፌሰር አህመድ ዘከሪያ የሽግግር ፍትሕ ማስፈጸሚያ ፖሊሲ መዘጋጀቱን እንደ ትልቅ እርምጃ ይወስዱታል። ፖሊሲው በማኅበረ-ኢኮኖሚው ዘርፍም ሁነኛ አገራዊ ሚና እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።
በአስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ የሽግግር ፍትሕን ሁሉንም ያሳተፈ በማድረግ ለሕዝብ እፎይታ በሚሰጥ አግባብ መከወን ይገባል። የትናንትናን ችግር ፈትሾ በሽግግር ፍትሕ መፍትሄ በመስጠት የተሻለ ነገን መገንባት ላይ ማተኮር እንደሚያሻም አንስተዋል። የሽግግር ፍትሕ ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በአጠቃላይ ፖሊሲው የኢትዮጵያን የተራዘሙና የተወሳሰቡ ችግሮች በሽግግር ፍትሕ አማራጭ የመውጣቱን ፋይዳ እና ትግበራ በተመለከተ ፖሊሲው እንዲህ አስቀምጦታል።
“በአገር አቀፍ ደረጃ በተደረጉ ሕዝባዊ ምክክሮች የተገኙ ግብዓቶችን ታሳቢ በማድረግ በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ የተፈጠሩ ውስብስብ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል አሳታፊ፣ አካታች፣ ከዓለም-አቀፍ የሰብዓዊ መብት መርሆዎችና ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣመ፣ መሰረታዊ የሽግግር ፍትሕ መርሆዎችን የተከተለ፣ የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ፣ እንዲሁም አፈፃፀሙን አሳታፊ እና ሠብዓዊ መብት ተኮር በሆነ አካሄድ በመምራት እና ስልቶችን በተሰናሰለ መልኩ በመተግበር ዘላቂ ሠላም፣ የሕግ የበላይነት እና ፍትሕን ለማረጋገጥ የሚያስችል የሽግግር ፍትሕ ሂደት በአገር-አቀፍ ደረጃ መተግበር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ወጥቷል።”
ለሒደቱ ተስፋዎችና ምክረ ሃሳቦች
የሽግግር ፍትሕ ሂደት ውጤታማ ለመሆን ደግሞ ሁሉን አሳታፊ፣ የሕግ ተጠያቂነት፣ ፍትሕ፣ እርቅ እና ካሳን ጭምር ታሳቢ ያደርጋል። ሂደቱ የይቅርታና የምሕረት ጉዳዮችን ያቅፋል።
የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍን በተመለከተ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች ማክበር ያለባቸውን መርሆዎች አስቀምጧል።
👉ዐውድ-ተኮር፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ተቋማዊ እና ሕጋዊ አደረጃጀት፣ ታሪክ፣ ባሕል እና ፍላጎቶች እንዲሁም ጥያቄዎች ላይ በመመሥረት በየአካባቢው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች በመለየት ተፈጻሚነት ያላቸው ዓለም አቀፍ ደንቦችን ያከበረ ሊሆን ይገባል።
👉ሥርዓተ-ጾታን ያማከለ፡- በሁሉም ሂደቶች ሴቶችን ማካተት፣ ጾታዊ እኩልነትን ማስፈን፣ በጾታዊ ጥቃቶች እና በሥርዓተ-ጾታ ላይ የተመሠረቱ ጥሰቶች እና ዋና መንስኤዎቻቸው ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት።
👉ሁሉንም ኅብረተሰብ የሚለውጥ፡- የሽግግር ፍትሕ ሂደት የተጎጂዎችን ፍላጎቶች በማሟላት እና አለመመጣጠኖችን ጨምሮ ፍትሐዊ ያልሆኑ የሥልጣን መዋቅሮችን፣ ሥር የሰደዱ አድልዎ እና አግላይ አሠራሮችን፣ ተቋማዊ ጉድለቶችን እና ለሌሎች መሰል የመብቶች ጥሰት ዋና መንስኤ የሆኑ ጉዳዮችን በመፍታት እንዲሁም ሠላም እና ደኅንነትን አደጋ ላይ ለሚጥሉ ሁኔታዎች መፍትሔ በማበጀት ጉልህ ማኅበረሰባዊ ለውጥን ለማምጣት የሚያስችል ዕድል ተደርጎም ሊወሰድ ይገባል።
👉የሽግግር ፍትሕን የማስፈጸም ኃላፊነት፡- የኢትዮጵያ መንግሥት በሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተደገፈ ከአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጋር በተጣጣመ መልኩ የሽግግር ፍትሕ ሂደቶችን የማስፈጸም ኃላፊነት አለበት።
👉የሽግግር ፍትሕ አካሎችን ማቀናጀት፡- የሽግግር ፍትሕ ተግባራትን የማቀናጀት ምርጫ፤ የሠላምና የዕርቅ እንዲሁም የፍትሕና የተጠያቂነት ዓላማዎችን ተደጋጋፊነትና አካታች ልማትን ለማረጋገጥ መጣር አለበት።
👉ትብብር እና ቅንጅት፡- ሠላም ፍትሕ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያለው ግፊት እንዲሁም የበርካታ ተዋናዮች መገኘት እና የሁሉም አካላት ትብብር እና ቅንጅት እጅግ አስፈላጊ ነው። የአገራዊ ባለቤትነትን፣ የአፍሪካዊ አመራርን፣ ሕጋዊነትን እና ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ሚናዎችን እና ኃላፊነቶችን ማብራራት እና መግለጽ ያስፈልጋል።
👉የአቅም ግንባታ ለዘላቂነት፡- ኅብረተሰቡ አገራዊ ሂደቶች እና ተቋማትን የሚደግፍበትና የሚያሳድግበትን አቅም ከማጠናክር አኳያ፤ ሁሉም የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች የአቅም ግንባታ አካል ሊኖራቸው ይገባል።
በርካታ የዓለም አገራት በሽግግር ፍትሕ ዕውነትን ፈልገው፣ የወንጀል ተጠያቂነትን አስፍነው፣ ካሳን አስክሰው፣ ዘላቂ ሠላም፣ ፍትሕና ዕርቅ ለመፍጠር ሂደቱን ተጠቅመውበታል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ደቡብ አፍሪካ፣ ሴራሊዮን፣ ላይቤሪያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋምቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ዩጎዝላቪያ፣ ቺሊ፣ እንዲሁም ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል።
አገራቱ የሽግግር ፍትሕን ከነበሩበት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ተላቀው የተሻለ ነገን ለመገንባት የተጠቀሙበት ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ደቡብ አፍሪካና ጋምቢያ ተጠቃሾች ናቸው። እንደ ዕድል ሆኖ በሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ምርምር ያደረጉ የሁለቱ አገራት ምሁራንን በአካል አግኝቼ የማነጋገር ዕድል ገጥሞኝ ነበር። ምሁራኑ ደቡብ አፍሪካ እና ጋምቢያ በሽግግር ፍትሕ ሂደት ያለፉበት መንገድ ለኢትዮጵያ የተሻለ ተሞክሮ እንደሚሰጥ አውስተውኛል።
በደቡብ አፍሪካው ፍሪታውን ዩኒቨርሲቲ የፍትሕና ዕርቅ ኢንስቲትዩት ኃላፊ እና በአፍሪካ ጥናትና ምርምር የካበተ ልምድ ያላቸው ፕሮፌሰር ቲም ሙሪቲ በአፍሪካ የሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ጥልቅ ምርምር አካሂደዋል። ታሪካዊና የአፍሪካ ተምሣሌት አገር የሆነችው ኢትዮጵያ ከገጠማት አዙሪት ለመውጣት የጀመረችውን የሽግግር ፍትሕ አማራጭ ሂደቱን መጀመሯን አድንቀዋል። የሽግግር ፍትሕ መልከ ብዙ ግጭትና ግፎችን ላሳለፉ ማኅበረሰቦች ትናንትን በይቅርታ የነገውን በተስፋ ለመሻገር አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን በማንሳት።
በቀድሞው የጋምቢያ ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜህ ዘመነ መንግሥት ለ22 ዓመታት የተፈጸሙ ግፎችን በሽግግር ፍትሕ ሂደት የፈቱት የዕውነት፣ ዕርቅና ካሳ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ፤ በሐርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ተባባሪ አባል እና በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ዴቪስ ምሩቁ ጋምቢያዊው ዶክተር ባባ ጋሌህ ጃሎው፤ የሽግግር ፍትሕ አስፈላጊነት በተለይም ኢትዮጵያን ለመሰሉ አገራት አጠያያቂ አይደለም ይላሉ።
ሁለቱ ምሁራን የየአገራቸው የሽግግር ፍትሕ ተሞክሮ ለኢትዮጵያ የተሻለ ልምድ እንደሚሰጥ ያምናሉ። ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ፣ ባርነት እና ቅኝ ግዛት የጭቆና ሥርዓት ነጻ ስትወጣ ሥርዓቱ በጥቆሮች ላይ የፈጸመውን ግፍ፣ በማኅበራዊ ኢኮኖሚ መገለልና ብዝበዛ መልክ ለማስያዝ ሽግግር ፍትሕ ሂደት ተግብራለች።
ፕሮፌሰር ሙሪቲ እንደሚሉት፤ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ በጥቁሮች ላይ የተፈጸሙ በደሎችን በሽግግር ፍትሕ ሂደት መልክ ለመስጠት ብሎም ሕዝባዊ አብሮነት እንዲቀጥል በሊቀ-ጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ መሪነት የዕውነትና ዕርቀ ሠላም ኮሚሽን መቋቋሙን ያስታውሳሉ። እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ከአፈጻጸም ጋር የተያያዙ ክፍተቶች ቢኖሩበትም አካታችና የአገሪቱን ቀጣይ ጉዞ ለመቀየስ መሰረት የጣለ ነበር።
በተመሳሳይ በጋምቢያ አምባገነን መንግሥት የተፈጸሙ በደሎችን መልክ ለማስያዝ የተቋቋመው የዕውነት፣ ዕርቀ ሠላምና ካሳ ኮሚሽን ዜጎች ዕውነቱን እንዲረዱ፣ በዳዮች እንዲጠየቁና ተበዳዮች እንዲካሱ የሚያስችል ሰነድ ለአገሪቷ መንግሥት ማቅረቡን ዶክተር ባባ ጋሌህ ይገልጻሉ።
ምሁራኑ ኢትዮጵያ ለማድረግ ያሰበችው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ከአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ፍትሕ ፖለሲ እና የአገራትን ልምድ የቀመረ፣ አካታች፣ ተበዳዮችን የሚክስና አገርና ሕዝብን ወደፊት በሚያሻግር አግባብ እንዲፈጸም በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል።
ስለዚህ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ትግበራ ዘላቂ ሠላም ያለው ነገ ለመገንባት ለልማት የተነሳ፤ ከቅራኔ የራቀ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ተስፋ ይሰጣል። ለትግበራው ውጤታማነት ደግሞ ግለሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ ልሂቃን እና ተቋማት አገራዊ ግዴታቸውን ሊወጡ ግድ ይላል።
ትግበራው በፖሊሲው ላይ እንደተመላከተው የሠብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ያከበረ፣ ተጎጂን ማዕከል ያደረገ እና የፖሊሲውን መርሆዎች ያከበረ መሆኑን በመከታተልና በመደገፍ፤ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላምና ልማት እንዲያመጣና ዜጎች ነገን በተስፋ እንዲጠብቁና በአገራቸው ላይ ብሩህ ተስፋ እንዲኖራቸው በተሟላ መልኩ መተግበር አለበት። ለዚህም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍና ትብብር ወሳኝ ነው። የሽግግር ሂደቱን ምሉዕ ለማድረግ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ትልቁ ቁምነገር እንደሆነ በምሁራን ይነሳል።