ቀጥታ፡

የዜጎች ግልጋሎት ዝማኔ

በአየለ ያረጋል (ኢዜአ)


       ቅምሻ…

በአንድ ወቅት አንድ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባል “ለመሆኑ መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር የሚለዋወጥ ሲቪል ሰርቪስ ይዘን የምንቀጥለው እስከመቼ ይሆን? ሲሉ ላነሱት ቁጭት አዘል ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) “በጣም ትክክለኛና የምጋራው ሃሳብ ነው” ሲሉ ነው ምልከታቸውን እና የመንግሥታቸውን መሻት ያስረዱት። ለመሆኑ ሲቪል ሰርቪሱና አገረ-መንግሥቱ ምንና ምን ናቸው? 

 ፅንሰ ሃሳባዊ ዳራ
አገረ-መንግሥት በሥርዓት ይበጃል፤ መንግሥትም በተዋቀረበት ምሰሶዎች ይቆማል። በመንግሥት መዋቅር  ውስጥ በሙያቸው ተወዳድረው ለመንግሥት መከታ የሆኑ ባለሙያዎች አሉ። መዝገበ ቃላቱም ሆነ የመስኩ ምሁራን ይህን የመንግሥት ግልጋሎት ሥርዓት ‘ሲቪል ሰርቪስ’ ይሉታል። ‘ሲቪል ሰርቫንት’ የሚለው ቃል ደግሞ “ባለሙያ የመንግሥት ሠራተኛ” ተብሎ ይተረጎማል። የአገልጋይ ሙያተኞች ሲባል “በሙያ  ብቃቱና  በንጹህ ኅሊናው ለዜጎች መንግሥታዊ አገልግሎቶችን የሚሰጥ በብቃትና ችሎታው ብቻ ተመርጦ የሚቀጠረው ሠራተኛ ነው” ሲሉ ይፈትቱታል።

የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ”የመንግሥት  ሠራተኛ” ማለት በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ  ቤት  ውስጥ በቋሚነት ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው ነው። ሆኖም ሚኒስትር ዴኤታዎችን፣ ዋና እና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮችን፣ በተመሣሣይ ደረጃና ከዚያ በላይ የሆኑ የመንግሥት ተሿሚዎችን አይጨምርም ይላል። እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላትን፤ የፍርድ ቤት ዳኞችንና ዐቃቢያነ ሕግን፤ የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወይም በመከላከያና በፖሊስ ደንብ የሚተዳደሩ ሠራተኞችን አያካትትም። 

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ፍኖተ ካርታ የዜጎች አገልግሎት (civil Service) እና የሕዝብ አገልግሎት (Public Service) አሰጣጥ ልዩነትና ተደጋጋፊነትን ያወሳል። በዚህም የዜጎች አገልግሎት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በዜጋ ባለሙያ ሠራተኞች ለዜጎች ብቻ የሚሰጥ አገልግሎት ነው። የሕዝብ አገልግሎት ደግሞ በአገሪቱ ለሚኖሩ ሁሉ በዜጋና በውጭ ባለሙያ ሠራተኞች በተቋማት የሚሰጥ አገልግሎት እንደሆነ ያብራራል። የመንግሥት ዋነኛ ተግባርና ኃላፊነት የዜጎችን ሰብዓዊ ልማት በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚያስችል አገልግሎት መስጠት ነው።

የመንግሥት አገልግሎት ተቋማዊ ዳራ

ሲቪል ሰርቪስ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ የዋለው በእንግሊዝ የሕንድ አስተዳደር ነው። ይህም የምስራቅ ሕንድ ኩባንያ ኮሌጅ የድርጅቱን አስተዳዳሪዎች ለመገምገምና ለማሰልጠን ያለመ እንደነበር ታሪክ ይናገራል። የዘመናዊ ሲቪል ሰርቪስ ጅማሮ ደግሞ በ17ኛው፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓና በአሜሪካ ከነበረው የአገረ-መንግሥትና የብሔረ-መንግሥት ግንባታ ጋር ይያያዛል። አንዳንዶች ዘመናዊ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ማቆጥቆጥን ከዘውዳዊ ሥርዓተ መንግሥታት መንኮታኮትና ከብሔረ-መንግሥት ዕድገት ጋር ያቆራኙታል።

የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት በጥንት ዘመን ሲቪል አገልጋዮች የንጉሣዊያን ቤተሰብ የዘውዳዊ ሥርዓት አገልጋዮች  አካል ነበሩ። ዘውዳዊ ሥርዓት ሲከስም በሚኒስትሮችና በሌሎች ባለሥልጣናት መልካም ፈቃድ የሚመረጡ ሰዎች ሆኑ። ይህ አሰራር ከሙስና፣ ከፖለቲካ ጥገኝነትና ከደመወዝ ጋር ተያይዞ በደረሰበት ተቃውሞ በሂደት ቦርድ መቋቋምን ጨምሮ የአሰራር ማሻሻያዎች መደረግ ጀመሩ። በሂደትም ገለልተኛ አሰራር ዘርግተው የሲቪል ሰርቪሱን የሰው ኃይል የሚያስተዳድሩ የሲቨል ሰርቪስ ኮሚሽኖች በየአገራቱ መቋቋም ቀጠሉ። የሠራተኞች ምልመላ ከትምህርት ሥርዓት ጋር ተጣመረ፤ ምደባው በተቀመጠው መስፈርት መሰረት በውድድር እንዲሆን ተደረገ።  

የዜጎች አገልግሎት (ሲቪል ሰርቪስ) ሥርዓት አስፈላጊነት


የሥነ-መንግሥት ምሁራን ‘መንግሥት’ የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ የአንድ ሕዝብ ደህንነት፣ ግዛታዊ አንድነትና ምጣኔ ሃብታዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ በሕዝብ፣ ለሕዝብ የተደራጀ ሕጋዊ ሥልጣን ያለው አካል ያደርጉታል። በአጭሩ ‘ሕዝብ ለመምራት በሕዝብ የቆመ ተቋም’ ማለት ነው። እናም ይህ በሕዝብ የቆመ ተቋም የፖለቲካ ስራውን ገቢራዊ ማድረጊያ፣ የግለሰብና የቡድኖች ፍላጎት ማንፀባረቂያ፣ የመብትና ግዴታ መዳኛ ነውና ውስብስብ አሰራሮችን፣ ሂደቶችን፣ ግንኙነቶችንና ተቋማትን ያዘለ ገፀ-ብዙ ሃሳብ የያዘ አስተዳደር ሥርዓት ይዘረጋል።

ሕዝቡ መሠረታዊ  ፍላጎቶች አሉት፤ ለፍላጎቱ ስኬት የዜጎች ሰብዓዊ ልማትን ይሻል። ሰብዓዊ ልማት ደግሞ አካላዊና አካባቢያዊ ጤንነትን፣ ዕውቀትን፣ ክህሎትን፣ የእሴቶች እምርታን፣ ቁሳዊና የተፈጥሮ ሀብቱን የማስተዳደርና የመጠቀም እንዲሁም በሰላም፣ በፍትሕና በእኩልነት ተጋግዞ የመኖር አቅምን ማበልፀግን ያካትታል። አልኪሬ የተባሉ የዘርፉ ምሁር የአንድ አገር ሕዝብ ሕልውናም ሆነ የዕድገት ደረጃው የሚለካው ‘የሕዝብ፣ በሕዝብ፣ ለሕዝብ’ የሆነ የዜጎች ሰብዓዊ ልማት ልክ ነው ይላሉ። መንግሥትን ደግሞ ሕዝቡ ፈልጎና ፈቅዶ የሚያደራጀው የሰብዓዊ ልማት መዳረሻ መሳሪያ ያደርጉታል። 

የመንግሥት አስተዳደር፤ በማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተመርኩዞ በሚያወጣው ፖሊሲ ማኅበረሰቡን ማገልገልና ሁለንተናዊ ልማቱን ለማረጋገጥ መልካም አስተዳደር ያሻዋል። ዜጎች መንግሥትን በራሳቸው ሥልጣን ሰጥተው የሚሾሙት ሰብዓዊ ልማታቸውን በዘላቂነት እንዲያረጋገጥ ነው። 

የአንድ አገር ሥርዓተ መንግሥት ያለ ሲቪል ሰርቪስ ከንቱ ነው። የዘርፉ ምሁራንም  ሲቪል ሰርቪስ የሥርዓተ መንግሥቱ ነፀብራቅ ነው ይሉታል። የትኛውም አገር ያለሲቪል ሰርቪስ ዕድገቱን ከፍ ማድረግ አይቻለውም። የመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ገቢራዊ የሚደረጉት ብርቱና ታታሪ ሲቪል ሰርቪስ ሲገነባ ነው። የመንግሥት አገልግሎት ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ለተገልጋዩ ሕዝብ የሚደርሰው በሕግ አስፈጻሚው አካል በኩል ነው።  

የሕግ አስፈጻሚው አካል  አደረጃጀት  እንደየፖለቲካ ሥርዓቱ የሚለያይ ሆኖ የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን አቅጣጫ ከወቅታዊ  የፖለቲካ  አስተሳሰብ አንጻር የሚወስንና አተገባበሩን የሚከታተል የፖለቲካ ጉዳዮች አስፈጻሚ እና  የፖለቲካ  አቅጣጫውን ተከትሎ  የአገልግሎት  አሰጣጥ  ሂደቱን በተገቢው የሀብት ግብዓት የሚያሳልጥ የአስተዳደራዊ  ሥራዎች አስፈጻሚ ተብለው በሚታወቁ የሥራ ክፍሎች የተዋቀረ ነው። የሥራ  ክፍሎቹም  የፖለቲካ  ሹመኞችን ጨምሮ በበርካታ የሕዝብ አስተዳደር በየደረጃው ያሉትን የመንግሥት የሥራ  ኃላፊዎችና  ሠራተኞችን የሚያካትት ነው። ሲቪል ሰርቪስ መንግሥት ፖሊሲውን፣ ስትራቴጂውን እና ፕሮግራሙን ለመንደፍ፣ ለማዘጋጀት በአጠቃላይ የስራ ዑደት ለማስቀጠል ብሎም ገቢራዊ የማድረጊያ መሳሪያው ነው። ውጤታማ የመንግሥትን አስተዳደርና ልማት አቅጣጫን ይወስናል። 

በአገረ-መንግሥት ግንባታው የሲቪል ሰርቪሱ ሚና የማይተካ ነው። ማዕከላዊ መንግሥት በየደረጃው ባለው አስተዳደር ወጥነት ያለው ሥርዓት ለማንበርና የኃይል ምንጭን ለመቆጣጠር ረድቷል። እያደገ የመጣውም የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያዎች ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን እንደየአገሩ ነባራዊ እውነታ  አጣጥሞ ለመቀመር አስችሏል።

ሺያቮ ካምፖ እና ሱንዳራም የተባሉ ምሁራን ስለ ቪሲል ሰርቪስ አስፈላጊነት ሲጠቅሱ ቀዳሚ ፋይዳው መልካም አስተዳደርን ማስፈን ነው። ለዚህ ደግሞ የሰለጠነ፣ ታታሪና ብቁ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባር የተላበሰ ሙያተኛ ያስፈልጋል። ሁለተኛው ደግሞ ምርትና አገልግሎት በጥራትና በብዛት ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ በክህሎት የሚመራ ሠራተኛ ማስፈለጉ ነው። ሦስተኛው ለምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ በፖለቲካ ይሁንታ የሚወጡ ፖሊሲዎችን ለማስፈጸም የመንግሥት ሠራተኛ የግድ ይላል። መንግሥት ወጭና ገቢን ለማስተዳደርና  ሀብት  ለማመንጨት የዘርፉ ሠራተኛ ያስፈልጋል። ሲቪል ሰርቪስ ለተቋማዊ ልማትም ወሳኝ ነው።

ሲቪል ሰርቪስ ለዘላቂ ልማት ለመልካም አስተዳደር የማይተካ ሚና አለው። በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት ገለልተኛ የአስተዳደር መዋቅር የሚሸከመው ሲቪል ሰርቪስ በመሆኑ የዴሞክራሲ ሁነኛ አካል ይሰኛል። በዚህ ሚናው አገራት ሲቪል ሰርቪስ ከፍ ያለ የሙያና የሥነ ምግባር ደረጃዎች ሊኖረው ይገባል ሲሉ ይመክራሉ። ሲቪል ሰርቪሱ ፖሊሲውን፣ ሕጎችን፣ የአሰራር ሂደቶችን፣ ሥርዓቶችንና ድርጅታዊ አወቃቀርን ያካትታል። ሲቪል ሰርቫንቱ በመንግሥት ተቋማት አስተዳደራዊ መሳሪያዎችን የሚያንቀሳቅስ፣ መንግሥታዊ ውሳኔዎችን የሚያስፈፅም ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደር መምህር የነበሩት ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ ሲቪል ሰርቪስ የሙያተኞች ማህደር ነው፤ የሥርዓተ መንግሥቱ ምሰሶ በማለት ይገልጹታል። ሲቪል ሰርቪሱ በሕግ ምንጭነት፣ በሕግ አስፈፃሚነት ያገለግላል። የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚሳለጠው በመንግሥት ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥ ነው። በጥቅሉ ሲቪል ሰርቪስ የዘላቂ መንግሥታዊ አስተዳደር ቀኝ ክንድ ይሰኛል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ከሠራተኞች፣ ከአማካሪዎች ጀምሮ የፕሮግራምና የፖሊሲ አስፈጻሚዎች እንዲሁም የዕለት ከዕለት ተግባራት ከዋኞችኝ ያጠቃልላል ይላሉ።

ሲቪል ሰርቪሱ በምን መልክ መደራጀት አለበት?

ዓለም የሄደበትና ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የገነባበት መንገድ ዓለም አቀፋዊ እሳቤን የያዘ ነው። ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የሚገነባው አቅምን፣ ችሎታን፣ ቁርጠኝነትን እና ለሕዝብ ተቆርቋሪነትን መሠረት አድርጐ  ነው። ሲቪል ሰርቫንቱ በችሎታው  ተወዳድሮ  እንዲመደብ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል። አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደወትሮው አገልግሎታቸውን መቀጠል እንጂ የምርጫ ውጤትን ተከትሎ በሚመጡ የፖለቲካ አለመግባባቶች መታወክ የለባቸውም። በብዙ አገራትም በችሎታና በልምድ ሥርዓት በፈተና ይቀጠራሉ።

የአንድ መንግሥት ሁለንተናዊ ሥራ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አሠራር ገለልተኛ ሆኖ ብቃት ባለው የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓት ታግዞ ሕዝብ ማገልገል ይጠበቅበታል። በዘርፉ ምሁራን ብያኔም በመንግሥት  አገልግሎት  ሥርዓት  የተሰማራ የመንግሥት ሠራተኛ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አሠራር ገለልተኛ መሆን መሠረታዊ ቅድመ-ሁኔታ ሆኖ ተቀምጧል። የሠራተኛው ገለልተኝነት የመንግሥት ተቋም ዴሞክራሲያዊ ቅቡልነት መሠረት ይሆናል።

የመንግሥት ሠራተኞች የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸውን መንግሥታት ለማገልገል የሚያስችል ዝግጁነትና ብቃት ሊኖራቸው ይገባል። በሕዝብ የተመረጠው መንግሥት ያወጣቸውን ፖሊሲዎች ሳይሸራርፉ በታማኝነትና በቅንነት የመተግበር፤ ከፖለቲካ እምነትና ፕሮግራም ባሻገር ያሉ ሙያዊ ምክሮችንና አስተያየቶችን የማቅረብና እንደአስፈላጊነቱም በምክንያት መሞገትም አለባቸው። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ቀድሞ ከነበረው መንግሥት የወረሰውን የካበቱ ፈርጀ ብዙ ወረቶችን ቀጥሎ ለሚመጣው የመንግሥት አስተዳደር ማውረስ አለበት። በየትኛውም ሁኔታ መንግሥት ሲለወጥ ሙያዊ ብቃትን መሰረት  ያደረገ  ሲቪል  ሰርቪስ ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ የመንግሥትን ግቦች የሚያስፈጽም ፋይዳ  አለው። “ፖለቲከኞች ይቀየራሉ፤ አስተዳደሩ (ሲቪል ሰርቪሱ) ግን ይዘልቃል” ይሰኛል። ሙያውን የጠበቀና ገለልተኛ ሲቪል ሰርቪስ መንግሥት ቢለወጥም ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት ሳያዛባ ይቀጥላል።

ብቁ በሆነ የሲቪል ሰርቪስ ማዕቀፍ የሚመራ ተቋም ስራውን በትክክል ቆጥሮ መከወን ይችላል። ምሁራኑ በጥቅል ሲቪል ሰራተኞች የፖለቲከኞችን ውሳኔና ኃላፊነቶች ይከውናሉ። የሕዝብ አስተዳደር ተግባራትን የሚከውነው የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓቱ ነው።

የሲቪል ሰርቪስ ጥቅሞችን በቀላሉ ለማሳየት አሜሪካን ማንሳት ይቻላል። የአሜሪካ ልዕለ ኃያል ሆኖ የመቀጠል አንዱ ጉዳይ የተዋጣለት ሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት መንበሩ ነው። ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት በምታራምደው አሜሪካ የሪፐብሊካንም ሆነ የዴሞክራት ፓርቲዎች መንበረ መንግሥቱን ሲቆጣጠሩ ሲቪል ሰርቪሱ  በምርጫ  ሳይናወጥ፤  ሥርዓቱ ሳይወዘወዝ ይቀጥላል። ይህ የሆነው በአሜሪካ በ1880ዎቹ ገዳማ የተጀመረው የሲቪል ሰርቪስ ለውጥ ንቅናቄ ከፖለቲካ ጥገኝነት አላቆ ወጥ ሥርዓት በማንበሩ ነው። የሰው ኃይል አስተዳደሩ ከጥቅም መራሽ ወደ ችሎታ መራሽ ሠራተኛ ምልመላና ምደባ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ወደ ቴክኒካዊ ብቃት ማሸጋገር ችሏል። በዚህም የሲቪል ሰርቪሱ የሰው ኃይል ሙያውን የጠበቀ እንዲሆን፣ አዎንታዊ ሚናው አገራዊ ፋይዳ እንዲያበረክት አድርጎታል።

ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ እንደሚሉት ሲቪል ሰርቫንቱ በሳይንሳዊ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች መሰረት በችሎታው የሚጠበቅበትን መወጣት እንዲችል የተደራጀ ቴክኒካዊና ሙያዊ አቅም ሊኖረው ይገባል። የተቀጣሪ ሠራተኞች የሥራ ዕድገት በፖለቲካ ውግንና ሳይሆን ባሳዩት ትጋት፣ ቁርጠኝነት፣  ለሕዝብ ጥቅም ባላቸው ተቆርቋሪነት መለኪያዎች ተመዝነው መሆን አለበት። ሲቪል ሰርቫንቱ የሚመለመለው በብቃቱና በችሎታው እንጂ በፖለቲካ ዝንባሌው ወይም በአባልነት መሆን የለበትም። የአሸናፊውን የፖለቲካ ኃይል ፖሊሲና ፕሮግራም አስፈጻሚ ቢሆንም ደጋፊና ነቃፊ መሆን አይገባውም።

አገልግሎት  ሰጪ ተቋማትን  በብቁ ባለሙያዎች መሙላት ይገባል። አንድ ባለሙያ በተመደበበት ቦታ ሆኖ የሚነቅፈውን የፖለቲካ ፕሮግራም እያስፈፀመ ከሆነና ፖለቲካውን ለመጉዳት ስራውን የሚበድል ከሆነ ሕዝብን እየጐዳና እያማረረ ስለሚሄድ ይህ ባህል መታከም አለበት። የአገልግሎት ቃል ኪዳንን መብላት ነው። የሲቪል ሰርቪስ ተቋም በየጊዜው እየተገነባ የሚሄድ ነው። 

በሌላ በኩል  ሲቪል  ሰርቪሱ የአሸናፊው የፖለቲካ ፓርቲ ፖሊሲና ፕሮግራም ማስፈጸም አለበት። የፖለቲካ አባልነትን  ከሲቪል ሰርቪሱ ማስፈጸም ጋር አቀላቅሎ ማየት አይገባም። የመንግሥት ሠራተኛ የሆነ የፓርቲ አባል  የፓርቲውን ፕሮግራም መሥሪያ ቤት የመንግሥትን ሃብትና ጊዜ ተጠቅሞ መፈጸም አይችልም።

ዶክተር ፋንታ እንዳሉት የአገልግሎት አሠጣጥ ደካማነት ሕዝብን ለአመፅ ይገፋፋል። ለሀገራዊ ለውጡ  ምክንያት የሆነው አመፅ የፖለቲካ ጥያቄ ብቻ አልነበረም። ዜጎች የሚፈልጉትን ጥራት ያለው አገልግሎት  የማግኘት ችግርም ጭምር ነው። የዜጋው ጥረት ፍሬ የሚያፈራው ሲቪል ሰርቪሱ ሲስተካከል ነው። ካለመልካም ሲቪል ሰርቪስ አገር አያድግም።

የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት አመሰራረት ሂደት በኢትዮጵያ


ኢትዮጵያ በሥርዓተ መንግሥት ምስረታ ቀደምት ብትሆንም ቅሉ ዘመናዊ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ጅማሮና በመተግበር ረገድ ከአውሮፓና ከሌሎች አገራት አንጻር ስትታይ ዘግይታ ነው ወደ ሥርዓቱ የገባችው። ሀገረ መንግሥቷን ስትመራ የቆየችው በባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት ነው። እንደ ሪቻርድ ፓንክረስት ጥናት የዘመናዊ ኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ የጀመረው በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1900 አካባቢ ነው። በወቅቱ የመንግሥትን ስራዎች በቀልጣፋ አደረጃጀትና ትዕዛዝ ለማስፈጸም ዘጠኝ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተቋቋሙ። እነሱም የሥራ፣ የፍትሕ፣ የግብርና እና ኢንዱስትሪ፣ የአገር ግዛት፣ የግቢ፣ የንግድና ውጭ ጉዳይ፣ የገንዘብ፣ የጦርና የጽህፈት ሚኒስቴሮች ነበሩ።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመናዊት ኢትዮጵያን የመገንባት ራዕይ እውን ለማድረግ  የአገር ደኅንነትን፣ የግብር አሰባሰብን እና ዘመናዊ ጦሩን ለመደገፍ ያቋቋሙት ካቢኔ የኢትዮጵያ የመንግሥት አስተዳደር እና የዘመናዊ አገልግሎት ሥርዓትም ጅማሬ ተደርጎ ይወሰዳል። ይህም የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደትን ለማስቀጠል ያበረከተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር። ከዚህ ቀደም ሲል የነበሩት ዘውዳዊ ሥርዓቶች ምንም እንኳ ሥልጣናቸውን ቢያስጠብቁም ምንም አይነት የአስተዳደር ማዕቀፍ አልዘረጉም ነበር። ለመንግሥት አስተዳደር ሥርዓቱ ብቃት-ተኮር መረጣና ምልመላ፣ የሥራ ስምሪት የአሠራር ሥርዓት ያልተዘረጋለት በመሆኑ ከንጉሣዊ ወገን መወለድ፣ ትውውቅ፣ ቅርርብ፣ ለንጉሣዊ ሥርዓቱ ታማኝነት፣ ዝምድና፣ ጋብቻና አምቻ የመሳሰሉት ዋነኛ የመመዘኛ መስፈርቶች ሆነው ቆይተዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ጥናት ኢትዮጵያ ከትምህርት በፊት ያቋቋመችው የመንግሥት ተቋማትን ነው። በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ በመሳፍንትና በቤተ ክህነት ሊቃውንት መተዳደር የግድ ብሏቸዋል። ዘመናዊ አስተዳደሩም በግለሰብ መልካም ፈቃድ አስተዳደርና ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ነበር። በተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጥ ያልተሟላ አወቃቀር፣ ብቁና በቂ ያልሆነ አገልግሎት፣ ሙስና  እና  የልዑላን ጣልቃ ገብነት ችግሮች ነበሩበት። በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን ሚኒስትሮች በጦርነት ጊዜ በሚያንቀሳቅሱት ጦር ብዛትና ታማኝነታቸው ተመዝኖ የሚሾሙና አለደመወዝ ያገለግሉ ስለነበር የሲቪል ሰርቫንቱ ቁጥር እዚህ ግባ የማይባል ከመሆኑም ባሻገር በዋናነት በሕግ ማስከበር ሥራ ላይ ያተኮረ ነበር።

ሄኖክ ስዩም አሰፋ የተባሉ ተመራማሪ በ2017 ዓ.ም “Advance Research and Development” በተሰኘ ዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔት ባሳተሙት ጥናት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በዘመናዊ አስተዳደር ሥርዓት ዝርጋታ ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል። በዘውዳዊው ሥርዓት ማክተሚያ ላይ ወጥነት ባለው ሕግ የሚመራ፣ ብቃት ያለው  ውጤታማ የሆነ የመንግሥት አስተዳደር ማደራጀትን ታሳቢ ያደረጉ ተቋማትን እንደገና የመመሥረትና የማዋቀር ተከታታይ ተግባራትን አከናውነዋል። የአገር ማዕከላዊነት እና ዘመናዊነት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው አፄ ኃይለሥላሴ ተከታታይ የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት አሰራሩ ተቋማዊ እንዲሆን ማድረጋቸው እንደሆነ የታሪክ ምሁራን ጽፈዋል። የሠራተኛ ማሰልጠኛ፣ ማማከርና ጥናት ላይ ትኩረቱን ያደረገ የዘውዳዊ  ሕዝብ አስተዳደር ኢንስቲትዩት በ1944 ዓ.ም መቋቋሙ በአብነት ይነሳል። እ.ኤ.አ 1962 የመንግሥት አገልግሎት መመሪያ እንዲሁም በ1972 የሠራተኛ ሥራ መደብ ዝርዝርና እርከን ደንብ ወጥቷል።

በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መበራከትና የሠራተኛው ብዛት በዓይነትና በመጠን በመጨመሩ፣ እንዲሁም የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዓለም አቀፍ ግንኙነት በመስፋፋቱ፣ የሠራተኛውን አስተዳደር ዘመናዊ መልክ ማስያዝ የግድ ብሎ እንደነበር አቶ ተፈራ ኃይለሥላሴ በኢትዮጵያ  ጥናት  መድረክ  ባሳተሙት ጥናት  አመላክተዋል። በተለይም በቅኝ ግዛት አስተዳደር ስር የቆዩ አገራት  የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደርን በኃላፊነት የሚመሩ መሥሪያ ቤቶችና ሠራተኞችን የሚያስተዳድሩባቸው ደንቦች ሲኖሯቸው፣ በነፃነት የኖረችው ኢትዮጵያ ያለደንብ ሠራተኞቿን ማስተዳደሯን የአፄ  ኃይለሥላሴ መንግሥት የሚቀበለው እውነታ አልነበረም። መንግሥት ይህን ክፍተት ለመሸፈን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች እና በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች አስጠንቶ በ1954 ዓ.ም የመንግሥት ሠራተኞች ማስተዳደሪያ ጠቅላይ መሥሪያ ቤት ስለማቋቋሙም ይገልጻሉ። በመቀጠልም የሠራተኞች ማስተዳደሪያ ዝርዝር ድንጋጌዎችን የያዘ ደንብ በ1955 ዓ.ም ወጥቷል። የመንግሥት ሠራተኞች ማስተዳደሪያ ደንብ መውጣቱ፣ በተለይ የሠራተኛ ቅጥርን፣ ዕድገትን፣ ደመወዝን፣ ዝውውርን፣ ልዩ ልዩ ፈቃድን፣ ቅጣትን፣ ሥልጠናን፣ ወዘተ በመሳሰሉት የአሰራር ሥርዓቶች ላይ ሥር ነቀል ለውጥ አምጥቷል። ሠራተኛውም ተግባሩንና ኃላፊነቱን፣ እንዲሁም መብትና ግዴታውን በመረዳት ሥራውን የሚያከናውንበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል።

በ1954 ዓ.ም የተጀመረው በሕግና ደንብ የሚመራ የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓት በመንግሥት የአገልግሎት ሥርዓቱ ታሪክ ውስጥ ብቃትን መሠረት ያደረገ የሠራተኞች ምልመላ፣ መረጣና ስምሪት ሥርዓት ማቆጥቆጥ የጀመረበት ጊዜ ነበር ማለት ያስችላል። ደንቦቹን ተከትለው ተግባራዊ የሆኑት አሠራሮች በዘመኑ ከበለፀጉት ሀገሮች ጋር ሲነጻጸሩ የአስተዳደር ሥርዓቱን ዘመናዊ ከሚባሉት አገሮች ተርታ ማስቀመጥ የቻሉ ነበሩ። በእነዚህ ደንቦች አማካይነት የመንግሥት ሠራተኞች ምልመላ፣ መረጣ፣ የሥልጠና አካሄድ፣ የሥራ አፈጻጸም ምዘና፣ የደመወዝ ጭማሪ ሥርዓት፣ የመንግሥት ሥራዎች የሚኖሯቸው እንደ ጥበቃና ጉልበት (ጥጉ)፣ እጅ ጥበብ (እጥ)፣ የፅህፈት ሥራ (ፅሂ)፣ አስተዳደር (አስ)፣ መለስተኛ ፕሮፌሽናል (መፕ) እና ፕሮፌሽናል ሣይንስ (ፕሣ) የመሳሰሉት ደረጃዎች እና የደመወዝ ስኬል ሥርዓት ተዘርግቷል። ይህ ወቅት የመንግሥት ሠራተኞች የዲሲፕሊን ሥርዓትና የአስተዳደር ፍርድ ቤት አሠራሮች የተቋቋሙበት፣ ዘመናዊና ወጥነት ያለው የሰው ሀብት አስተዳደር፣ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄድ የሠራተኞች ሥራ አፈጻጸም ምዘና፣ እና ሌሎች የመንግሥት አስተዳደር ሕጎችና አሠራሮች ተግባራዊ የሆኑበት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የመንግሥት ሠራተኞች ማስተዳደሪያ ጠቅላይ መሥሪያ ቤት የተቋቋመበት ዓላማ የመንግሥት አስተዳደር ሠራተኞች በአንድ ወጥ ደንብና የአሰራር (የሠራተኛ ቅጥርና  ስንብት፣ ደመወዝ፣ የደረጃ ምደባና ዕድገት፣ ፈቃድ፣ የሥራ ሰዓት፣ ወዘተ) የአሰራር ሥርዓት (ዲሲፕሊን) ማስከበሪያ ሥርዓትን፣ የሠራተኛ ማሰልጠኛ ደንቦችን እና መመሪያዎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን እያጠና ለመንግሥት አቅርቦ ማስፈቀድና አፈጻጸማቸውንም መከታተል  ነበር። መሥሪያ ቤቱ በንጉሡ በሚሾሙ የበላይ ኮሚሽነር እና በሁለት ኮሚሽነሮች የሚመራ ሆኖ ተጠሪነቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነበር። የመሥሪያ ቤቱ ማንኛውም ጉዳይ የሚወሰነው በኮሚሽነሮች ጉባዔ ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መራሹ መንግሥት ደግሞ ከ1984 ዓ.ም  እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓት በቀደሙት ሥርዓቶች የነበሩትን የሰው ሀብት አስተዳደር ደንቦች በማሻሻልና ሌሎችም የአሠራር ዘዴዎችን በመተግበር ሥርዓቱን ለማዘመን ጥረት አድርጓል። ሥርዓቱ በተነጻጻሪነት ካስተናገዳቸው መሠረታዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ጋር የተጣጣመ የአገልግሎት ሥርዓት ለመዘርጋት  የሚያስችል  የለውጥና የማሻሻያ መርሃግብር ነድፎ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል። እንደቀደሙት መንግሥታት ሁሉ የመንግሥት አስተዳደሩንም ሆነ የአገልግሎት ሥርዓቱን የኃላፊነትና የሥራ መደቦች ለፓርቲው ፍጹም ታማኝ በሆኑ ሠራተኞች የሚሞላበትን አሠራር ቀጥሎበት ቆይቷል። ሥርዓቱም በፓርቲው ቀጥታ ጣልቃ ገብነት የሚመራበትን አቅጣጫ ለማጠናከርም አበክሮ  ሠርቷል።

ታሪካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ እውነታዎች በሲቪል ሰርቪሱ ሙያዊ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ አሳድረውበታል። ፖለቲካው በሰው ኃይል አስተዳደርና ውሳኔዎች ላይ ቁልፍ ሚና ይጫወት ነበር። በዚህም ሲቪል ሰርቪሱ በከፍተኛ ሁኔታ የፖለቲካ ተቋም ሆኗል ሲል የአቶ ተፈራ ኃይለሥላሴ ጥናት ይደመድማል። የሰራተኛ ምልመላ ሂደቶች በሕግና ሥርዓት አለመመራታቸው፣ አድሎ፣ ጉቦ፣ ፖለቲካዊ ታማኝነት የሲቪል ሰርቪሱን ሙያ ሲበድል ኖረዋል፤ በተለይም በመካከለኛና ከፍተኛው አመራር አካባቢ። በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር  በ1962 የተቋቋመው የማዕከላዊ የሰው ኃብት ኤጀንሲ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ምስረታ መሰረት ሆኗል። ዓላማውም ብቃትን መሰረት ያደረገ ብቁ፣ ውጤታማ፣ ቋሚ ሲቪል ሰርቪስ መዘርጋት ነበር። በእርግጥ ቢሮክራሲውና አወቃቀሩ የአውሮፓ ተዕጽኖ ነበረበት። በግሉ ዘርፍ ያለው የገበያ ውድድር እና የሲቪል ሰርቫንቱ አነስተኛ ክፍያ በመንግሥት አገልግሎት ተቋማት ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች በየሙያ መስኩ እንዳይቆዩ ማድረጋቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ።


የአገልጋይነት ተልዕኮ እና ሥነ-ምግባር


ለኢትዮጵያዊያን የጋራ በሆነችው ኢትዮጵያ ሁሉም በእኩልነትና በፍትሃዊነት ሠርተው የሚለወጡባት አገር ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ነው። አገልግሎት የሁላችንም ነው፤ በአንድ ተቋም ያለ አገልጋይ በሌላው ተቋም ተገልጋይ ነው። የሲቪል ሲርቪስ ተልዕኮ ከከሸፈ ራሱ ሲቪል ሰርቫንቱ ተጎጂ ይሆናል። የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓት ትኩረት ሰጥቶ ሊያጠናክራቸውና ሊሰራባቸው ከሚገቡ አበይት ዕሴቶች መካከል ዜጋና ውጤት ተኮር ሰብዓዊ ብልፅግና፣ በራስ የመተማመንና ራስን የመምራት ብቃትን ማረጋገጥ፣ ፈጠራና ሰላማዊነት (ለሰላም ዘብ መቆም) የሚሉ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሥነ-ምግባር ዕሴቶች በአራት ይከፈላሉ። እነሱም:- 
1.    ሥነ-ምግባራዊ  ምሉዕነት  (ሰብዓዊ  ታማኝነት እና ፍትሃዊነት)፤
2.    ዴሞክራሲያዊነት (ግልፅነት፣ተጠያቂነት፣ ሕጋዊነት  እና ተወካይነት)፤ 
3.    ሙያዊ  ብቃት (አገልግሎት፣ ጥራት፣ አመራር እና ፈጠራ) እና ፤
4.    ሰብዓዊ ዕሴት (መቻቻል፣ ርህራሄ፣ መልካም ምግባር፣ ድፍረት፡ ደግነት፣ እና ፍትሃዊነት) ናቸው።
እነዚህ ዕሴቶች  የመንግሥት ዘርፍ ሥነ-ምግባር በዕለት ተዕለት ሥራ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ የመንግሥት ሠራተኛው (ሲቪል ሰርቫንቱ) ሊላበሳቸውና አበክሮ ሊተገብራቸው ይገባል። የሥነ መግባር እሴቶች ሳይኖሩ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳለጥ፣ መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥና  የሕዝብ አመኔታን ማግኘት አይቻልም። 
የሰው ሀብት አስተዳደር ፍልስፍና በብቃትና ችሎታ “ምሉዕ ስብዕና” ያለውን ሰው የመንግሥት ሠራተኛ አድርጎ በማሰማራት የዜጎች አገልጋይ እንዲሆን ማድረግ ነው። በአንድ አገር የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ መልካም አስተዳደር የማስፈን ጉዳይ ችሎታ፣ ብቃት፣ ምሉዕ ሰብዕና እና ቁርጠኝነት ያላቸውን ሰዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ ወደ መንግሥት ዘርፍ ከማስገባት ወይም ካለማስገባት ጋር በቀጥታ ይያያዛል። “ምሉዕ ስብዕና” በመንግሥታዊ አገልግሎት ዘርፍ ከራስ በፊት አገርንና ሕዝብን ማስቀደምን፣ ታማኝነትን፣ የዓላማ ፅናትን፣ ዝቅ ብሎ ማገልገልንና በቃል መገኘትን ተላብሶ በአእምሮና በአካል ለሥራ ዝግጁ መሆንን የሚያስገነዝብ ገዥ ሃሳብ ነው። በመንግሥት ሥራ በመሪነትም ሆነ በሠራተኛነት የ”ምሉዕ ስብዕና” ባለቤት ሳይሆኑ በኃላፊነት ቦታዎች መቀመጥ እንደ ቀላል ስህተት የማይታለፍ ጥፋት ነው። የሀገራችን የአስተዳደር ሥርዓት ከዚህ ገዥ ባህርይ አንጻር ሲገመገም እያሽቆለቆለ የመጣ ማንነት ያለው መሆኑን በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።  

የኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂም ዋና ትኩረቱን ያደረገው ማገልገል ክብር የሆነበት ሥርዓት መገንባት ተገቢነት ላይ ነው። የመንግሥት ዘርፍ የሰው ሀብት ልማት የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች ዘርፉን የሚቀላቀሉት አገርንና ሕዝብን ማገልገል ሀገረ መንግሥትንና ሉዓላዊነትን የማስቀጠል ጉዳይ መሆኑን በውል መገንዘብ ያሻቸዋል። የመንግሥት ሠራተኞች ከመንግሥት ሥራ የሚያገኙት ጥቅም በገንዘብና በንብረት የሚለካ ሳይሆን ዜጎችን አክብሮ ከሚሰጥ የላቀ አገልግሎትና ከተገልጋይ እርካታ በሚመነጭ አንፀባራቂ ክብር የሚገለፅ ነው። ስለሆነም የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ አገርንና ሕዝብን ማገልገል ድርብ ክብር የሚያስገኝ መሆኑን ከሕፃንነት ጀምሮ በትምህርት ቤት በሚሰጡ ትምህርቶችና የሞራል አስተምህሮዎች ተደግፎ የሚሰርጽ ይሆናል።


የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ ችግሮች 


ጥናቶች እንደሚያስረዱት አፄ ኃይለሥላሴ በሕግና ሥርዓት የሚመራ፣ ብቃት ያለው ውጤታማ የሆነ የመንግሥት አስተዳደር ማደራጀትን ታሳቢ ያደረጉ ተቋማትን እንደገና የማቋቋምና የማዋቀር ተከታታይ ተግባራት  እንዲከናወኑ  ያደረጉት  በተቋማቱ አደረጃጀት የመሣፍንቱን አቅም ለመገደብና የንግሥናቸውን ማዕከላዊ ሥልጣን ለማጠናከር ነበር። የመንግሥት 
ሥራዎችን በሰው ኃይል በማስያዝ ረገድ ለፖለቲካ ታማኝነት የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት፤ በመመሪያዎች አወጣጥና አተገባበር ላይ የነበረው ቀጥተኛ የፖለቲካ ጣልቃገብነት የመመሪያዎቹን ውጤታማነት ጎድቶታል።  

በኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ (ኢሠፓ) ብቸኛና ግንባር ቀደም መሪነት የቆየው ወታደራዊው የደርግ  መንግሥትም ለሚከተለው የማርክሲስት-ሌኒኒስት ርዕዮተ-ዓለም ፍጹም ታማኝ የሆነ ሠራተኛ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱ ውስጥ በስፋት እንዲካተት፤ ፓርቲው ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት እንዲኖረው፣ በመንግሥት አስተዳደር እና በፓርቲው አሰራር መካከል ሊኖር የሚገባው መሠረታዊ ልዩነት እንዲደበዝዝ አድርጓል። ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ የደርግ ርዕዮተ-ዓለም ማራመጃ ሆኖ የቆየ በመሆኑም ነፃና ገለልተኛ አልነበረም። በጊዜው ቁልፍ የመንግሥት ውሳኔዎች የሚተላለፉባቸው የኃላፊነት ቦታዎች በፓርቲ አባላት እንዲያዙ ተደርጓል። ሥርዓቱ እንደቀደሙት ሁሉ የተማከለ አስተዳደርን በመከተሉ፣ በርካታ ነባር ደንቦች በደብዳቤ በመሻራቸው፣ አምራች ያልሆነ የሰው ኃይል በመሰባሰቡ፣ ለብዝሃነት ዋጋ ባለመስጠቱ እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ባለማካተቱ የመንግሥት ሠራተኞች ክብር በኢኮኖሚም ሆነ በማኅበራዊ ይዞታው እያሽቆለቆለ መምጣቱንም  አቶ ተፈራ ያስረዳሉ።
ከወታደራዊው ደርግ ቀጥሎ አገር የማስተዳደር ሥልጣን የተረከበው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መራሹ መንግሥት የመድብለ ፖለቲካ ፓርቲ ሥርዓትን የተከተለ ነበር። “በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ” አስተሳሰብ እየተመራ ሀገሪቱን ያስተዳደረው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥትም እንደቀደሙት የመንግሥታት አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ለፖለቲካ ፓርቲው ፍጹም ታማኝ በሆኑ  ሰዎች በማሲያዝ  የፓርቲውን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት አስፍኗል። አንዳንድ ወገኖች መንግሥት ለዘመናት የተንሰራፋውን የፓርቲና የመንግሥት ሥራዎች መደበላለቅ መለየት እንዳለበት ይገልጻሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ“መደመር” መጽሐፋቸው እንዳመለከቱት ገዥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለዋወጡ ቁጥር የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ተቋማትን ከመሠረታቸው አፍርሶ የመገንባት ልማድ የሀገራችንን የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ሁሌም ለጋ እና የቀጨጨ እንዲሆን አድርጎታል። በመንግሥት ፖለቲካ ሥራዎችና  በአስተዳደራዊ ተግባራት መካከል ሊኖር የሚገባው በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ የሥራ ግንኙነት ፈሩን ስቶ በሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ በተቀያየረ ቁጥር ሀገረ-መንግሥቱ የተዋቀረባቸው ተቋማት ፈርሰው ፍጹም እንደ አዲስ የሚገነቡበት፤ ያም ሆኖ ከማኅበረሰቡ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ባህሎች ዘላቂ ለውጥ ጋር በንቃት ለመጓዝ ራሳቸውን ማደስ የሚችሉ አልሆኑም።

በ2013 ዓ.ም የታተመው የመንግሥት አገልግሎት ፍኖተ ካርታ ባለፉት አሥርት ዓመታት በሀገራችን የመንግሥት አገልግሎት ሥርዓትን ለማጠናከርና የማስፈጸም አቅምን ለማጎልበት እንዲቻል የተለያዩ የማሻሻያ ፕሮግራሞች ቢነደፉም፤ ወቅቱ በሚፈልገው ልክ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን በመምራት የዜጎችን ፍላጎት የሚያረካ መንግሥታዊ መዋቅር እንዳልተገነባ ያትታል። የአገልግሎት ሥርዓቱን ለማሻሻል የተተገበሩ የለውጥ መሳሪያዎችም ለውጥ እንዳላመጡ ይልቁንም ተቋማት የሕዝብን ፍላጎት ከማርካት ይልቅ ለቅሬታ የዳረጉ፤ የመንግሥት ፖሊሲ አስፈጻሚ የሆነውን የመንግሥት ሠራተኛ የሕዝብ አገልጋይነት ስሜት ያሳጡ፤ ሕዝቡ ለሲቪል ሰርቫንቱ ያለው አመለካከት የተዛባ እንዲሆን ምክንያት መሆናቸውንም አመላክቷል። 

ሕዝብን ከመምራት ጋር በተያያዘ ኃላፊነት የተጣለበትን አንድ ተቋም ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ ተጽዕኖ ውጪ ማድረግ ፈጽሞ ባይቻልም፤ ከፖለቲካ ፓርቲ ቀጥተኛ ቁጥጥር የራቀ እንዲሆን ማድረግ እንደሚቻል ጥናቶች ያመለክታሉ። በመንግሥት የአስተዳደራዊ ሥራዎች ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነትና ባለሙያዎችን የማግለል አሰራር በዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ተቀባይነት የለውም። ካዩዚያ የተባለ የዘርፉ ምሁር የፖለቲካ ሥራዎችን ከመንግሥት አስተዳደራዊ ሥራዎች ለያይቶ ማየት ፈጽሞ ባይቻልም ሁለት የሚደጋገፉ የሕግ አስፈጻሚው የሥራ ክፍሎች እንጂ አንድ አይደሉም ይላሉ። አንዱ በሌላው አሰራር ውስጥ ዘልቆ በመግባት በሚወስንበት ጊዜ የፖለቲካና የመንግሥት አስተዳደራዊ ሥራዎች ሚዛናዊ መደጋገፍ ይዛነፋል። በዚህም የመንግሥት ውጤታማነት፣ አካታችነትና ተጠያቂነት ያለበት ተቋማዊ አሰራር መገለጫ የሆነው የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በሁሉም ገፅታው የተዛባ ይሆናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ“መደመር” መጽሐፋቸው “ሀገረ-መንግሥቱ በደቀቁ፣ ሙያዊ ብቃታቸው ዝቅተኛ በሆኑ፣ እንዲሁም ነፃና ገለልተኛ ባልሆኑ ተቋማት የተደራጀ ሆኗል” ይላሉ። በዚህም በርካታ ሰዎች ደረጃቸው ከፍተኛ በሆኑ የመንግሥት ሥራ መደቦች ላይ የፖለቲካ ምደባ ተደርጎላቸው ሥልጣንን ለግል ብልፅግና የሚያውሉ፣ በባለሥልጣናቱና በባለሀብቶች መካከልም የእንካ-በእንካ ግንኙነቶች በመንግሥት አገልግሎት መስኮች እንዲጎላ ሰበብ መሆኑን አመላክተዋል። 

ወርቁ ታደሰ ከሦስት ዓመት በፊት “የፐብሊክ ሰርቪስ ለውጥ በኢትዮጵያ ተግዳሮትና የአፈጻጸም ክፍተቶች” በሚል ርዕስ በዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔት ያሳተሙት ጥናት የለውጥ መሳሪያዎችን ተግባራዊነት እና ክፍተትን ዳሷል። የጥናቱ ግኝት የፐብሊክ ሰርቪሱ ማሻሻያ መርሃ ግብሮች ከሀገሪቷ የልማት ስትራቴጂ ጋር አብረው የማይራመዱ፣ የኢትዮጵያን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያላስገቡና ከሌሎች አገራት በቀጥታ የተቀዱ መሆናቸውን አመላክቷል። አተገባበራቸውም በፖለቲካዊ ግፊት በቀጥታ ከላይ ወደታች መውረዳቸው ውጤታቸው በወረቀት ትርክት ተንጠልጥሎ ከግባቸው መራቃቸውን በጥናቱ አሳይተዋል። ለውጡ ከፍተኛ የሠራተኛ ፍልሰት በማስከተሉ ተቋማት ልምድ ያላቸውን ሠራተኞች እንዲያጡና እንዲዳከሙ መደረጋቸውን እና ፖለቲካና ዘውግ ዘመም ሲቪል ሰርቪስ እንዲፈጠር ማድረጋቸው፤ በጥቅሉ የለውጥ ሥራዎቹ በሲቪል ሰርቪሱ መዋቅር አገልግሎት አሰጣጥ ተጨባጭ ለውጥ እንዳላመጡ ይደመድማሉ።

ተክላይ ተስፋይ እ.አ.አ በ2016 በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ ጥናታቸውን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ሥነ ምግባር ላይ አካሂደዋል። ጥናቱ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች የሥነ ምግባር እሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን አመላክቷል። ወጣቱ ትውልድ ኢ-ሥነ ምግባራዊና ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በአቋራጭ መክበርን ምርጫው ስለማድረጉ፣ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት በሥርዓተ ትምህርቱ ቢካተትም የወጣቱ የሥነ ምግባር ጥሰት እየተባባሰ ስለመሄዱም አንስቷል።
ባጫ ከበደ እና ሌሎች አጥኚዎች ባካሄዱት ጥናት የመንግሥትን አመኔታ ለማትረፍና የዜጎችን አገልግሎት እርካታ ለማሳደግ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። የመንግሥት ተቋማት የማስፈጸም አቅም ማነስ፣ የምዕራቡ ዓለምና የአገር በቀል ሥርዓት አለመጣጣምና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች የዘርፉ ችግር እንዲባባስ ሰበብ መሆናቸውን ያነሳሉ። በጥቅሉ እነዚህና መሰል መንስኤዎች ሕዝብ በመንግሥትና በሕዝብ አስተዳደር ተቋማት ላይ እምነት እንዲያጣ አድርገው እ.አ.አ ከ2014 እስከ 2018 በሕዝባዊ ማዕበል መመታቱን ይገልጻሉ።
አጥኚዎቹ እንደሚሉት በሰው ኃይል ረገድ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የተደረገው ተቋማዊና የፖለቲካ አስተዳደር ማሻሻያ በክልልና በፌዴራል የነበረውን የሰው ኃይል ሥራ አመራር ለውጦታል። የሰው ሀብት ምልመላ፣ አቅም ግንባታና ዕድገት ሙያ መር የፖለቲካ ጥገኝነት የተቀላቀለበት ነበር። ሲቪል ሰርቪሱ ከንጉሣዊውና ከአብዮቱ ዘመን የፋሽን ለውጥ አድርጓል። ፖለቲካና አቅም መር መመዘኛዎች ተደበላልቀዋል። አተገባበሩም ከላይ ወደታች መሆኑ ሲቪል ሰርቫንቱ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ እንዲሆን አስገድዶታል። 

የዘውዳዊው ሥርዓት ማዕከላዊ ሥልጣንን ለማጠናከር ታልሞ የተሠራ እንደነበረ መረጃዎች ያስረዳሉ። የመንግሥት ሥራዎችን በሰው ኃይል በማስያዝ ረገድ ለፖለቲካ ታማኝነት የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት፣ በመመሪያዎች አወጣጥና አተገባበር ላይ ፖለቲካው የነበረው ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የነፃና ገለልተኛ ሥርዓት ግንባታውን ውጤታማነት ተፈታትኖታል።ሥርዓቱ የራሱ ጥንካሬዎች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ችግሮችም ነበሩት። ለአብነትም የወጡትን ሕጎች ከሀገሪቱ ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር ፈትሾ አለማሻሻሉ፣ ሥራን አቅዶ የአፈጻጸሙን  ውጤት በአግባቡ አለመመዘኑ፣ በሀብት አጠቃቀሙ ብክነትን ተከላክሎ ውጤታማ አለመሆኑ፣ አገልግሎቱ የተማከለ አሠራርን መከተሉና ዜጋው ለአንድ አገልግሎት በርካታ ቢሮዎችን በማዳረስ እንዲንከራተት መንሥኤ መሆኑ ይጠቀሳሉ። የመንግሥት ሠራተኛውም ለግብር ከፋዩ ማኅበረሰብ የሚገባውን ክብር አለመስጠቱ፣ ሌብነትን አምርሮ የማይጸየፍ መሆኑና አልፎ ተርፎም በድርጊቱ ተጠርጣሪ ሆኖ መታየቱ ሠራተኛውም ሆነ ዘርፉ በደበዘዘ ክብር እንዲዘቅጥ አድርጎታል።

የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ችግሮች ሥር የሰደዱ መሆናቸው፣ ሲቪል ሰርቫንቱ የፖለቲካ አራማጅና  የፓርቲውን የደንብ ለብሶ የፓርቲ  አባል እንዲሆን የተጀመረው በደርግ ሥርዓት እንደነበር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ይገልጻሉ። ይህም ቀደም ሲል የተጀመረውን የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ባሕል አበላሽቶታል። ይህ ባሕል ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ቀጥሎ ጉዳት አድርሷል። ኢሕአዴግ በወቅቱ ከደርግ ሥርዓት ጋር ወግኗል ያለውን ከሲቪል ሰርቪሱ አስወጥቶ ተጎጂ አድርጓል።

የመንግሥት የዘርፉ ትኩረት


የዜጎች ግልጋሎት ጉዳይ ዝማኔ ያሻዋል። ወጥ ሆኖ ደረጃውን ጠብቆ ሊዘረጋ ይገባዋል። የመንግሥት አገልግሎትን ጉዳይ የመንግሥትን አቋም የማገልገል ጉዳይ አድርጎ መመልከት አይገባም። የሕዝብና የአገር አገልግሎት ነው፤ ስኬታማ ልማትና አገር የሚገነባው በስኬታማ ሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ነው። 

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ባለፉት ዘመናት የግሉ ዘርፍ ለሲቪል ሰርቫንቱ መበላሸት አስተዋጽኦ አድርጓል። የሚገባውን አገልግሎት በተገቢው መንገድ ማግኘት ሲችል ገንዘብ ስላለው ብቻ በገንዘቡ አገልግሎትን ሲገዛ ነበር። ስለዚህ ገንዘብና አገልግሎት መራራቅ አለባቸው። ሲቪል ሰርቪሱን በሙያተኛ የማደራጀትን ተግባር ይጠይቃል።

በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው መንግሥት የሲቪል ሰርቪስን ዘመን ተሻጋሪና በመንግሥት መለዋወጥ የማይዛባ መዋቅር እንዲሆን ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል። አዲሱ የሰው ኃብት ልማት ፖሊሲ ከሚገዛባቸው መርሆዎች ዋናው ከስትራቴጂዎችና ከአደረጃጀት፣ ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና መሳሪያዎች በላይ ለሰዎች ዕውቀትና የአስተሳሰብ ልህቀት አብልጦ ትኩረት ማድረጉን በ2013 ዓ.ም የታተመው የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ ፍኖተ-ካርታ አመላክቷል። ከሰው ኃብት ልማት መስኮች መካከልም በመንግሥት ዘርፍ የሰው ኃብት ልማት ፖሊሲ ለሰዎች የፈጠራ ችሎታ፣ ምጡቅ አስተሳሰብ እና ሃሳብ የማመንጨት ችሎታ ከዕውቀትና ከክህሎት በላይ ዋጋ የሚሰጠው “ቅድሚያ ችሎታ ላላቸው” የሚለው መርህ አንዱ ነው። 

ለመንግሥት ሠራተኛነት የሚመለመሉ ሰዎች ‘ምሉዕ ስብዕና’ን ተላብሰው ዘርፉን እንዲቀላቀሉ፣ ለዜጎች የላቀ ውጤት ሊያስመዘግቡ የሚችሉ፣ ፈጠራን የሚያመነጭ ብሩህ አዕምሮ፣ ምጡቅ አስተሳሰብና የአዲስ ሐሳብ ባለቤቶች ሊሆኑ ይገባል። ስለሆነም በጥንቃቄ መቅጠር፤ ጥፋትን ፈጥኖ ማረም፣ ውጣ ውረድ የበዛበት የሥራ ሰንሰለትን ማሳጠር፣ አሠራርን ማቅለል፣ ችግር-ፈቺዎች፣ ለሠራተኞች ግልፅ ዕቅድ የሚሰጡ፣ አዳዲስ የሥራ ሂደቶችን የሚቀርጹና በተግባር ደግፈው ለሠራተኛው የሚያስተዋውቁ ብቁ የሥራ መሪዎችን ማፍራት፣  ማገልገል ክብር የሆነበት ሥርዓት መገንባት በተለይም የመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎታቸው በገንዘብና በንብረት ጥቅም የሚለካ ሳይሆን፤ ዜጎችን አክብሮ ከሚሰጥ የላቀ አገልግሎትና ከተገልጋይ ዜጎች እርካታ በሚመነጭ አንጸባራቂ ክብር መሆኑን ማሳመንን ትኩረት አድርጓል።

በፍኖተ-ካርታው እንደተመላከተው ሙያዊ ብቃት ያለው ነፃ፣ ገለልተኛ የመንግሥትና የሕዝብ አገልጋይ  ከማድረግ ባሻገር የአደረጃጀቶችን ምክንያታዊነት ማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ ለውጤት ተኮር አፈጻጸም ትኩረት መስጠት፣ ግልፅነት፣ ተደራሽነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ላይ በትኩረት ይሰራል። የመንግሥት ዘርፍ የሰው ኃብት ልማቱ በተለዋዋጭ ሁኔታዎችና ለውጦች የሚያልፍ በመሆኑ፤ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ ማለፍን ይጠይቃል። በዚህም ምክንያት ከዘመን ዘመን የሚለዋወጥ ቁመናውን የሚወስኑ “ዕሴቶችን” ዜጎች/ተገልጋዮች ከሚፈልጉት ውጤት ጋር የሚጣጣሙ አድርጎ መላበስና ለየዘመኑ ጥያቄ ምላሽ ሰጪ የሆኑ አሠራሮችን ቀርጾ መተግበርን ይጠይቃል።

የመንግሥት ሠራተኛን ከፖለቲካዊ ርዕዮተ-ዓለምና ወገንተኛነት ጋር አዛምዶ በመንግሥት ሥራዎች ላይ መመደብ የብልሹ መንግሥታዊ ሥርዓት መገለጫ ነው። የመንግሥት አገልግሎት ዘርፉ ተለውጦ በሁለንተናዋ የበለፀገች ኢትዮጵያ ተፈጥራ በተለወጠ ሥርዓትም ትውልድ በቅብብሎሽ ሊኖርባት እንዲችል ተስፋና እምነት ሰንቆ መራመድ የግድ ይላል። ነባሩን የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት ዘመኑን የዋጀ፣ ከፖለቲካ ጋር ያልተዛመደ፣ ለሀገረ መንግሥቱ ሕልውና የወገነ እንዲሆን ሁለንተናዊ ለውጥ እንደሚያስፈልገው ብዙዎች ያነሳሉ። ሰብዓዊ ልማትን ማዕከል ያደረገ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሆኖ መዘርጋት አለበት። 

በመሆኑም ከፖለቲካ ፓርቲ ተጽዕኖ እና አላስፈላጊ ጣልቃገብነት ነፃና ገለልተኛ የሆነ፣የመፈጸም ብቃት ያለው የአገልግሎት ሥርዓት ለሀገረ መንግሥት  ግንባታ ተጨማሪ ጉልበት ነው። ስለሆነም “አርቆ በማሰብ፣ እንደገና ከአድማስ አቆራርጦ በማሰብ” በሥርዓቱ ግንባታ ዳግም ምልከታና ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል። በማንኛውም የመንግሥት አገልግሎት ዘርፍ የሚሰማራ የሰው ኃይል በብቃትና በችሎታው ተመልምሎና ተመርጦ ከተሰማራ፣ የአገልጋይነት አስተሳሰብና ዕምነት በሕዝብ ውስጥ ከሰረጸ፣ ንቃተ ኅሊና ካደገና በአዲስ ዕውቀት ከበለጸገ በእርግጠኝነት የአገልግሎት ዘርፉ ችግር ይወገዳል። ሥርዓቱ በማይናወጥ ማዕዘን ላይ ከተሰራ ደግሞ ‘መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር የሚቀያየር ሲቪል ሰርቫንት ይዘን እስከመቼ ነው የምንዘልቀው’ የሚለው ተጠየቅ ገቢራዊ ምላሽ ያገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም