በ1500 ሜትር ማጣሪያ ድርቤ ወልተጂና ጉዳፍ ፀጋይ ለፍጻሜ አለፉ - ኢዜአ አማርኛ
በ1500 ሜትር ማጣሪያ ድርቤ ወልተጂና ጉዳፍ ፀጋይ ለፍጻሜ አለፉ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ1500 ሜትር የግማሽ ፍጻሜ ውድድር አትሌት ድርቤ ወልተጂና አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለፍጻሜ አልፈዋል።
በምድብ 2 የተወዳደረችው ድርቤ 3 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ ከ10 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ ወጥታለች።
በዚሁ ምድብ የነበረችው ጉዳፍ 3 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ ከ41 ማይክሮ ሴኮንድ አራተኛ ደረጃን ይዛ ለፍጻሜው አልፋለች።
በምድብ 1 ውድድሯን ያደረገችው ብርቄ 4 ደቂቃ ከ03 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ 10ኛ በመውጣት ለፍጻሜው ማለፍ አልቻለችም።
በሁለት ምድብ ተከፍሎ በተካሄደው የማጣሪያ ውድድር ከየምድቡ ከአንድ እስከ ስድስት የወጡ አትሌቶች ለፍጻሜው አልፈዋል።
የፍጻሜው ውድድር ቅዳሜ ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ላይ ይከናወናል።
በፍጻሜው የኢትዮጵያ አትሌቶች ከኬንያውያኑ አትሌቶች ፌዝ ኪፕዬጎንና ሱዛን ሎካዮ ኢጆሬ ጋር የሚያደርጉት ፋክክር ከወዲሁ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።