ቀጥታ፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራን ለማሳካት ተቋማት በትጋት ሊሰሩ ይገባል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦ መንግሥት የጀመረውን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ለማሳካት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ ተቋማት በአርዓያነትና በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆኑ ተቋማት የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት ተገምግሟል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የ2016 በጀት ዓመት በብዙ መልኩ ስኬት የተመዘገበበት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን ዕድገት ማስቀጠል የተቻለበት ዓመት እንደሆነ ጠቅሰው በተያዘው በጀት ዓመትም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በማሻሻያው የአገር ውስጥ ገቢን በማሳደግ አገራዊ የልማት ፍላጎትን በራስ አቅም ለማሳካት፣ የፋይናንስ ዘርፉን አካታችነትና ተወዳዳሪነት ለማጠናከርና የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጠን በማሻሻል ጠንካራ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ግብ መያዙን ጠቅሰው፤ ለስኬቱ መረባረብ እንደሚገባ አንስተዋል።

ከዚህ አኳያ ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆኑ ተቋማት በአርዓያነት ሌት ተቀን መትጋት፣ ሕገ-ወጥነትን መከላከልና ከድህነት የሚያላቅቁ ሥራዎችን ማፋጠን እንዳለባቸው ነው የገለጹት።

በግምገማ መድረኩ የተሳተፉት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ ተቋማት የመንግሥትን የመፈጸም አቅም በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።


 

ይህንን አቅም በተጨባጭ ሥራና በተደራጀ አገራዊና ተቋማዊ የተግባቦት ሥራ መግለጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትርና የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ፥ ተቋማቱ ለአገራዊ የሪፎርም አጀንዳዎችና ኢኒሼቲቮች መሳካት ታሪካዊ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።


 

ለአብነትም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በፍጥነት ወደ ማምረት እንዲገቡ ማድረግ፣ የፕሮጀክቶችን የአካባቢ ተፅዕኖ በየጊዜው መፈተሽ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ቀነዓ ያደታ (ዶ/ር)፤  ተጠሪ ተቋማት ዕቅዳቸውን በአብዛኛው ማሳካታቸውን ጠቅሰው፤ በአዲሱ በጀት ዓመትም አሰራሮችንና ሕግጋትን በመተግበር ውጤት ማምጣት ይጠበቃል ብለዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) በሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ የሚያሻሽል ሙያን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት እንደሚኖር ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ለጠቅላይ ሚኒስትር ተጠሪ የሆኑ ተቋማት በአሰራር፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል አርዓያ ሆነው እንዲሰሩ ድርብ ተልዕኮ እንደተሰጣቸው አስገንዝበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በሰጡት ማጠቃለያ፤ ቁልፍ ችግሮችን የሚፈታ፣ ሙስናን መዋጋት የሚችል አመራር ለመገንባት የሁሉንም ትኩረት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

በአዲሱ በጀት ዓመት መልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥን በመሰረታዊነት ለመቀየር መንግሥት ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፥ ተቋማቱም ለስኬቱ እንዲረባረቡ አሳስበዋል።

ብልሹ አሰራርን መከላከልም ዋነኛው የመንግሥት ዐቢይ ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋምን ማዘመንና ዘላቂነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የተቋማቱ ዕቅድና ሪፖርት ከአገራዊ ስትራቴጂክ ዕቅድና ከልማት ግቦች ጋር በተናበበ መልኩ የተዘጋጁ፣ መፈጸም የሚችሉና የሚለኩ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም