ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ያላትን አመቺ የካካዋ የግብርና ሥነ-ምህዳር በመጠቀም ከዘርፉ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል  

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ለካካዋ ምርታማነት ተስማሚ አየር ንብረትና የግብርና ሥነ-ምህዳር ያላት በመሆኑ አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የግብርና ተዋናዮች በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ተመላከተ።   

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል በካካዋ ምርት የተደረገውን የምርምር ውጤት የማስተዋወቅና ለተጠቃሚ የማስተላለፍ የአውደ-ጥናት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።


 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሞ (ዶ/ር)፤ የምዕራብ አፍሪካ አገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የካካዋ ምርት በማምረት ኢኮኖሚያዊ ተጠቀሚነታቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።  

ኢትዮጵያን  በደቡብ፣ በምዕራብና ማዕከላዊ የአገሪቱ ክፍል ከፍተኛ ካካዋን የማምረት ጸጋ ቢኖራትም አምራች ባለመሆኗ ከዘርፉ ተጠቃሚ ሳትሆን እንደቆየች ነው የሚያስረዱት። 

ለካካዋ ምርት ያለውን ምቹ የግብርና ሥነ-ምህዳር፣ የአፈርና የአየር ንብረት ጸጋ ታሳቢ በማድረግ  ከ20 ዓመት በፊት ጀምሮ በተሰራ የምርምር ውጤት አንድ የካካዋ ዝርያ ውጤታማነቱ ተረጋግጦ ተለቋል ብለዋል።

ውጤታማነቱ ተረጋግጦ የተለቀቀው የካካዋ ምርትም በተሟላ ሁኔታ ከተሰራበት ከቡናና ሌሎች የግብርና መስኮች ባልተናነሰ ሁኔታ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምንጭ ከፍተኛ አቅም እንደሚሆን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ፈቃዱ ጉርሙ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች የካካዋ አምራች አገራት በተለየ መልኩ ለዘርፉ ምርታማነት ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ሁኔታ በመኖሩ የግብርና ተዋናዮች በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ኢንስቲትዩቱም ለካካዋ ምርታማነት ያለውን ተስማሚ ጸጋ ታሳቢ በማድረግ ምርታማነቱን በማስፋፋት አገርን ከዘርፉ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ቀጣይነት ያለው የምርምር ሥራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።  

በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል የቅመማቅመምና የካካዋ ተክል ተመራማሪ አቡኪያ ጌቱ፤ ሞቃታማና እርጥበታማ አካባቢዎች ለካካዋ ምርታማነት አመቺ ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያም በደቡብ፣ በምዕራብና ማዕከላዊ የአገሪቱ ክፍሎች "ፎራስት ኢሮ-ዋን" የተሰኘን የተሻለ አንድ የካካዋ ዝርያ ማስፋፋት እንደሚቻል በጥናት ማረጋገጥ እንደተቻለ ተናግረዋል።

የንብ ከረሜላ የቤተሰብ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ምሕረትአብ ተሾመ፤ ካካዋ ቸኮሌትን ለማምረት ዓለም ላይ ከ100 ቢሊየን ዶላር በላይ ግብይት የሚፈጸምበት ተፈላጊ የግብርና ምርት ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያም የካካዋ ምርታማነትን ማስፋት ከተቻለ ከውጭ የሚገቡ የፋብሪካ ግብዓቶችን በመተካት ከፍተኛ አቅም እንዳላት በምርምር ማረጋገጥ እንደተቻለ ተናግረዋል። 

በአፍሪካ ኮትዴቯር፣ ላይቤሪያ፣ ጋና፣ ካሜሩን፣ ዩጋንዳ፣ ሴራሊዮን፣ ናይጄሪያና ፓፓዋ ኒው ጊኒ፤ በደቡብ አሜሪካ ኢኳዶር፣ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ሜክሲኮ፣ ፔሩ፣ ቬንዝዌላና ዶሚኒካን ሪፐብሊክ፤ በእስያ ሕንድና ኢንዶኔዥያን የመሳሰሉት ከፍተኛ የካካዋ አምራች አገራት ናቸው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም