ቀጥታ፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስምሪቶች ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና ነበራቸው - አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦የተቋሙ ስምሪቶች ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተለያዩ የሥራ ክፍሎችን ተዘዋውረው በመጎብኘት በቀጣይ ስምሪቶች ዙሪያ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡


 

ተቋሙ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ የሰላም መደፍረሶችና ግጭቶች እንዲፈቱ፤ ኅብረተሰቡም በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ፤ በተከናወኑ ስምሪቶችና ኦፕሬሽኖች ጸረ ሰላም ኃይሎችና ጽንፈኞች የሀገርንና የህዝብን ሰላምና መረጋጋት ለማወክ የሚሠሯቸው የተለያዩ ሴራዎች ከሽፈዋል፡፡ በዚህም የጸጥታ ችግር ያለባቸውን አካባቢዎች ማረጋጋትና ሀገርን ማጽናት ተችሏል ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች የነበራቸው ቁርጠኝነት ከፍተኛ ነበር ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፤ የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ሥራን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።


 

ተቋሙን በአደረጃጀት፣በአሠራር፣ በቴክኖለጂና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ከፍ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ተግባራትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን አመልክተዋል፡፡

የላቀ የመፈጸም አቅም ያለው ተቋም እየተገነባ መሆኑን እንዲሁም ሀገራዊ ሰላምና ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ የሚያበረክተው የማይተካ ሚና ጎልቶ እየታየ በመሆኑ፤ ይህን ያረጋገጠው ሪፎርም ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት እየተቃኘ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች በ2016 የበጀት ዓመት የነበራቸው የላቀ አፈጻጸም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሥራ ስምሪት መስጠታቸውን አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙኃን የላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም