የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት ተመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት ተመረቁ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ በስነ-ልቦና ግንባታ፣ በሀገር ፍቅር ስሜትና በአካል ብቃት ሥልጠና የወሰዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት ተመረቁ።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ 2ኛ ዙር የዕጩ መኮንን ሰልጣኞች የትከሻ ምልክት የማልበስ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በሥነ-ሥርዓቱ የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ኦፕሬሽን ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ለገሠ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያደቻን ጨምሮ የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ተመራቂ የአየር መንገድ የተቋም ደኅንነት አባላቱ በንድፈ-ሃሳብና በተግባር መሠረታዊ ውትድርና እና የአካል ብቃት ሥልጠና የወሰዱ መሆናቸውም ተገልጿል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያደቻ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከምስረታው ጀምሮ ብቁና ውጤታማ ተቋም እንዲሆን የቀድሞ የኢትዮጵያ ኃይል አመራሮች የነበራቸውን አይተኬ ሚና አስታውሰዋል።
አሁንም እገዛና ትብብሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ ሁለቱ ተቋማት የቆየ ታሪካዊ ትስስር ያላቸውና የሀገር ኩራትም ናቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ሰልጥነው በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት በንድፈ-ሃሳብና በተግባር ሥልጠና የወሰዱ ናቸው ብለዋል።
ከዚህ በፊት በአየር ኃይል አካዳሚ 248 አብራሪ ካዴቶች፣ 303 የአውሮፕላን ጥገና ሠራተኞች መሰልጠናቸውን አስታውሰው፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ የደኅንነት ጥበቃ አባላት ተመርቀዋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ላደረገው የላቀ አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ኦፕሬሽን ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ለገሠ፤ አየር ኃይሉ ሁሉን አቀፍ ተቋማዊ አቅም ግንባታ ሪፎርም ላይ መሆኑን ገልፀዋል።
አየር ኃይል ከራሱ የሰው ኃይል ባሻገር ለሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት የትከሻ ምልክት ያደረጉ ዕጩ መኮንን ሰልጣኞችም ሆነ ተመራቂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት በቀጣይ ለላቀ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲዘጋጁ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአየር መንገድ ጋር ያለውን አብሮነትና ትብብር አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት መካከል ብርሀኑ ጎንፋ እና በዓለምላይ ተመስገን፤ በአየር ኃይል ቆይታቸው ጠቃሚ ትምህርትና ሥልጠና ማግኘታቸውን ገልፀዋል።
በቀጣይም በሥራ መስካቸው ተቋማቸውን በቅንነትና ታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የትከሻ ምልክት የለበሱ የአየር ኃይል ዕጩ መኮንን ሰልጣኞችም፤ በጥብቅ ዲሲፕሊን የታገዘ የንድፈ-ሃሳብና የተግባር ሥልጠና መውሰዳቸውን ገልጸው፤ በቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።