ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ለጤና ተቋማት የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ከ58 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የጤና ተቋማቱ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚገኙ 32 የጤና ተቋማት መሆናቸውም ተገልጿል።


 

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ተጠባባቂ ዋና ፀሐፊ አበራ ዱሜሳ፤ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም ከብሪታኒያ መንግሥት በተገኘ የ14 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ እገዛ በአራት ክልሎች አደጋን መቋቋም የሚችል ፕሮጀክት ይፋ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በዚህም በተለያዩ ክልሎች በግጭትና ድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የድጋፍና መልሶ ማቋቋም ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።

አሁንም ከ58 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

የመድኃኒትና ቁሳቁስ ድጋፉን የትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጤና ቢሮ ኃላፊዎች ተረክበዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አማኑኤል ኃይለ፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አበበ ተምትሜ፣ የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ጉሻ በላከ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዱልሃቅ አህመድ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፋት 80 ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም