በሀገርና ህዝብ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም ህገ ወጥ ተግባራትን በብቃት መመከት የሚችል /ኦፕሬሽናል/ የዘመቻ መምሪያ ሃይል ተገንብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገርና ህዝብ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም ህገ ወጥ ተግባራትን በብቃት መመከት የሚችል /ኦፕሬሽናል/ የዘመቻ መምሪያ ሃይል ተገንብቷል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦ በሀገርና ህዝብ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ማናቸውንም ህገ ወጥ ተግባራትን በብቃት መመከት የሚችል /ኦፕሬሽናል/ የዘመቻ መምሪያ ሃይል መገንባቱን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ ገለጹ፡፡
የልዩ ፀረ-ሽብር መምሪያና የአድማ ብተና መምሪያ በንድፈ ሀሳብና በተግባር የሥራ ላይ ሥልጠና የወሰዱ የፖሊስ አባላት ተመርቀዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፤ በሀገርና ህዝብ ላይ ሊቃጡ የሚችሉ ህገ ወጥ ተግባራትን በብቃት የሚመክት /ኦፕሬሽናል/ የዘመቻ መምሪያ ክፍል ተገንብቷል ብለዋል።
ለሁለት ወራት የተሰጠው የአድማ ብተና የሥራ ላይ ሥልጠናም ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን በቀላሉ ለመቆጣጠር ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የአድማ ብተና ፖሊስ ጠንካራ ቁመናና ልምድ ያለው ሰራዊት መሆኑን ጠቅሰው በተለያዩ ግዳጆች ላይ ስምሪት በመውሰድ በላቀ ብቃት እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።
ከለውጡ በኋላ በተደረገ ሪፎርም በሀገር ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም ጥቃቶች በማንኛውም ጊዜና ቦታ በብቃት መመከት የሚያስችል ኦፕሬሽናል/ ዘመቻ መምሪያ ክፍል መቋቋሙን አስታውሰዋል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሰማርቶ የሰላም ማስከበር ሥራውን በብቃት የሚወጣ የአድማ ብተና ፖሊስ ሰራዊት መገንባቱንም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን የማስከበር ተልዕኮን ለመወጣትና ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ዝግጁ የሆነ አስተማማኝ ሃይል መገንባቱን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተልዕኮው ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን መጠበቅ በመሆኑ ለዚህም የላቀ ዝግጁነት አለው ሲሉ አረጋግጠዋል።