መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እየሰራ ይገኛል - አቶ ብናልፍ አንዱአለም - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እየሰራ ይገኛል - አቶ ብናልፍ አንዱአለም
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እየሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱአለም ገለጹ።
ሚኒስትሩ የዛምቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ እና የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ጃኮብ ጃክ ምዊቡን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ በውይይቱ ወቅት በሀገራችን ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ያብራሩ ሲሆን በቀጣይም ያጋጠሙ ችግሮችን በውይይትና በመነጋገር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሀገራችንን ልማት ከማረጋገጥ አንጻር በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በግብርና፣ በአረንጓዴ አሻራና በአይ ሲቲ ዘርፍ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ መንግስት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ህገ- ወጥ የሰዎችን ዝውውር ለመቀነስና በህጋዊ መንገድ እንዲሔዱ በማድረግ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን ሞት፣ ስቃይና እንግልት ለማስቀረት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በተጨማሪም የዛምቢያ መንግስት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
የዛምቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ እና የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ጃኮብ ጃክ ምዊቡን በበኩላቸው በዛምቢያና በኢትዮጵያ መካከል የቆየ ግንኙነትና ትብብር እንዳለ ገልጸው ለአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ነጻ መውጣት የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ለዚህም ያላቸውን ክብርና አድናቆት ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በሰላምና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ በጋር ለመስራት ያላቸውን ሃሳብ ገልጸው፤ በተለይ ሀገራቸው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መተላፊያ መንገድ እንደመሆኗ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ኢ- ሰብአዊ ድርጊትና እንግልት በዘላቂነት ለማስቀረት በትብብርና በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አያይዘውም በደቡብ ኢትዮጵያ በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘንም ገልጸዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ በማጠናከርና የጋራ የመረጃ ልውውጥ ስርአት በመዘርጋት የአፍሪካን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ብሎም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊያን ለመፍታት ከምን ጊዜውም በላይ ልንሰራ ይገባል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።