ቀጥታ፡

ኮሌጁ ለመጀመሪያ ጊዜ በፀሐይ ሐይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ቁሶችን የሚጠግኑና የሚዘረጉ 48 ባለሙያዎችን ዛሬ አስመረቀ

ድሬዳዋ፤ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፡-በድሬደዋ የሚገኘው የኢትዮ- ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በፀሐይ ሐይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ ቁሶችን የሚጠግኑና የሚዘረጉ 48 ባለሙያዎችን ዛሬ አስመረቀ።

መንግስት ከዋና የኤሌክትሪክ መስመሮች በርቀት ስፍራ የሚገኙ የአገሪቷን የአርብቶና አርሶ አደሮች ቀበሌዎችን በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።

ባለፈው ወር ብቻ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በምስራቅ የአገሪቷ ክፍሎች በብዙ ሚሊዮን ብር ያስገነቧቸውን የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶች መርቀው ወደ አገልግሎት ማስገባታቸው ይታወሳል።


 

የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶቹ ወጥነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ በመስኩ የሚሰማራ የሰው ሃይል ለማፍራት ደግሞ በድሬዳዋ የሚገኘው የኢትዮ- ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር የስራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው እንደተናገሩት፤ የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶቹ የገጠሩን ህብረተሰብ ሁለንተናዊ ህይወት እንዲቀይሩና ህብረተሰቡ ከተረጂነት እንዲላቀቅ የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያፋጥኑ ናቸው።


 

በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ በሙያው የሰለጠኑ ሙያተኞችን በብዛት ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

የድሬዳዋ ኢትዮ - ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለመጀመሪያ ጊዜ አሰልጥኖ ያስመረቃቸው 48 ባለሙያዎች በዚህ ረገድ መሠረታዊ አበርክቶ አላቸው ብለዋል።

በተለይም በድሬዳዋ በ2016 ዓ.ም ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የአርሶ አደሩን ህብረተሰብ ህይወት ለመለወጥ እና አነስተኛ መስኖዎችን ለማስፋፋት የተዘረጉትን የፀሐይ ኃይል ፕሮጀክቶች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጡ የባለሙያዎቹ ድርሻ የጎላ መሆኑን ነው የገለፁት።

ለዚህም ከግብርና፣ ከትምህርት እና ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ወደ ስራ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የድሬዳዋ ቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋጡም ሙስጠፋ በበኩላቸው ዛሬ የተመረቁት ባለሙያዎች በጸሀይ ሀይሉ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።

ኮሌጁ በሀገር ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ላይ ክህሎት መር ዕውቀት የጨበጡ ባለሙያዎችን በማፍራት ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በማቅረብ ላይ ይገኛል ያሉት ደግሞ የኢትዮ -ጣሊያን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ታደለ አሰፋ ናቸው።


 

አቶ ታደለ እንዳሉት፤ ዛሬ በአጫጭር የትምህርት መርሃግብር ለስምንት ወራት የተግባርና የንድፈ ሐሳብ ስልጠናቸውን አጠናቀው የተመረቁት ባለሙያዎች አሁናዊውን የገበያ ፍላጎት የሚያሟሉ ናቸው።


 

ከተመራቂዎቹ መካከል ወጣት ሌንሳ አብዱልሰላም እንዳለችው፤ በድሬዳዋ እና በማያ ከተሞች በዘርፉ  የሚታየውን የባለሙያ ክፍተቶቹን ለመሙላት መመረቃቸው ወቅታዊ መሆኑን ተናግራለች።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም