ቀጥታ፡

ባለፉት ሁለት ወራት በብቁ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ከተለያዩ አገራት ከ80 ሺ በላይ የርቀት ስራ ማምጣት ተችሏል- የስራና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦ባለፉት ሁለት ወራት በብቁ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ከተለያዩ አገራት ከ80 ሺ በላይ የርቀት ስራ(ሪሞት ጆብስ) ማምጣት መቻሉን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የመረጃ ቋቱ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ስራ ለማግኘት መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ ብቁ ወይም (E-LMIS) የተሰኘ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት በማበልፅግ ለዜጎች ፍትሃዊ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 36ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ በርቀት ስራ ወይም ሪሞት ጆብስ በርካታ ወጣቶችን ማሰማራቷን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የስራ መስኩ እጅግ አጓጊ፣ከአገር ሳይወጡ የሚሰራና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የመረጃ ቋቱ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ስራ ለማግኘት መመዝገባቸውንና ከእነዚህም መካከል 345 ሺህ ዜጎች የውጭ አገር ስራ ስምሪት ተጠቃሚ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ፕሮጀክት አስተባባሪ ብርሃኑ አለቃ ለኢዜአ እንዳሉት ክፍሉ የራሱ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ተቋቁሞለት እየሰራ ይገኛል፡፡

በዚህም ባለፉት 11 ወራት 23 አገልግሎቶችን ለመስጠት አቅዶ እስካሁን 17 ቱን አጠናቆ ወደ ስራ ማስገባቱን ተናግረዋል።

የለማው የመረጃ ቋት ከ23 የሚበልጡ ዌብሳይቶችን በአንድ ላይ በመያዙ ዜጎች ስራ ለመፈለግ የሚያባክኑትን ጊዜ በእጅጉ እንደሚቀንስላቸው አብራርተዋል።

ብቁ ስራ ፈላጊው እንግልት ሳይደርስበት ስራ እንዲያገኝ ከማድረግ በዘለለ ፍትሃዊ የስራ እድል እንዲፈጠርና በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ መሆኑንም ተናግረዋል።

በስርዓቱ እስካሁን ከ 80 ሺህ በላይ የርቀት ስራዎች መምጣታቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል።

ከመጣው ጠቅላላ 80 ሺህ ስራ ውስጥ ወደ 17 ሺህ በዚህ ሶስት ሳምንት የመጣ ሲሆን ከዚህ ውስጥ  ከ 6 በላይ የሚሆኑ ስራውን ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የስራ ዕድሉን ያገኙት ተጠቃሚዎች ወደ 55 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ደሞዝ እንደሚኖራቸውም ነው ያብራሩት።

በለማው የገበያ መረጃ ስርዓት እስካሁን ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች መመዝገባቸውንና ከእነዚህም መካከል 345 ሺህ ያህሉ የውጭ አገር ስራ ስምሪት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የለማው E-LMIS (ብቁ)  የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት  ዕድሜው ከ15 እስከ 64 የሆነ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የተለያዩ የአገር ውስጥና  የውጪ አገር የስራ ስምሪት መረጃዎችን የሚያገኝበት ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም