ለዘመናት ጥያቄ ምላሽ ሰጪው ጭላንጭል ተስፋ

በትንሳኤ ገመቹ (ኢዜአ)

የዛሬው የ76 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ያኔ በለጋነታቸው፤ ዳገት፣ ቁልቁለት፣ ሜዳ ሳይመርጡ እንዳሻቸው በሚቦርቁበት፣ ሮጠው በማይጠግቡበት፣ ገና ታዳጊ ሳሉ በ13 ዓመት ዕድሜያቸው በደረሰባቸው የተሽከርካሪ አደጋ ነው ሁለት እግሮቻቸውን ያጡት። ይሁንና ይህ ጉዳታቸው ሳይበግራቸው በብዙ ውጣ ውረድና እልህ አስጨራሽ ትግል በትምህርታቸው እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ መዝለቅ ችለዋል።

እኚህ ሰው ካለሙበት ለመድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል። ትውልድና ዕድገታቸው በአዲስ አበባ መሆኑ በተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቼር) ድጋፍ ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ ዕድልን ሰጥቷቸዋል፤ የሥራ ዓለምንም ተቀላቅለዋል። ይህ ስኬታቸው ግን እንዲሁ እንደዋዛ የተገኘ አልነበረም።

የመዲናዋ የእግረኛም ሆኑ የተሽከርካሪ መሄጃ አስፓልት መንገዶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያላደረጉ፤ ለዊልቼር መንቀሳቀሻ በቂ ቦታ የሌላቸውና አስቸጋሪ መሆናቸው እንቅስቃሴያቸውን በእጅጉ አክብዶባቸዋል፤ ለዓመታት በዊልቼር የተመላለሱባቸው ለእግረኛ እንኳን የማይመቹ የተቦረቦሩ፣ ወጣገባ፣ ዳገታማና ቁልቁለታማ መንገዶች ተጨማሪ የሕይወት ፈተናዎቻቸው ነበሩ። አዛውንቱ በታዳጊ፣ በወጣትነት እና በጉልምስናም ዕድሜያቸው በእጅጉ የፈተኗቸውን እነዚያን የስቃይ ጊዜያት “መቼም አልረሳቸውም” ሲሉ እንደ እርሳቸው የአካል ጉዳት የገጠማቸውን ሰዎች የዕለት ተዕለት ተግዳሮቶች ይገልጻሉ፤ አቶ አለበል ሞላ።

ዓለም አቀፋዊ የአካል ጉዳተኝነት ሁኔታ

በዓለም-አቀፉ የአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቬንሽን አንቀፅ አንድ እንደተመለከተው አካል ጉዳተኝነት ከረጅም ጊዜ የአካል፣ የአዕምሮ ወይም የስሜት ህዋሳት እክል ጋር የሚኖሩና በአመለካከትና በአካባቢያዊ ጋሬጣዎች ምክንያት በማኅብረሰቡ ውስጥ ሙሉና ትርጉም ያለው ተሳትፎ በእኩልነት ማድረግ የማይችሉ ሰዎችን ያጠቃልላል።

አካል ጉዳት ማለት፤ የአካል ክፍልን ማጣት ወይም የተግባር መገደብን የሚያመላክት ፅንሰ-ሀሳብ ነው። አካል ጉዳተኝነት ማለት ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ጋር እኩል ተሳትፎ እንዳያደርጉ የሚያደርግ የአካል ጉዳት፣ የአመለካከት ችግርና አካባቢያዊ መሰናክሎች ድምር ውጤት ነው።

በዓለም ላይ የተለያየ አይነት አካል ጉዳተኝነት የሚያጋጥም ሲሆን፤ ዓይነ-ስውርነት፣ መስማት መሳን፣ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት፣ ማየትና መስማት መሳን እንዲሁም ተደራራቢአካል ጉዳት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2023 ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ያህል ሰዎች የተለያየ አይነት የአካል ጉዳት ያጋጥማቸዋል። ይህ አሃዝ 16 በመቶ የሚሆነውን የዓለምዝብ ቁጥር የሚወክል ነው። ይህም የአካል ጉዳት ከስድስት ሰዎች በአንዱ ላይ አለ ማለት ነው። እነዚህ ዜጎች ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ተያያዥ የጤና እክሎች የሚያጋጥማቸው መሆኑንም መረጃው ያሳያል። ድብርት፣ አስም፣ የስኳር በሽታ፣ ስትሮክ፣ አላስፈላጊ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ የአፍ ጤና እክልና ሌሎችም ተያያዥ በሽታዎች ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ተያይዘው ከሚከሰቱት መካከል ይጠቀሳሉ

በዓለም ላይ ስለ አካል ጉዳተኝነት ያለው ስያሜ የተለያየ ነው። ለምሣሌ በተለያዩ አገራትለው ቴክኖሎጂ፣ የሰዎች አመለካከት፣ ከድጋፍ አሰጣጥና ከመሰረተ ልማት ተደራሽነት ጋር ተያይዞአካል ጉዳተኝነት የሚሰጠው ስያሜ እንዲለያይ አድርጓል። ለአብነት ለዓይነስውራን ልዩ የዓይን መነፅርና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማቅረብ በሚችሉ አገራትይነስውራን እንደ አካል ጉዳተኛ አይታዩም። የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት የማይሄዱት በወላጆቻቸው የተዛባ አመለካከትና ትምህርት ቤቶች ለልዩ ፍላጎት ማስተማሪያ ተገቢውን ቁሳቁስ ማሟላት ባለመቻላቸው እንጂ ሕፃናቱ መማር ስለማይችሉ ወይም ቢማሩ ስለማይለወጡ አይደለም። ይህን ማሟላት በቻሉ አገራት የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች እንደ አካል ጉዳተኛ ሊቆጠሩ አይችሉም።

በሌላ በኩል በተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቼር) ለሚንቀሳቀስ ሰው ትምህርት ቤትም ሆነ ወደ ስራ ቦታ ለመሄድ የሚያዳግተው አካል ጉዳቱ ሳይሆን፤ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ሳይፈጠርለት ሲቀር ብቻ ነው። የተባበሩት መንግሥታት የትምህርትሳይንስናባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) መረጃ እንደሚያሳየው በታዳጊ አገራት 90 በመቶ አካል ጉዳተኛ ልጆች ትምህርታቸውን አይከታተሉም። እ.ኤ.አ 1998 ይፋ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥናት የአካል ጉዳተኛ ጎልማሶች ዓለም አቀፋዊ የማንበብ ደረጃ ሦስት በመቶ ሲሆን የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ደግሞ አንድ በመቶ ብቻ መሆኑንመላክቷል።

አካል ጉዳተኝነት በአፍሪካ

በአፍሪካ 80 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተለያየ አይነትአካል ጉዳት እንዳለባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል። በአህጉሪቱ በተለይም በየጊዜው የሚከሰቱ አለመረጋጋቶች፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በርካቶችን ለአካልና ለአዕምሮ ጤና ጉዳት የሚዳርጉ ምክንያቶች ሆነው ይጠቀሳሉ። የአብዛኞቹ የአፍሪካገራት ፈተናዎች የሆኑት የምጣኔ ሀብት እና የመሠረተ ልማት ችግሮች አካል ጉዳተኞችን የበለጠ ጫና ውስጥ የሚከቱ ከመሆናቸው ባሻገር ተገቢውን ድጋፍ እንዳያገኙ ተግዳሮት ሆነው ቆይተዋል።

አካል ጉዳተኝነት በኢትዮጵያ

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዓለም ጤና ድርጅትና የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ዜጎች ከተለያየ ዓይነት የአካል ጉዳት ጋር እንደሚኖሩ ግምት አስቀምጠዋል። ይሁንና የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ከተካሄደ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ምን ያህል አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ትክክለኛ መረጃ ማግኘትን አዳጋች አድርጎታል። እነዚህ ዜጎች በጎጂ ልማዶችና በተዛባ አመለካከት እንዲሁም በሕግጋት እና በአፈጻጸማቸው ክፍተት ሳቢያ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እየተጋፈጡ እንደሆነም ይጠቁማሉ። በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች የሚመጥንመሠረተ ልማት አውታር ግንባታ አለመኖርናአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለት በርካቶችን ለከፍተኛ እንግልትና ለተጨማሪ የጤና እክል እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል። በመንገዶች ላይ የቁም እና የወለል ምልክቶች አለመኖር፤ በሕንፃዎች ላይ አካል ጉዳተኞችን የሚደግፉ መወጣጫዎች እጥረት፤ የመጸዳጃ እና ሌሎችም ተያያዥ አገልግሎቶች ላይ አካል ጉዳተኞች ተደጋጋሚ ቅሬታ እንዲያነሱም አድርጓል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ስምምነትን (Convention) ተቀብላ የሕጓ አካል አድርጋለች። የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት የሕንፃ አዋጆች ጸድቀው ወደ ስራገብቷል። 60 በመቶ በላይ አካል ጉዳተኞችን ለቀጠረ ድርጅት ከታክስ እናቀረጥ ነፃ የሚያደርግ መመሪያ ወጥቶ ስራ ላይ ውሏል። ይሁን እንጂ አካል ጉዳተኞችን እኩል ተሳታፊና ፍትሃዊ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብለው የወጡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሬት ላይ ወርደው በተጨባጭ ምን ለውጥ አመጡ? አፈፃፀማቸውስ? የሚለው አሁንም ድረስ የበርካቶች ጥያቄ ነው።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 41 ንዑስ አንቀፅ 5 እንደተደነገገው “መንግሥት የአካልና የአዕምሮ ጉዳተኞችን፣ አረጋዊያንና ያለ ወላጅ ወይም ያለ አሳዳጊ የቀሩ ሕፃናትን ለማቋቋምና ለመርዳት የአገሪቱኢኮኖሚ አቅም በፈቀደው ደረጃ እንክብካቤ ያደርጋል” የሚል ድንጋጌ ተቀምጧል። መንግሥት አካል ጉዳተኞችን በሚችለው አቅም መርዳት እንዳለበት የሚገልጸው ይህ ድንጋጌ በራሱ ትችት የሚቀርብበት ነው። ድንጋጌው አካል ጉዳተኞች አምራች እንዳልሆኑ እንዲሰማቸው የሚያደርግ መሆኑን ከሚተቹት መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎትና የአካቶ ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ተክለማርያም (ዶ/ር) አንዱ ናቸው።

እንደ እርሳቸው፤ በዚህ አንቀፅ አካል ጉዳተኞችን ዕድሜያቸው ካልደረሱ ሕፃናት እንዲሁም ስራ ሰርተው ከጨረሱ አረጋዊያን እኩል ቦታ መስጠቱ ተገቢ አይደለም። አካል ጉዳተኞች በውክልና ካልሆነ ንብረታቸውን ማውረስ እንደማይችሉ በሕገ መንግሥቱ መደንገጉ አካል ጉዳተኞች “አልችልም” የሚል የበታችነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ ነው። አካል ጉዳተኞች ሁኔታዎች ከተመቻቹላቸውና ዕድሉ ከተሰጣቸው ለራሳቸውም ሆነ ለሀገራቸው ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ ነው። ስለሆነም ይህ ለትርጉም ተጋላጭ የሆነውን አንቀፅ ማስተካከልና የኅብረተሰቡን አመለካከት መቀየር ካልተቻለ አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ጉዳዮች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የመሆን ዕድላቸው የሚፈለገውን ያህል አይሆንም። የአካል ጉዳት ያለባቸውን ዜጎች የተመለከቱጎች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ አመራሮችና ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ስለመሆኑ የሚጠቁሙት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ ሕጉን አስገዳጅ ማድረግ እስካልተቻለ ድረስ ክፍተቱ ሊፈታ አይችልም።

ትምህርት ሚኒስቴር የሚያወጣቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች አካቶ ትምህርትን የሚደግፉ ቢሆኑም፤ በየትምህርት ቤቶቹ ያለው አተገባበር ላይ ክፍተት መኖሩን አመልክተው፤ ይህም ከአመራር አካላት በጎ ፈቃደኝነትና ግንዛቤ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ቀደም ካሉት ዓመታት ከነበረው የተሻለ ግንዛቤ ቢፈጠርም፤ አሁንም 90 በመቶ የሚሆኑት ከትምህርት ውጭ ከመሆናቸውም ባለፈ አንዳንድ የሚወጡ ሕጎች አካል ጉዳተኞችን የዘነጉ ናቸው። አካል ጉዳተኞች የትምህርት ዕድል ማግኘታቸው በኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደርጋል። ይህም ካላቸው ከፍተኛ ቁጥር አኳያ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ዕድገትና ለድህነት ቅነሳ የድርሻቸውን እንዲወጡ ያስችላል ሲሉም ያክላሉ።

በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲግሪ ተማሪዎች የአካቶ ትምህርትን እንዲወስዱ መደረጉ አበረታች ውጤት መሆኑን የሚጠቅሱት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ “መሰል አስገዳጅ ሁኔታዎች የተዛባ አመለካከትን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላሉ” ይላሉ።

በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 9/4/ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸውለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቷ ሕግ አካል እንዲሆኑ ይደነግጋል። ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸውለም አቀፍ ስምምነቶች (Conventions) ውስጥ አንዱ ዓለም-አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብት ስምምነት ሲሆን፤ በዚህ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ መሰረት ኮንቬንሽኑ የአገሪቷ የሕግ አካል ሆኗል ማለት ነው።

በተጨማሪም የሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 25 ስለእኩልነት መብት ሲዘረዝር ሁሉም ሰዎች በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግባቸው እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። በዚህ አንቀፅ በአካል ጉዳት ምክንያት ልዩነት መደረግ እንደሌለበት በግልፅ ባያስቀምጥም "በሌላ አቋም ምክንያት" የሚለው ሐረግ አካል ጉዳትንም እንደሚጨምር ታሳቢ ይደረጋል ማለት ነው።

በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 41 ንዑስ አንቀፅ 5 ስለአካል ጉዳተኞች መብት በግልፅ ያስቀመጠ ሲሆን፤ አንቀፁመንግሥት የአካልና የአዕምሮ ጉዳተኞችን ለማቋቋምና ለመርዳት የአገሪቷ ኢኮኖሚ በሚፈቅደው መጠን እንክብካቤ ያደርጋል” ይላል። ይህ አንቀፅ አካል ጉዳተኞች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ የሰጠው መብት ቢኖርም ወደ መሬት ወርዶ ተጨባጭ ለውጥ ከማምጣት አኳያ በርካታ ቀሪ ስራዎች አሉ።

ሀገሪቷ ከምትከተለው እኩል የሥራ ዕድል መርሆ ጋር የሚጣጣም፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሥራ ሁኔታ የሚፈጥርና በሥራ ሥምሪት የሚደርስባቸውንድልዎ በፍርድ መድረኮች በቀላሉ ለማስረዳት የሚያስችል አሠራር መዘርጋት ወሳኝ በመሆኑ ስለ አካል ጉዳተኞች የስራ ስምሪት መብት የሚደነግግ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568/2000 ወጥቶ ተግባራዊ ሆኗል።

በዚህ አዋጅ ላይ እንደተመላከተው፤ የሥራው ጠባይ የማይፈቅድ ካልሆነ በቀር የተፈላጊ ችሎታ መመዘኛዎችን አሟልቶ የተገኘና በውድድር ውጤቱ ብልጫ ነጥብ ያገኘ ማንኛውም የአካል ጉዳተኛ በምንም ዓይነት መልኩ መድልዎ ሳይደረግበት፣ በማንኛውም መሥሪያ ቤት ወይም ድርጅት ውስጥ የሚገኝን ክፍት የሥራ ቦታ በቅጥር፣ በዕድገት፣ በድልድል ወይም በዝውውር የመያዝ መብት አለው።

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር በሚሰጥ የሥልጠና ፕሮግራም የመሳተፍ መብት እንዳለውና የተፈላጊ ችሎታ መመዘኛዎችን አሟልቶ የተገኘና ለውድድር ውጤት እኩል ወይም ተቀራራቢ ነጥብ ያገኘ ማንኛውም አካል ጉዳተኛ በምንም ዓይነት መልኩ መድልዎ ሳይደረግበት የተመደበበት የሥራ መደብ የሚያስገኘውን ደመወዝና ሌሎች ጥቅሞች የማግኘት መብት እንዳለው አዋጁ ያትታል።

የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን ስምምነት አዋጅ ቁጥር 676/2002 ላይ እንደተመላከተው፣ስምምነቱ ዋነኛ ዓላማ ሁሉም አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዓይነትብዓዊ መብቶችና መሠረታዊ ነፃነቶች ረገድ ሙሉ እና እኩል ተጠቃሚነት ያላቸው ስለመሆኑ ማረጋገጥ፣ ማሳደግና ለነዚሁ ጥበቃ ማድረግ፣ ብሎም ተፈጥሯዊ ክብራቸውን ከፍ ማድረግ ነው።

በዚሁ አዋጅ ስለ ሥራ እና ቅጥር በተቀመጠው አንቀፅ 27 ንዑስ አንቀፅ () ላይ ምልመላን፣ ጊዜያዊም ሆነ ቋሚ ቅጥርን፣ በቋሚ ስራ ላይ መቀጠልን፣ የሙያድገትን፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ጤናማ የሥራ ሁኔታዎችን ጨምሮ ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ሁሉ አስመልክቶ በአካል ጉዳት ላይ የተመሰረተ ማናቸውም አይነት አድልዎ እንዳይፈፀም ይከለክላል።

የዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ () ደግሞ ከወከባ መጠበቅንና ለቅሬታዎች የመፍትሄ ምላሽ ማግኘትን ጨምሮ እኩል ዋጋ ላለው ሥራ እኩል ዕድሎችንም ሆነ እኩል ክፍያ የማግኘት፣ ደህንነታቸው የተጠበቀና ጤናማ የሥራ ሁኔታዎችን ጨምሮ ከሌሎች ጋር በእኩል ደረጃ ለአካል ጉዳተኞች ትክክለኛና ምቹ የሥራ ሁኔታ የማግኘት መብት መስጠቱን ያትታል።

ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (አይ.ኤል.ኦ) እ.ኤ.አ በ2021 ይፋደረገው መረጃ እንደሚያሳየው በዓለማችን ዕድሜያቸው ለሥራ ከደረሰ ዜጎች 386 ሚሊዮን የሚገመቱት የአካል ጉዳትለባቸው። በአንዳንድ ታዳጊ አገራትም የአካል ጉዳተኞች ሥራ አጥነት እስከ 80 በመቶ ይደርሳል። ይህም የሚያሳየው አሰሪዎች አካል ጉዳተኞችንመቅጠር ፍላጎት እንደሌላቸውናአካል ጉዳተኞች መስራት አይችሉም’ የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መያዛቸውን ነው

አካል ጉዳተኝነት ያልበገራቸው ብርቱዎች

በጽሁፉ መግቢያ የተዋወቅናቸው የ76 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አቶ አለበል ሞላ ገና 13 ዓመት ታዳጊ እያሉ በደረሰባቸው የተሽከርካሪ አደጋ ሁለት እግሮቻቸውን አጥተዋል።

አቶ አለበል አዲስ አበባ ተወልደው ማደጋቸው በተሽከርካሪ ወንበር (ዊልቼር) ድጋፍ ወደ ትምህርት ቤትም ሆነ ወደ ስራ ተመላልሰው ለመማርና ለመስራት የሰጣቸው ዕድል ቢኖርም የከተማዋ የእግረኛም ሆኑ የአስፓልት መንገዶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያላደረጉ፤ ለዊልቼር መንቀሳቀሻ በቂ ቦታ የሌላቸው መሆናቸው እንቅስቃሴያቻውን በእጅጉ አክብዶባቸዋል። ከመኖሪያቸው ወደ ትምህርት ቤትና ወደ ስራ ቦታቸው በዊልቼር በሚመላለሱበት ጊዜ በመንገዱ ወጣገባነት ይገጥማቸው ነበረውን ፈተና እና ያሳለፉት ስቃይ እጅግ ከባድ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ይሁንና አቶ አለበል በርካታ ውጣ ውረዶችና ተግዳሮቶችን አልፈው ትምህርታቸውን በመከታተል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን መያዝ ችለዋል። በመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥረው 25 ዓመታት አገልግለዋል። ሥራ ለመቀጠር አጋጥሟቸው የነበረውን እልህ አስጨራሽ ትግል አሁንም ድረስ በቁጭት ነው የሚያስታውሱት። ያንን ጊዜአስከፊና ተስፋ አስቆራጭ” ሲሉ ይገልፁታል።

በፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 ለአካል ጉዳተኞች የሚጠበቁ የሥራ ሁኔታዎችን በተመለከተ እንደተቀመጠው አካል ጉዳተኞች በቅጥር፣ በደረጃ ዕድገት፣ በዝውውር፣ በድልድል፣ በትምህርትና ሥልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። ማንኛውም የመንግሥት መስሪያ ቤት የሥራ አካባቢው ለአካል ጉዳተኛ ሠራተኞቹ ምቹ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ለሥራ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችንና ቁሳቁሶችን ማሟላትና ስለአጠቃቀማቸው አስፈላጊውን ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ አለበት።

በሌላ በኩል ማንኛውም የመንግሥት መስሪያ ቤት ረዳት ለሚያስፈልገው የአካል ጉዳተኛ የመንግሥት ሠራተኛ ተገቢውን ድጋፍ የሚሰጥ ረዳት እንዲመደብለት የማድረግ ኃላፊነት የተጣለበት ሲሆን፤ በሌሎች ሕጎች ለአካል ጉዳተኞች የተሰጡ መብቶች ለዚህ አዋጅ አፈጻጻም ተግባራዊ እንደሚሆኑ ያስቀምጣል።

ይሁን እንጂ ለአቶ አለበል ይህ የመንግሥትራተኞች አዋጅ በወረቀት ላይ ብቻ የሰፈረ የህልም እንጀራ ነው። “ስራ ለመቀጠር ማስታወቂያ በወጣባቸው የመንግሥትና የግል ተቋማት አካል ጉዳት ከሌለባቸው ጋር ተወዳድሮ ማለፍ ትልቅ ፈተና ነበር፤ ፈተናውን በጥሩ ነጥብ አልፌ እንኳን ለቃለ-መጠይቅ ዊልቸሬን እየገፋሁኝ ስገባ ከጠያቂዎቹ ፊት ላይ ያለውን ስሜት በመረዳት ነበር ስራውን እንደማላገኝ እርግጠኛ የምሆነው’’ይላሉ።

የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁ ከአራት ዓመታት በኋላ በአንድ የመንግሥት ተቋም ውስጥ በጀማሪ ባለሙያነት የመቀጠር ዕድል ማግኘታቸውንና ይህን ዕድል በመጠቀም አካል ጉዳተኝነት ምንም አይነት ስራ ከመስራት ወደኋላ እንደማያስቀር ለማሳየት ጥረት ሲያደርጉቆየታቸውን ይናገራሉ።

ይሁንና እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ሆነ ነገ ሁሉም አካል ጉዳተኞችን የሚመለከትበትን መነፅር መጥረግ እንዳለበት አጽንኦት የሚሰጡት አቶ አለበል በተለይም እውቀትና ችሎታው ኖሯቸው እኩልድል ባለማግኘታቸው በከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ለመታደግ እያንዳንዱ ዜጋ በሰብዓዊነት ስሜት ሊንቀሳቀስ፣ መንግሥትም ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።

አቶ አለበል ያለፉበትን የሕይወት ውጣ ውረድ መንገድ ዛሬም በርካታ አካል ጉዳተኞች ይመላለሱበታል። የ12 ክፍል ተማሪዋ ዓይናለም መክብብ ከእነዚህ መካከል አንዷ ነች። ዓይናለም ስትወለድ ጀምሮ ዓይነስውር ናት።

ዩኒቨርሲቲ ገብታ ሕ የመማር ከፍተኛ ፍላጎት ያላት ዓይናለም ለምን ማጥናት እንደፈለገች ስትጠየቅ “በሀገራችንይነስውራንን ጨምሮ የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸው ዜጎች አካል ጉዳት ከሌለባቸው እኩል የትኛውንም አገልግሎት የማግኘት መብታቸው በአግባቡ ተከብሮ ከፍተኛ በሚባሉ የሥራ ቦታዎች ላይ በኃላፊነት እንዲመጡ ካለኝ ፅኑ ፍላጎት ነው” ትላለች።

ዓይናለም የምትማርበት ትምህርት ቤት ከብሬል አቅርቦት ጀምሮ የተለያዩ ችግሮችሉበት ቢሆንም፤ እርሷ ግን በትምህርቷ ከዓይናማዎች እኩል፤ አንዳንዴም ከእነርሱም በላይ የላቀ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች። ለዚህ ስኬቷምእችላለሁ’’ የሚል ጠንካራ ሥነ-ልቦና እንዲኖራት ወላጆቿ ያሳደሩባትን አዎንታዊ ተጽዕኖ በምክንያትነት ትጠቅሳለች

በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የሚወጡጎች በትክክል አይፈፀሙም የሚለውን ቅሬታ ዓይናለምም ትጋራዋለች። ለምን አይፈፀሙም የሚል ጥያቄ ሲነሳም “ሰ ጆሮ እና ተመልካች ዓይን” የለም ነው ምላሿ። አካል ጉዳተኞች በከፍተኛ የሥራላፊነት ላይ ሆነውገራቸውን እናዝባቸውን እንዲያገለግሉ የሚያግዝ አረንጓዴ መብራት አይታይም።

በፈተና ውስጥም ቢሆን፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ አጥንቼ በጥሩ ውጤት እንደምመረቅና ያሰብኩትን እንደማሳካ እርግጠኛ ነኝ” የምትለው ዓይናለም፤ እንደ አገር ለአካል ጉዳተኞች ያለውን ሁለንተናዊ አመለካከት ማስተካከል በተለይም የሕግ ተፈጻሚነትን ማሻሻል የቅድሚያ ቅድሚያ የስራ ትልሟ ስለመሆኑ ትገልፃለች።

የሕጎችተፈጻሚነት ክፍተት

በኢትዮጵያ ለአካል ጉዳተኞች ያለው አመለካከት የተንሸዋረረ ነው በሚል የሚነሳውን ቅሬታ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይነህ ጉጆም ይስማሙበታል በአገሪቷ አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ የሚወጡጎች በትክክል አካል ጉዳተኞችን እየደገፉለመሆኑ ባሻገር አካል ጉዳተኞችን ብቻ አስመልክቶ የወጣ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩንም አጥብቀው ይተቻሉ።

አካል ጉዳተኞች ለሚያነሷቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ አሰራር መዘርጋትግድ ስለመሆኑ አፅንኦት የሚሰጡት አቶ ዓባይነህ “አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የሚወጡጎችና አሰራሮች በ’እኔ አውቅልሃለሁ’ እሳቤ የወጡና አካል ጉዳተኛውን የማይወክሉ ናቸው” ይላሉ።

በአጠቃላይ በሀገሪቷ አካል ጉዳተኞችን አስመልክተው የሚወጡ ሕጎች ተፈጻሚነታቸው ዝቅተኛ ነው። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት በአካል ጉዳተኛው ቦታ ሆኖ ችግሩን አለመረዳትና የተቆርቋሪነት ስሜትለመኖሩ ነው ሲሉም ያክላሉ።

በኢትዮጵያ ሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 በሀገሪቷ የሚገነቡ ሕንፃዎች ማሟላት ስለሚገባቸው አጠቃላይ ግዴታዎች ያስቀመጠ ሲሆን፤ በአንቀፅ 36 ስር የሚገነቡ ሕንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ሊሆኑ እንደሚገባ አስፍሯል።

የሕንፃ አዋጁ ይውጣ እንጂ አብዛኞቹ የሚገነቡንፃዎች አካል ጉዳተኞችን ያላማከሉ ናቸው። ሕጉ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ እንዲያደርጉ የማያስገድድ በመሆኑንፃ ገንቢዎቹ ስለአካል ጉዳተኞች መብት ግድ እንዳይሰጣቸው አድርጓል።

መንግሥት አካል ጉዳተኞችን በሀገሪቷ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ተሳታፊ ለማድረግ  ጉዳታቸውን ታሳቢ ያደረገ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበትአፅንኦት የሚገልጹት አቶ ዓባይነህ ፌዴሬሽኑ አካል ጉዳተኞች በሀገሪቷ ሁለንተናዊ ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ወጥነት ያለው የአካል ጉዳተኞች እንዲወጣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ጥረት እያደረገ ስለመሆኑ ነው ያስረዱት።

በኢትዮጵያ የሚገነቡንፃዎችና መንገዶች ከዲዛይን ጀምሮ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ማኅበሩ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን እና ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

የዚህ ስምምነት ዋና ዓላማ አዳዲስ የሚገነቡ መንገዶችናንፃዎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ እንዲያደርጉ እንዲሁም ነባር ሕንፃዎችንም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የማድረግ ሁኔታን መፍጠር ነው።

አካል ጉዳተኞች በሀገሪቷ ሁለንተናዊ ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ሁሉንም ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እንደሚያሳድግ የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ ለአብነትም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስራ ውጤታማነት አካል ጉዳተኞች የድርሻቸውን መወጣት እንዲችሉ በንቃት የሚሳተፉበትን ዕድል ማመቻቸት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትላፊ አቶ እያሱ ሰለሞን በመዲናዋ ለዓይነስውራን እና ዊልቼር ለሚጠቀሙ አካል ጉዳተኞች ታስበው የተገነቡ የእግረኛ መንገዶች መኖራቸውን ይናገራሉ። ይሁንና ሁሉም ቦታ ላይ ያሉ መንገዶች የተገነቡት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ተደርገው ነው ማለት ግን አይቻልም። ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ይላሉ

ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አካባቢ መፍጠር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ግዴታ ስለመሆኑ ያነሱት አቶ እያሱ በተለይ የእግረኛን ጨምሮ የመንገድ መሰረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም በአፅንኦት ይገልፃሉ

ቀደም ባለው ጊዜ በተቋማቸው የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከሌሎች የሥራ ዘርፎች ጋር ተቀናጅቶ ይሰራ እንደነበር በማስታወስ ይህም ጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዳያገኝ ከማድረግ ባለፈ አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ የሚሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓል የሚሉት ደግሞ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ግንዛቤ ማስጨበጥ ዴስክላፊ አቶ ሲሳይ ብርሃኑ ናቸው።

አቶ ሲሳይ አክለውም ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ብቻ የሚከታተል የሥራ ክፍል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱን እና በዚህም ለውጦች መምጣታቸውን ይገልጻሉ። ቀደም ባሉት ዓመታት ስለ አካል ጉዳተኞች የነበረው የተዛባ አመለካከት አሁን አሁን የተወሰኑ መሻሻሎችን ቢያሳይም፤ በርካታ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን አልሸሸጉም።

አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ የሚወጡ ሕጎች ተፈጻሚነት ላይ ጉልህ ክፍተቶች አሉ በሚለው አስተያየት አቶ ሲሳይ ይስማማሉ። በተለይ ኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቬንሽንን ተቀብላ ያጸደቀች ቢሆንም፤ ወደ ተግባር ከመቀየር አኳያ በርካታ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። እንደ አቶ ሲሳይ ገለፃ እያንዳንዱ የመንግሥት ተቋም አካል ጉዳተኞችን አካቶ መስራት እንዳለበት በኮንቬንሽኑ ተቀምጧል። ይሁንና በየተቋማቱ ከአመራር እስከ ባለሙያ ድረስ አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ሊያደርግ የሚችል አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ገና ብዙ ቀሪ ስራዎች አሉ።

ለአካል ጉዳተኞች አገልግሎት ከመስጠት አኳያ በርካታ ተቋማት ተደራሽ አይደሉም። በዊልቼር ለሚንቀሳቀሱ፣ ለዓይነስውራን እና መስማት ለተሳናቸው ዜጎች የተቋማት አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ብዙ ሊሰራ ይገባልም ይላሉ።

ጭላንጭሉ ተስፋ…

አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ በአንዳንድጎች ላይ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ድክመቶችን የማረም ጥረት ተጀምራል። ለአብነት በኢትዮጵያ የሚገነቡንፃዎች ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ አለመሆናቸው ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል። ይህን ችግር ለመፍታት የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የሕንፃ አዋጁ እንዲሻሻል በጋራ እየሰራ ነው። በማሻሻያ አዋጁ ላይ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና አስፈላጊውን ግብዓት እንዲጨምሩም ተደርጓል።

አካል ጉዳተኞች ከቀረጥ ነፃ ተሽከርካሪ ማስገባት የሚያስችላቸው መመሪያ ተግባራዊ እንዲሆን ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የአካል ጉዳተኞችን መረጃ የማደራጀት እንዲከናወንና በተሰጣቸው ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። አካል ጉዳተኞች በፌዴራልና በክልል ደረጃ በጉዳት አይነታቸው ተደራጅተውእኩል ዕድል ተጠቃሚነታቸውና ተሳትፏቸው እንዲጨምር ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል። ያም ሆኖ አሁንም አንድ ትልቅ ችግር አለ፤ “በኢትዮጵያ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ከተካሄደ ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ ምን ያህል አካል ጉዳተኞች እንዳሉ ትክክለኛው መረጃ አይታወቅም” ይላሉ ይህም አካል ጉዳተኞችን እንደ ጉዳት አይነታቸው ለይቶ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ከባድ ፈተና ሆኗል።

አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ የሚወጡጎች በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የጉዳዩ ባለቤቶች የሆኑት ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ፤ ራሳቸው አካል ጉዳተኞችም ለመብቶቻቸው መከበር ይበልጥ መታገል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። ይህም ብቻ አይደለም የአካል ጉዳተኞች እኩል ተጠቃሚነት ጉዳይ በአንድ ተቋም ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ድጋፍ ይሻል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም