የአዲስ አበባ አዲስ መልክ

በአህመድ መሀመድ (ኢዜአ)

መግቢያ

ከተሞች የዘመን መስታወቶች ናቸው። የሥልጣኔ መልክና ልክ ማሳያ ጭምር። የመልከ-ብዙ ባሕል፣ ወግና ትውፊት መድመቂያ፣ የሉላዊ እሳቤ መታያ፣ የሥራ እና ሥራ ፈጣሪዎች መናኸሪያ እና የዕድገት መስፈንጠሪያ ናቸው። ብዝሃ የኑሮ ደረጃ ያዝላሉ፤ አዲስ ትውፊት ይወልዳሉ፤ የከተሜዎችን የነገ የጋራ ትዝታ በሕብረት ይቀርጻሉ። ለአያሌ ምዕተ ዓመታት የዓለም ታሪክ ከተሞች ለሥልጣኔ ማማ፣ የባሕል፣ የንግድና የአስተዳደር መልኮች አውድማ ናቸው። ድሮም ሆነ ዘንድሮ የኑሮ መሻትን ለማርካት በሚደረግ ግርግር ይታወቃሉ።

የስነ-ከተማ አጥኚዎች እንደሚሉት ከተሞች የተወጠኑት ወንዝ ተከትለው ነው። በነዋሪዎች ጥግግት፣ በተማከለ አስተዳደር፣ አብያተ መንግሥታት እና አብያተ መቅደሶች በቤተ-መቅደሶቻቸው ይታወቃሉ፡፡ የከተማ ፕላን ባለሙያው አማን አሰፋ (ዶ/ር) ከተሞች በየዘመናቱ የንግድ፣ የኪነ-ጥበብ እና የሃይማኖት ማዕከላት እንዲሁም የሥልጣኔ መሰረት ናቸው።

ለአብነትም በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ኃይል የመነጨው፤ ፋብሪካና የባቡር ሀዲድ የተዘረጋው በከተሞች ነው። ከተሞች በፈጠራ ጥበባቸው የሕዝብ ስበት ማዕከል ሆነዋል። ከድሕረ 20ኛው ክፍለ ዘመን እስከ ዛሬው የዲጂታላይዜሽን አብዮት ዘመንም ከተሞች የአዳዲስ ግኝት፣ የቴክኖሎጂና የዲጂታላይዜሽን አስኳል ሆነው ቀጥለዋል። በዚህም የኢንቨስመንት፣ የፋይናንስ፣ የባሕል እና የዕውቀት ሜዳ ናቸው። ዘመኑን የዋጁ ኪነ ሕንጻዎች፣ መንገዶች እና የትንሿ ዓለም መልክ መገለጫዎችም ናቸው። ከጥንት እስከዛሬ ከተሞችን የዘመን መመልከቻ መስታውቶች እና አሻራ ማንበሪያ ሰሌዳዎች ሊባሉ ይችላል።

አዲስ አበባ እንደ ከተማ

የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤቷ ኢትዮጵያ በጥንተ ታሪክ ገጾቿ የራሷን ከተሞች መፍጠሯ ዕሙን ነው። የከተማ ፕላን ባለሙያው አማን አሰፋ (ዶ/ር)  እንደሚሉት ሞሶፖታሚያ፣ ግብጽ፣ ፋርስ እና መሰል ቀደምት የሥልጣኔ ባለቤቶች እንደነበሩ ሁሉ ኢትዮጵያም አክሱምን መሰል ከተሞች ነበሯት። እስከዛሬዋ አዲስ አበባ ድረስ በየዘመን ሕዳጉ ከተማ የሚሰኙ ማዕከላት ተመስርተዋል።

በ1879 ዓ.ም የተከተመችው የዛሬዋ የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መናኸሪያ፣ የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት። ከባሕር ጠለል በላይ ከ2 ሺህ 300 ሜትር ከፍታ ላይ የምትገኝ፣ 527 ስኲዬር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያላትና አምስት በመቶውን የአገሪቷን ሕዝብ ያቀፈች ግዙፍ ከተማ ነች። የከተሜነት ምጣኔውም በየዓመቱ 3 ነጥብ 7 በመቶ ይጨምራል። ዳሩ የከተማዋን ስፋትና ዕድገት የሚመጥን የከተሜነት መሰረተ ልማት፣ ገጽታ እና የኑሮ ጥራት እንደሚጎድላት ይነሳል። የመዲናዋ ዕምብርት የሚሰኙ በርካታ አካባቢዎች ገጽታ ከዛሬ 70 እና 80 ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር የተራራቀ አለመሆኑም ለዚህ አስረጂ ነው።

በ1920ዎቹ አዲስ አበባን የጎበኘው እንግሊዛዊው አልኸንድሮ ዲል ባዮ(ኮሎኔል) ‘ቀይ አንበሳ’ በተሰኘው ስለ ኢትዮጵያ የሚያትት የጉዞ ማስታወሻው “አዲስ አበባ የገጠር ከተማ ነች፡፡ ከሌሎቹ የአቢሲኒያ ከተሞች አንጻር አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ ዘመናዊ ቤቶችና የመገናኛ አውታሮች መዘርጋት ለዋና ከተማነት አብቅቷታል። ከውጭ ለሚጎበኝ የውጭ ዜጋ ግን ሁኔታዋ ከሌሎች ከተሞች እምብዛም አይለይም” ሲል ገልጿታል፡፡ በተመሳሳይ ዘመን ኢትዮጵያን የጎበኘው ቼካዊው ዜጋ አዶልፍ ፓርላሳክ ‘የሃበሻ ጀብዱ’ (ተጫነ ጆብሬ እንደተረጎመው) በተሰኘው መጽሐፉ፤“መሀል ከተማ ላይ ሁለት ፎቅ የድንጋይና የእንጨት መኖሪያ ቤቶች እና የግሪክ ነጋዴዎች ሱቆች እንዲሁም ሌሎች አውሮፓዊያን መኖሪያ ቤቶች ተሰርተውበት ደመቅመቅ ብሏል”  በማለት የአዲስ አበባን ለጋነት ይተርካል።

የሁለቱ አውሮፓዊያን ትዝብት የሚተርከው የፒያሳን የዘመን መልክ ነው። ከ80 ዓመታት በፊት የነበሩ ትዝብቶች ከበርካታ ትውልድ መተላለፍ በኋላ ዛሬም ቢቃኙት የፒያሳ የከተሜነት መልኳ ምን ያህል ተለውጧል ቢባል ምላሹ ግር ማሰኘቱ አይቀርም። ፒያሳና መሰል ቀደምት መንደሮች ታሪክ፣ ስምና ዕድሜቸውን የሚመጥን እድሳት አልተደረገላቸውም። ከጌጥነት ይልቅ ማኅበራዊ ጠንቅነታቸው የሚያደሉ ነታባ መንደሮች ሆነዋል። ጣሪያና ግድግዳቸው፣ በርና መስኮታቸው የተቦዳደሰ፣ ዛኒጋባዎች የተዛዘሉ፣ መንገዳቸው የፈራረሰ ለዓይን የሚቀፉ፣ ለአፍንጫ የሚረብሹ ስሜቶች ነበሩባቸው።

ልከኞቹ የአዲስ ኮሪደሮች

ኮሎኔል አልኸንድሮ ዲል ባዮ “የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት ለጅቦች እና ለጥንብ አንሳ አሞራዎች የተተወ ይመስላል፡፡ እነኚህ አውሬዎች በየሜዳው የወደቁትን እና የተጣሉትን ቆሻሻዎች በመመገብ የከተማዋን ንጽህና ይቆጣጠራሉ፡፡ በግልጽ በሕዝብ መተላለፊያዎች እና መንገዶች ላይ የወደቀውን ለመጋራት ሲጣሉና ሲናከሱ ይታያሉ” በማለት ነበር ትዝብቱን ያሰፈረው። ይህ ስሜት ለዚህ ዘመኗ አዲስ አበቤዎች ለአፍንጫና ለዓይናቸው የቀረበ ዕውነት ሆኖ ኖሯል፡፡

አዲስ አበባን ከመልከ ብዙ ጉድፎቿ በማንጻት ስምና ክብሯን የሚመጥን ገጽታ ማላበስ ያለሙ ፕሮጀክቶች አሁን ተግባራዊ መሆን ጀምረዋል።

የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት አንዱ ነው። የመዲናዋን ስድስት ክፍለ ከተሞች የሚያካልለው የኮሪደር ልማቱ ለአዲስ አበባ ውበትም፣ ወረትም እንደሚሆን ትልቅ ተስፋ ተሰንቆበታል። በፕሮጀክቱ ከተጀመሩ ኮሪደሮች መካከል አምስቱ ግንባታቸው እየተጠናቀቀ ነው። 

የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ገጽታዋን ማስዋብ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነዋሪዎች ለኑሮ የምትመች የጸዳችና የተዋበች መዲና ማድረግን ያለመ ነው። አምስቱ ኮሪደሮች ከፒያሳ-አድዋ ድል መታሰቢያ- አራት ኪሎ፣ ከአራት ኪሎ አደባባይ-መገናኛ፣ ከሜክሲኮ-ሳር ቤት በጎተራ ወሎ ሰፈር፣ ከአራት ኪሎ-መስቀል አደባባይ- ቦሌ ድልድይ እንዲሁም ከመገናኛ እስከ አዲስ አፍሪካ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሲሆኑ 48 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ይሸፍናሉ፡፡

ኮሪደር ልማቱ አይነተ ብዙ ልማቶችን ያቅፋል። የተሽከርካሪ እና የእግረኛ መንገዶችን በማስፋትና ምቹ በማድረግ ለትራፊክ ፍሰት እየተመቻቹ ነው። ጎዳናዎች በዘመናዊ የኤሌክትሪክ መብራት እና የመንገድ ዳር አረንጓዴ ልማት ተውበዋል። ዘፈቀዳዊ ፍሳሽ አወጋገድ ዘመኑን በዋጀ አግባብ በሥርዓት ይተካል። ለዓይን የማይመቹ ሕንፃ ግንባታዎች ተጠግነው ሳቢና ማራኪ ውበት እየተላበሱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ዘላቂነት ባለው አግባብ ለነዋሪዎቿ ኑሮ የተመቸችና የላቀች፣ ውብ መኖሪያ ከተማ የማድረግ ዘመን ተሻጋሪ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው ነበር።

የከተማ ፕላን ባለሙያው አማን (ዶ/ር)  የታቀፉ ሰፈሮች ለኑሮም ሆነ ለንግድ አገልግሎት የተጨናነቁ፣ ለሥራም ሆነ ለኑሮ የማይመቹ፣ በጽዳት አገልግሎት ዕጦት የታወኩ መንደሮች በኮሪደር ልማቱ ታቅፈው ወደ ልማት እንዲገቡ መደረጉን ትክክለኛ ውሳኔ ይሉታል።

በአስር ዓመት የልማት ዕቅዱ ውስጥ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፤ አሳታፊና ዘላቂ ልማትን ታሳቢ ያደረጉ ከተሞችን መገንባት ትኩረት ተሰጥቶታል። ለኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ አካባቢያዊና ሥርዓተ ምህዳር ተጽዕኖዎች የማይበገሩ ከተሞችን ማልማት ላይ ያተኮረ ነው። ይኸውም የመሬትና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ማሻሻል፣ የተቀናጀ መሠረተ ልማትና የአገልግሎት አቅርቦት ማሳለጥ፣ የጽዳት እና የአረንጓዴ ልማት ሽፋንን ማሳደግ በጥቅሉ ለኑሮ ምቹና ተስማሚ ማድረግ ነው። የኮሪደር ልማቱ ከዚህ ዕቅድ ጋር የተጣጣመ ነው። ከትራፊክ ፍሰት እና ውበቱ ባሻገር ጤናማነትን ጨምሮ ተጓዳኝ ማኅበራዊ አበርክቶ እንዲኖራቸው ያስችላል።

ዘላቂ ክትመት

ዘላቂ ክትመት ማለት ለአካባቢ ተስማሚ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያላቸው ከተሞች መፍጠርን ያነገበ ሰፊ ጽንሰ-ሃሳብ መሆኑን መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ የከተማ ልማት ዓላማ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ ሐብቶች እና ሥነ-ምህዳሮችን በመጠበቅ የአሁኑን እና የመጪውን ትውልድ ፍላጎቶች ሊያሟላ የሚያስችል ነው፡፡ የዘላቂ ክትመት እንቅስቃሴ ከተሞች የሥራ ዕድልን በስፋት እንዲፈጥሩ በማድረግ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት እንዲሁም የብልጽግና ጉዞን ለማፋጠን ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል ነው።

በተጨማሪም ከተሞችን ማልማት ለሥራና ለኑሮ ሳቢ በማድረግ ለመዋቅራዊ ሽግግሩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ከዚህ አኳያ በአስር ዓመት የልማት ዕቅዱ፤ 'ለልማት የሚሆኑ የመሬት አቅርቦቶችን ማሻሻልና በመልሶ ማልማት ሂደት ዘላቂ የከተማ ልማትን ማረጋገጥ፣ ከተሞችን በዙሪያቸው ካለ ልማት ጋር በማስተሳሰርና ከሌሎች የልማት ማዕከላት ጋር በማቆራኘት ምርታማነትን ማሳደግ፣ የመንግሥት እና የግል አጋርነትን በመጠቀም የቤቶችን ዕጥረት መፍታት፣ ያልተማከለ የከተማ ልማትን ማጠናከር እንዲሁም የከተሞችን የመሠረተ ልማት ፍላጎት ማሟላት ይገኙበታል’።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት በመንግሥት የሚደረገው ክትትል እና ቁጥጥር አናሳ መሆን እና የኅብረተሰቡ ቸልተኝነት ከተማዋን በሚገባት መንገድ እንዳታድግ አድርጓት ቆይቷል ነው ያሉት። በመዲናዋ በየትኛውም አካባቢ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚቀጠሉት ላስቲኮች እና ቆርቆሮዎች፣ ሥርዓት በሌለው መንገድ እና ዲዛይን በሌለበት ሁኔታ የሚቀጠሉ የኤሌክትሪክ መብራቶች እና የውሃ አገልግሎቶች ለከተማዋ አስቸጋሪ ሆነው ቆይተዋል።

ከተሞች የስራ ዕድል የሚፈጠርባቸው፣ ፈጠራ እና ግኝቶች የሚያድጉባቸው፣ የካፒታል ዝውውር የሚደረግባቸው ልዩ ማዕከላት ናቸው። የከተማ ፕላን ባለሙያው አማን አሰፋ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ‘ከተሞች ሰው እንደሚተነፍሰው ሁሉ የመተንፈሻ ሥርዓት ሊኖራቸው ይገባል። የሰው ልጅ በሕይወት ለመቆየት የደም ዝውውር እንደሚያስፈልገው ሁሉ ከተሞችም እንዲያድጉ የዘመነ የመብራት፣ የመንገድ፣ የኢንተርኔት፣ የውሃ መስመር፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት ሊኖራቸው ይገባል።’ ከተሞች መሰረተ-ልማታቸው ሲሟላ የኢኮኖሚ ዕድገት ይፈጥራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉት የልማት ኮሪደሮች ከጊዜው ጋር የሚራመዱ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ የሚከሰቱ የዓለም የፈጠራ ውጤቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ ቀጣይነት ያለው መሠረተ ልማት በመፍጠር የነዋሪዎቿን እና የአካባቢውን ደህንነት የሚደግፉ ዘላቂ መሠረተ ልማቶች ላይ ትኩረት ማድረጉን ያነሳሉ። በተለይ የከተማዋን መጨናነቅ እና የአዕምሮ ማደሻ ቦታ ጥበት በሚፈታ ሁኔታ የመዝናኛ፣ የብስክሌት መንቀሳቀሻ መንገድ እና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ምቹ የሆኑ የእግረኛ መንገዶችን ያካተቱ ናቸው ይላሉ።

ከዚህ ቀደም ሲከናወኑ የቆዩ ግንባታዎች፣ የመሰረተ-ልማት ሥራዎች በተቋማት አለመናበብ ምክንያት በተፈለገው ጊዜና ጥራት ከመጠናቀቅ አኳያ ችግር ሲገጥማቸው ቆይቷል። በዚህ ሳቢያም በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ሲያስነሱ የኖሩ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። አንዱ ተቋም ገንብቶ የጨረሰውን ሌላኛው ሲያፈርስ፣ አንድ እና ሁለት ዓመት ሳያገለግሉ መልሰው ሲፈርሱ የኖሩ ፕሮጀክቶች በርካቶች ናቸው። ይህም ቀደም ሲል የነበሩ ግንባታዎች ዘላቂ ክትመት እንደ ግብ ላለመቆጠሩ ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ነው። በአሁኑ የልማት ኮሪደር የሥራ ስምሪት ወቅት እነዚህ እና መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ ተቋማት በመናበብ እና ኃላፊነታቸውን ወስደው በመተግበር ላይ ይገኛሉ። የኮሪደር ልማቱ የመዲናይቱን ገጽታ በተሻለ መልኩ የሚቀይር መሆኑን የሚገልጹት አቶ ጃንጥራር፤ በጥናት ላይ ተመስርቶ የተጀመረና የተለያዩ አካላት በቅንጅት የሚመሩት መሆኑን በዋቢነት ጠቅሰዋል።

በኮሪደር ልማቱ የመንገድ፣ የመብራት፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የውሃ እና መሰል ተቋማት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛሉ። በመሬት ውስጥ የሚሰሩ ሥራዎች እና አጠቃላይ የመሰረት ሥራ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡ የጎርፍ ማስወገጃ ቱቦዎች ዝርጋታ፣ የመብራት እንዲሁም የአፈር ሙሌት እና የኮንክሪት ሥራዎችም በአግባቡ እየተከናወኑ ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሪደር ልማት የኤሌክትሪክ መስመር ማዛወር እና መልሶ ግንባታ ሥራ አጠናቆ ለደንበኞች አገልግሎት መስጠት መጀመሩን እና በመስመር ማዛወር ሥራው ወቅት የልማት ተነሺ ለነበሩ 2 ሺህ 700 ደንበኞች አዲስ ኃይል የማገናኘት ስራ እንደተከናወነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያሳያል፡፡

አዲስ የሥራ መንፈስ

ለረጅም ጊዜያት መደበኛ ባልሆነ መልኩ በመስፈር የተጎሳቆለ የአኗኗር ዘይቤ እየተከተለ የሚገኘውን ነዋሪ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል፣ እያደገና ከተማዋን እያጨናነቀ ለመጣው የትራፊክ ውጥረት መፍትሔ መንገዶችን ለማስፋት፣ ለእግረኞች ሰፋፊ መንገዶችን ለማበጀት፣ የቅርስ ቦታዎችን ለመጠገን ብሎም ሕንፃዎችን በከተማዋ የሕንፃ ሥነ-ውበት ደረጃ ልክ ለማድረስ ሠራተኞች እዚህም እዚያም በትጋት እና በፍጥነት እየሰሩ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን እየተለመደ የመጣ አዲስ የሥራ ባሕል ተፈጥሯል። 24/7 ተሰርተው ያለቁ ፕሮጀክቶች ለምስክርነት የቆሙ ህያው ሃውልቶች ናቸው። በተለይም በመንግሥት የተገነቡት አዳዲስ ፓርኮች፣ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም፣ የተለያዩ የተሽከርካሪ እና የእግረኛ መንገዶች ፕሮጀክቶች በትኩረት ከተሰሩ በፍጥነት መጠናቀቅ እንደሚችሉ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ይህ የኮሪደር ልማት በተያዘለት አጭር የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ማዕከል ያሉ አመራሮች ከሠራተኞች ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን እና ግንባታው በስኬት እየተከናወነ አንደሆነ ምክትል ከንቲባው አቶ ጃንጥራር ዓባይ ገልጸዋል። በኮሪደር ልማቱ የሚካሄዱት የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የእግረኛና የተሽከርካሪ መንገዶች፣ የታክሲና የአውቶቡስ መናኸሪያዎች ከተማዋን በሚመጥን መልኩ እየተገነቡ ይገኛሉ። በአሁኑ ወቅት የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ፍጥነትን ከውበት አቀናጅተው ሁሉንም ኮሪደሮች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ በግስጋሴ ላይ ናቸው።

የኮሪደር ልማቱ ሠራተኞች 24/7 በትጋት ላይ ናቸው፡፡ ያላቸው ጊዜ ዛሬ ብቻ ሳይሆን 'አሁን' ብቻ ይመስላል፡፡ ለአፍታ ቆሞ የሚታይ ሠራተኛ አይስተዋልም፡፡ ሁሉም እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡ ፕሮጀክትን በጊዜው እና በጥራት ከማድረስ አኳያ ይነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሆን በሚችል መልኩ ሌት ከቀን በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እየተስተዋለ ያለው አዲስ የሥራ ባሕል ማቆጥቆጥ በመላው አገራችን ሊቀዳ እና ሊባዛ የሚገባው መሆኑን ያስገነዘቡት፡፡ አመራሮች ሥራው የደረሰበትን ደረጃ በየዕለቱ እንደሚከታተሉ እና ሠራተኞችም ሌሊቱን ሙሉ ሥራ ላይ ሆነው መታዘባቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያን ዕድገት እውን ለማድረግ ይህ መንገድ ብቸኛው አማራጭ ነው፤ በሣምንት አምስት ቀን፣ በቀን ስምንት ሠዓት ብቻ በመስራት ኢትዮጵያን የሚያህል አገር መለወጥ አይቻልም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም መንግሥት ‘የገጠር መንግሥት ነኝ፣ ከተማው አይመለከተኝም’ ሲል የኖረው ከተማ መምራት ከባድ በመሆኑ ነው፤ ይሁን እንጂ አሁን በተጀመረው ስኬታማ ጉዞ ‘እኛም ከተማ መምራት እንደምንችል ያሳየንበት፤ ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ለማዛመት የሚያስችል ልምድ እና እውቀት የተገኘበት አጋጣሚ ነው ብለዋል።

ከውበት ባሻገር

ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት የሰዎች ወደ ከተሞች የሚደረግ የጉዞ ፍላጎት በመጨመር ላይ ይገኛል። ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ መንገደኞች ልዩ የሆኑ የባሕል፣ የታሪክ እና የመዝናኛ ትዕይንቶችን ለማየት ወደ ዓለም ከተሞች ይጎርፋሉ።

የከተማ ቱሪዝም ዕድገት የጉዞ እና የከተሞችን ልምድ ለውጦታል። ይህ አዝማሚያ እየተሻሻለ ሲመጣ የከተማ ቱሪዝም መንገደኞችንም ሆነ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ በከተማ ቱሪዝም የሚቀርቡትን ዕድሎች ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ለዜጋው ብሎም ለቀጣዩ ትውልድ የተሻሉ፣ የሚያምሩ እና ወጥነት ያላቸውን ከተሞች መፍጠር እንደሚቻል የዘርፉ ምሁራን በጥናቶቻቸው ያትታሉ።

የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) እንደገለጸው ባለፉት አስርት ዓመታት የከተማ ቱሪዝም በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። እ.አ.አ በ2019፤ በከተሞች ውስጥ የሚገኙ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻዎች 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በሚሆን ድግግሞሽ ተጎብኝተዋል። እነዚህ የከተማ መዳረሻዎች ከጠቅላላው የዓለም አቀፍ የቱሪዝም ፍሰት ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነውን ይሸፍናሉ። የከተማ ቱሪዝም በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት በአማካይ ከ5 እስከ 6 በመቶ በየዓመቱ እንደሚያድግ ይገመታል።

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ የዘመን ስሌት በ2021 በድምሩ 518 ሺህ ቱሪስቶችን በማስመዝገብ ከዓለም በ67ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ወርልድ ዴታ አስነብቧል። በዚሁ ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ብቻ 2 ነጥብ 60 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች። ይህም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 2 ነጥብ 1 በመቶውን ይሸፍናል። እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ የዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻዎች 31 በመቶ ድርሻ ይዟል።

አዲስ አበባ 138 ዓመታትን ያስቆጠረች ጥንታዊት ከተማ ነች፡፡ ባሳለፈችው የዕድገት ጎዳና፣ በጠረገችው የልማት ትልም ሳቢያ በርካታ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ እንዲሁም ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት ሆናለች፡፡ በተጨማሪም አዲስ አበባ የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች፣ ቆንስላዎችና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ መቀመጫ ድንቅ እና ውብ ከተማ ብትሆንም እንደ ዕድሜዋ ያልዘመነች፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ ያልሆነች ከተማ እየተባለች ትተቻለች፡፡ በዚህ ሳቢያ ቱሪስቶች እንደ መሸጋገሪያ እንጂ እንደ መዳረሻ ሳይቆጥሯት ለረጅም ጊዜ  የቱሪዝም ባይተዋር ሆና ከርማለች፡፡

ቱሪስቶች ወደ ሌሎቹ የአገሪቷ የቱሪስት መዳረሻዎች ሲያልፉ ሆቴሎቿን ለማረፊያነት ቢጠቀሙም፣ ምግቦቿን ለመሰንበት ቢቀማምሱም እሷነቷን ፈልጎ የሚመጣ ቱሪስት የላትም ሲሉ አስጎብኚ ድርጅቶች ጭንቀታቸውን ሲገልጹ ከራርመዋል፡፡ ይህም ለሥራቸው ውጤታማነት እና ቅልጥፍና እንከን እንደፈጠረባቸው ሲያስረዱ ይደመጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ በቅርቡ ከተማዋን ለማዘመን፤ ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ እየተሰራ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ከተማዋ ካንቀላፋችበት እንድትነቃ፣ ማለፊያ ብቻ ሳትሆን ማረፊያ እንደሚያደርጋት ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

አዲስ አበባ አሁን ጎዳናዎቿን ገላልጣ፣ በፓርኮቿ፣ በሙዚየሞቿ እና በምቹ ጎዳናዎቿ ለሚመለከቷት ሀሴት የምትፈጥር አዲስ አበባ ሆናለች። በጅምር ላይ ያሉት የልማት ኮሪደሮች ሲጠናቀቁም አዲስ ውበት፣ አዲስ ሕይወት እንደምትፈጥር ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ መንግሥታዊ እንግዶች ወደ መዲናይቱ ሲመጡ፤ እንደ መንግሥት ለአንድ ሠዓት እንኳን ከሸራተን ውጭ እንዲያዩ እና እንዲጎበኙ የሚያስችል መዳረሻ እንዳልነበረ አንስተው፤ አሁን በመዲናዋ በሁለት እና ሦስት ቀን ተጎብኝተው የማያልቁ መዳረሻዎች መኖራቸውን ነው የገለጹት።

የመልሶ ግንባታው አንዱ ገጽታ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስፋት፣ የሕዝብ መገልገያ ቦታዎችን ማሻሻልን ያለመ ጭምር ነው። በከተማዋ የተገነቡት ፓርኮች፣ የታዳጊዎች መዝናኛ ቦታዎች፣ የስፖርት መጫወቻ ሜዳዎች እና ሌሎች የጋራ መጠቀሚያ ስፍራዎች በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ነዋሪዎች ማኅበረሰባዊ እርካታ መፍጠር ያስቻሉ ናቸው። ይህም የከተማዋን ውበት ከማሻሻል ባለፈ ማኅበራዊ መስተጋብርና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሚያበረታታ ነው።

አዲስ አበባ ውብ እና ፅዱ ከሆነች፤ የቱሪዝም ኮንፈረንስ መቀመጫነቷ ይቀጥላል። እንጦጦን ያለማችው አዲስ አበባ፤ ሸገር ፓርክን፣ አንድነት ፓርክን፣ አድዋ ሙዚየምን ለውበቷ ተጨማሪ ጌጥ ያደረገችው አዲስ አበባ፤ የልማት ኮሪደሮቿን ስታጠናቅቅ አብዛኞቹ የልማት እንቅስቃሴዎች የልኬት ደረጃቸውን የጠበቁ እንደሚሆኑ አቶ ጃንጥራር አመላክተዋል። ቱሪስቶች በከተማዋ እንዲቆዩ የሚያስችል ዕድል ይፈጠራል፤ በዚህም የነዋሪው የኑሮ ደረጃ የተቃና መስመር ይይዛል።

ለቱሪስት መዳረሻነት የሚሆኑ በርካታ ታሪካዊ እና ሰው ሰራሽ ሐብቶችን የያዘችው አዲስ አበባ፤ በተለይም ታሪካዊ ቦታዎች፣ ቴአትር ቤቶች እና ሙዚየሞች፣ ሆቴሎች፣ የእንግዳ ማረፊያዎች እንዲሁም የተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎችን በጉያዋ አቅፋለች። ይሁን እንጂ እነዚህ ብቻቸውን የጎብኚዎችን ቀልብ አይስቡም። ንጹህ እና በቂ የትራንስፖርት መንገዶች፣ ምቹ እና ውብ የእግረኛ ጎዳናዎች ከሌሏት የቱሪዝም ፍሰቱ ፈተና እንጂ ‘መና’ ሊወርድለት አይችልም። ጥራት ያለው መሰረተ ልማት ለቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል። ይሁን እንጂ አዲስ አበባ ለእዚህ ሳትታደል ለረጅም ጊዜያት ቆይታለች። ምቹ ያልሆኑት መንገዶቿ፣ የቆሸሹት የጎዳና መልኮቿ ዓይንም ልብም መሳብ ሳይችሉ ቀርተዋል።

አሁን ይህን መልኳን ለመቀየር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የቱሪዝም ዕድገቱንም እያፋጠኑት ይገኛሉ። ኢትዮጵያ እምብዛም ተጠቃሚ ያልሆነችበት የአገር ውስጥ ቱሪስት መፍጠር መነቃቃት እያሳየ ነው። የከተማዋ አስተዳደር የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን፤ ባለፉት አሥር ወራት ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮችን መጎብኘታቸውን ገልጿል። በቅርቡ በተሰሩ እና በተጠናቀቁ ውስን ሐብቶች ከ800 ሺህ በላይ የአገር ውስጥ ቱሪስት መፍጠር ከተቻለ፤ የልማት ኮሪደሮቹ ሲጠናቀቁ ከአገር ውስጥ ባሻገር አሃዙ ከፍ ያለ የውጭ አገር ጎብኚ መፍጠር እንደሚችሉ ይታመናል።

አዲስ አበባ ከጄኔቫ እና ኒው ዮርክ ቀጥላ ሦስተኛዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል ነች። ከ130 በላይ ኤምባሲዎች፣ የበርካታ አገራት ቆንጽላ ጽ/ቤቶች የሚገኙባት፣ እንደ አፍሪካ ኅብረት፣ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን፣ ኢጋድ ዋና መስሪያ ቤቶቻቸውን ያሳረፉባት ከተማ መሆኗን የሚገልጹት የከተማ ፕላን ባለሙያው አማን አሰፋ (ዶ/ር)፤ ይሁን እንጂ መዲናዋ እነዚህን ሁሉ ዕድሎች በጉያዋ ብትይዝም ከቱሪዝም የምታገኘው ገቢ እምብዛም ነው ይላሉ። ይሁንና አሁን የቆሸሹ የነበሩ ቦታዎች ለምተው ማረፊያ ስፍራዎች እየሆኑ፤ በእነዚህ አካባቢዎችም የከተማ ጽንሰ-ሃሳብ እየተፈጠረ መምጣቱን ያብራራሉ።

'በሁሉም፣ ከሁሉም እና የሁሉም'

አካታች ከተሞችን መገንባት በዘላቂ ክትመት ውስጥ ቁልፍ ከሆኑ መርሆዎች አንዱ የሆነውን ማኅበራዊ ውህደት እና ፍትሃዊነትን ያመጣል። ይህም ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖሪያ ቤት፣ የጤና እንክብካቤ፣ ትምህርት እና የሕዝብ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ ከዚህ አኳያ በኮሪደር ልማቱ እንደ ግብ የተወሰደው ምቹ ከባቢዎች በመፍጠር እና በማሻሻል የገቢ አለመመጣጠንን እና ሰፊ የማኅበራዊ ልዩነቶችን የሚፈቱ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ ሁሉም ነዋሪዎች የአገርን እንዲሁም የዜጎችን ሕይወት በሚቀይሩ የኢኮኖሚ ልማቶች ውስጥ እንዲሳተፉ ዕድሎችን በመፍጠር፣ የባለቤትነት ስሜት እና የኅብረተሰቡን አንድነት ማጎልበት የሚያስችሉ ናቸው።

በተጨማሪም ለተለያዩ ባሕሎች፣ የአስተሳሰብ ዳራዎች እና ማንነቶች አካታች እንዲሆኑ የሚያስችል ነው፡፡ የኮሪደር ልማቱ የመድብለ ባሕላዊ ዝግጅቶችን ለመደገፍ፣ ባሕላዊ ውይይቶችን ለማስተዋወቅ እና የሁሉንም ማኅበረሰብ ባለቤትነት በማግዘፍ ብዝሃነት እና ውህደትን የሚያዳብሩ ይሆናሉ፡፡ አካታች የሕዝብ ቦታዎችን፣ የባሕል ተቋማት እና የማኅበረሰብ ማዕከላትን መፍጠር ነዋሪዎች እንዲገናኙ፣ እንዲማማሩ እና እርስ በእርስ እንዲተሳሰቡ ዕድሎችን ያሰፋል። ከተሞች ብዝሃነትን በማክበር  የሁሉንም ነዋሪዎች ሕይወት የሚያበለጽግ የበለጠ ንቁ እና የተቀናጀ ማኅበራዊ ትስስር መፍጠር ይችላሉ።

የእግረኛ መንገድ ባለመኖሩ በየቀኑ ዜጎችን በትራፊክ አደጋ ማጣት የተለመደ ነው። በአዲስ አበባ እ.አ.አ ከ2018-2020 ብቻ፤ 8 ሺህ 458 የመንገድ ትራፊክ አደጋዎች መመዝገባቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ከእነዚህ አደጋዎች መካከል 1 ሺህ 274 አደጋዎች ዜጎችን ለሕልፈት ሲዳርጉ፣ 7 ሺህ 184 አደጋዎች ደግሞ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት አድርሰዋል።

ነገን የሚመሩ ሕጻናት፣ የአገር ተስፋ የሆኑ ልጆች፣ ባለ ራዕይ ወጣቶች፣ በካበተ ልምዳቸው አገር የሚያንጹ ጎልማሶች እና አዛውንቶችን በየቀኑ በዚህ አስከፊ አደጋ እናጣቸዋለን። ለአደጋው በከፍተኛ ደረጃ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው ምቹ የእግረኛ መንገድ እና መተላለፊያ አለመኖሩ መሆኑን የወርልድ ባንክ ቡድን አባል የሆነው ዓለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት ተቋም (GRSF) ገልጿል።

በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ ባለው የኮሪደር ልማት በአግባቡ እየተሰሩ ያሉ ምቹ እና አካታች የእግረኛ መንገዶች፤ ለአገር የሚበጁ ዜጎችን የመታደግ ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ እሙን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ይህንን በተመለከተ ባነሱት ሃሳብ፤ “በየቀኑ ከምናጣቸው ወገኖች አንጻር፤ ለዚህ የእግረኛ መንገድ የምናወጣው ወጪ እና ድካም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” ሲሉ የእግረኛ መንገዱን በአካታችነት መገንባት የሰው ሕይወት ማዳን መሆኑን አመላክተዋል።

በአጠቃላይ የኮሪደር ልማት ሥራው ብዙ ትምህርት የተወሰደበት፣ ማድረግ እንደሚቻል የታየበት፣ የኅብረተሰቡ የልማት ጥማት እና ተባባሪነት የታየበት፣ ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች፣ በራሷ ሐብት አገር መቀየር የሚያስችል አቅም እንዳላት የታየበት አጋጣሚ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

አሳታፊነት

የማኅበረሰብ ተሳትፎ የማንኛውም የከተማ ልማት ፕሮጀክት ወሳኝ ገጽታ መሆኑ ይታመናል። በተለይ አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ መልክ ያላት አድርጎ ለመገንባት የየአካባቢዋ ነዋሪዎች ፍላጎቶች ቅድሚያ ግምት ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ኅብረተሰቡን በዕቅድ እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ ማሳተፍ አስፈላጊ ነው።

በመሆኑም የልማት ኮሪደር ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከነዋሪዎች ጋር ምክክር መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ መረጃ ይጠቁማል። በተለይም በመንግሥት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ለነበሩ ነዋሪዎች ፅዱ እና ምቹ የሆኑ የመኖሪያ ቤቶች ተገንብተው መተላለፋቸውን፣ የንግድና የመስሪያ ቦታ ለነበራቸው ነዋሪዎች በተገቢ ቦታ የተሻለ የንግድ ቦታ እንዲሁም የግል ይዞታ ለነበራቸው ነዋሪዎች ካሳ እና ምትክ ቦታ ተሰጥቷል። የልማት ኮሪደሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በሙሉ የተነሱ ሲሆን፤ ለሁሉም ምትክ መኖሪያ ተሰጥቷቸዋል። ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ አንድም መኖሪያ ቤት ሳይረከብ የወጣ ነዋሪ አለመኖሩን ነው የገለጹት። 

በመልሶ ማልማት ውስጥ፤ በአካባቢው የነበሩ ነዋሪዎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቻቸው በማይጎዳበት መልኩ ወደ ሌላ አካባቢ ማዘዋወር ውስብስብ እና ጥንቃቄ የሚጠይቅ ክስተት ነው፤ ከተነሺ ነዋሪዎች ጋር ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ፣ ምክክር እና ቅንጅት ይጠይቃል። እንደ ልማት ኮሪደር ያለ መጠነ ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ፕሮጀክት በሚከናወንበት ጊዜ በለውጥ የሚነሱ ግለሰቦች እና ቤተሰቦች ደህንነትና መብት ቅድሚያ ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበት የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ በዚህ የግምገማ ሂደት ውስጥ የኅብረተሰቡ አባላት፣ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት ድምፃቸውን፣ ስጋታቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን ከግምት በማስገባት መከናወኑን አስረድተዋል።

የልማት ተነሺዎች ወደ ሌላ ስፍራ በሚዘዋወሩበት ጊዜ አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝ እና ተደራሽ የቤት አማራጮች ከመቅረባቸው በተጨማሪ ንብረቶቻቸውን ወደ አዲሱ መኖሪያቸው ማጓጓዣ፣ የገንዘብ ድጋፍ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶቻቸው እንዳይቋረጡ፣ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ የትምህርት አገልግሎት እንዳያጡ፣ ነዋሪዎች በአዲስ ማኅበረሰብ ውስጥ ሕይወታቸውን እንዲገነቡ በሚያስችል መልኩ መከናወኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።

አካታች እና ቀጣይነት ያለው ሁለገብ ከተማ ለመገንባት ከአስተዳደራዊ ሥራ በተጓዳኝ የሁሉንም ነዋሪዎች ደህንነት እና ክብር ማስቀደም አስፈላጊ ነው። ነዋሪዎች ፍላጎቶቻቸው እና ስጋቶቻቸው በልማት ሂደት ውስጥ እንዲፈቱ ኅብረተሰቡን ማሳተፍ ግዴታም ጭምር ይሆናል። በተለይም ማኅበረሰቡ በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ ሲሳተፍ በአካባቢው በሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል።

በልማት ኮሪደር ሥራዎች ውስጥ ኅብረተሰቡ የልማቱ አጋር መሆኑን አሳይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዳሉት፤ “እነዚህ ሁሉ የልማት ሥራዎች ሲሰሩ ኅብረተሰቡ ቆሞ የሚመለከተው፣ ሱቁ ሳይዘጋበት፣ ጥቅሙ ሳይነካበት ቀርቶ አይደለም። ይልቁንስ እየተሠራ ያለው ሥራ የለበጠ ሳይሆን ትልቅ መሆኑን በመረዳቱ ነው” ብለዋል።

ከራስ ለራስ የተሰጠ ስጦታ

መሠረተ ልማት የአንድን ከተማ ዕድገትና ስኬት በመቅረጽ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ከተሞች እንደ አዲስ በሚገነቡበት ጊዜ የመሠረተ ልማት አውታሮች የረጅም ጊዜ ዘላቂነት ያላቸው እንዲሆኑ እና ከተሜነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆን እንዳለባቸው አማን አሰፋ (ዶ/ር) ይናገራሉ። የከተማ ሕይወት የጀርባ አጥንት የሆኑት የመጓጓዣ ሥርዓቶች፣ የሕዝብ መገልገያዎች እና የመገናኛ አውታሮች በመሰረተ-ልማት ዝርጋታ ውስጥ መካተት እንዳለባቸውም እንዲሁ።

ከሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች የተሻለ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ምህዳራዊ ጥቅሞችን በመሻት የሚመጣው ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በማደግ ላይ ይገኛል። በመሆኑም እያደገ የሚሄደውን የሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት መሠረተ ልማትን ማሻሻል፣ ማስፋፋት እና በየጊዜው ከከተማ ዕድገት ጋር እየፈጠነ ያለውን የቴክኖሎጂ ዝማኔ መለዋወጥ የመዲናዋን ቀጣይ ስኬት ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። የኮሪደር ልማቱ እነዚህን ሁሉ ፍላጎቶች ሊያሟላ በሚችል መልኩ በመከናወን ላይ ይገኛል።

የትራፊክ መጨናነቅን ለማቃለል፣ ዘላቂነት ያለው እንቅስቃሴ ለማስፋፋት እና በከተማ ውስጥ ያለውን መስተጋብር ለማጎልበት የትራንስፖርት ሥርዓቶችን ማሻሻል ወሳኝ መሆኑን የሚገልጹት አማን አሰፋ (ዶ/ር)፤ በሕዝብ ማመላለሻ፣ በብስክሌት መንገድ እና ለእግረኛ ተስማሚ መሠረተ ልማት ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የነዋሪዎችን አጠቃላይ የሕይወት ጥራት ለማሻሻል እንደሚያግዝ ያብራራሉ።

ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይም፤ አስተማማኝ እና ቀልጣፋ የፍጆታ አገልግሎቶችን እንደ ውሃ፣ ኤሌክትሪክ እና የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት መዘመን ለአንድ ከተማ የዕለት ተዕለት ተግባር አስፈላጊ በመሆኑ የኮሪደር ልማቱ እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎች በሚገባ ይመልሳል ብለዋል።

ከተሞች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ዕድገትን የሚያመቻቹ መሆን አለባቸው። በዘላቂነት እንዲለሙ ማድረግ ደግሞ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑንም የሚጠራጠር አይኖርም፡፡ ከተሞችን በማደስ ሐብት የማፍራት፣ የኑሮ ጥራትን የማሳደግ፣ ጎብኝዎችን በዘላቂነት የማስተናገድ ሥልጣን ሁሉም ዜጋ የሚጋራው ነው፡፡

የበርካታ አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ምርትና ፍጆታ ማዕከሏ አዲስ አበባ፤ ሐብትና ዕድል ይዘው የመጡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ በረከቶችን በውስጧ ይዛለች። በአንጻሩ በሽታ፣ ወንጀል፣ ብክለትና ድህነትንም በጉያዋ አቅፋ አስቀምጣለች፡፡ ይህን ኢ-ፍትሃዊነት፣ ያልተደላደለ ሕይወት፣ ያልተገራ ዕድገት፣ በውበት ያልታጀበ ኑሮ፣ በእኩልነት ያልባረከ ጉዞ ለማስቀረት የከተማዋ ሁለንተናዊ ዕድገት ለአንድ አካል የማይተው፤ የሁሉንም ዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

መንግሥት የኮሪደር ልማቱን ሲያቅድ፣ ዕቅዱን ወደ ተግባር ለመቀየር ሲነሳ፣ ዲዛይኑን ወረቀት ላይ ሲያሰፍር ይህን ፕሮጀክት ተፈጻሚ እንደሚያደርግ በሙሉ እምነት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተሰሩ መዝናኛዎች፣ ሙዚየም፣ ፓርኮች በራስ ኃይል እና አቅም ማሳካት እንደሚቻል ያስመሰከሩ፤ ይህኛውም እንዲሳካ ቀድመው የተጠረጉ መንገዶች፣ መሻገሪያ ድልድዮች፣ የክህሎት ማበልጸጊያ ትምህርት ቤቶች፣ ለስኬት አቅጣጫ ጠቋሚዎች ሆነው ያገለግሉታል፡፡ ትናንት ያልነበረው የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ለዛሬ እውነት እንደበቃው ሁሉ፣ ትናንት ያልታሰቡት ፓርኮች ለዛሬ ማረፊያዎች እንደሆኑት ሁሉ፤ የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅ ለዓይን የሚማርክ ውስጥን በሀሴት የሚሞላ ውበት ይሆናል፡፡ 

መውጫ

የበርካታ ከተሞች የከተማነት መስፈርት እና ገጽታ የሕዝብ ቦታዎች እና መሠረተ ልማት አስፈላጊነት ከግምት ገብተው ሲሰሩ አይስተዋልም። ይህም የከተማ ፕላን ከግለሰቦች የኑሮ ጥራት፣ ከማኅበራዊ ልማትና ከሌሎች የሰው ልጅ ደህንነት አካላት ጋር ያለውን ዝምድና ሙሉ በሙሉ ካለመረዳት የሚመጣ መሆኑን የከተማ ፕላን ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በተመሳሳይ መልኩ ማራኪ ከተሞች የሥራ ፈጠራ፣ የአዳዲስ ፈጠራዎች መነሻ እና የሠለጠነ የሰው ኃይል ባለቤቶች በመሆናቸው የከተማ ኢኮኖሚ ሊያሳድጉ የሚችሉ ኢንቨስትመንቶችን የመሳብ ዕድላቸው ሰፊ ነው። ይሁን እንጂ የከተሞች ብሎም የአገራት የፋይናንስ አቅም በማነሱ ሳቢያ፤ የከተማ ዲዛይኖች የከተማ ልማት፣ ውበት፣ ጽዳት እና ምቹነትን ሲያሳኩ አይታይም።

ከዓለም አገራት ከ90 በላይ ከሚሆኑት ጋር በአጋርነት የሚሰራው UN-HABITAT እ.አ.አ ከ1998 ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር በርካታ ፕሮጀክቶችን ተፈጻሚ አድርጓል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈትነው ውጤታማ የሆኑ መመሪያዎችን በማዳበር የተሻሻሉ፣ ዘላቂነት ያላቸው፣ ቀልጣፋ እና ፍትሃዊነትን ያነገቡ ከተሞች እንዲፈጠሩ የዲዛይን እና የዕቅድ ንድፎችን በማዘጋጀት አባል አገራቱን ያግዛል፡፡

ትልልቅ ከተሞች ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የተጠጋጋ የማኅበረሰብ አኗኗር ያላቸው በመሆናቸው የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ምህዳራዊ ማዕከልነትን ይዘዋል። በትልልቅ ከተሞች፤ የከተማ ፕላንን ዛሬ ላይ ችላ ማለት ወደፊት ችግሩን ለመፍታት የበለጠ ወጪ የሚጠይቅ ሁኔታን ይፈጥራል። የUN-HABITAT ጥናቶች በአጠቃላይ ከከተማ ዲዛይን ማነቆዎች ዋነኛው በአገር አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ በቂ ማዕቀፎችና ሕጎች አለመኖራቸው መሆኑን ያሳያል።

የኢትዮጵያ ከተሞች በመሰረተ ልማት ኮሪደሮች ዙሪያ እንዲያድጉ የሚያስችሉ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ሐብት ባለቤቶች ናቸው። ከአዲስ አበባ ባሻገር ሌሎች ከተሞችም እንደ አዲስ የዕድገት ሞተር በመሆን ብቅ እያሉ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የከተሞች ዕድገት ቀድሞም ያልታቀደ እና ያልተቀናጀ በመሆኑ ሰፊ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ዕድሎችን እንዲያጡ ሲያደርጋቸው ቆይቷል። አዲስ አበባም በዚህ ሳቢያ ስሟን ሳትመስል ለዘመናት አንቀላፍታለች።

በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ዜጎች ፍላጎቶታቸውን እና መሻቶቻቸውን የሚያሟሉባቸው በየደረጃው በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በሚያስችሉ የገቢ አቅምና ጥሪቶች እንዲሁም እነዚህን ጸጋዎች ለመፍጠር በሚያግዙ ቁሳዊ፣ ሰብዓዊና ተቋማዊ አቅሞች፤ በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች መኖራቸውን ያትታል። ሁሉም ዜጎች የኢኮኖሚ አቅማቸው ፈቀደም አልፈቀደም ለመኖር መሰረታዊ የሆኑትን እንደ ተመጣጣኝ ምግብ፣ መጠለያ፣ ንጹህ የመጠጥ ውኃ፣ መሰረታዊ የጤናና የትምህርት አገልግሎቶች ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ማድረግ በዕቅዱ የሰፈረ ሃቅ ነው። ይህ የሚሆነው በዘላቂነት የሚለማ፣ አካታች፣ ጽዱ እና ጤናማ አካባቢ ሲኖር ነው።

በመዲናዋ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ያለው የኮሪደር ልማት የUN-Habitatን መስፈርቶች ባሟላ መልኩ የተመጣጠነ እና ፍትሃዊ አከታተምን በማረጋገጥ በየደረጃው የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ሚና ያላቸው ከባቢዎች ተመጋጋቢ ሆነው እንዲያድጉ በማድረግ የከተማዋን የዕድገት ዕድል ማስፋት እና የሕዝቦችን የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ማረጋገጥ በሚያስችል ሁኔታ በተቀናጀ መንገድ በመከናወን ላይ ይገኛል።

አዲስ አበባን መልሶ በመገንባት ሂደት ከዚህ ቀደም መንግሥት ስሟን የሚመጥን፣ 'እንደ ስሟ አዲስ እናደርጋታለን፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እንሰራለን' በማለት የገባውን ቃል የመፈጸም ሂደት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ይህንን መፈጸም መቻል የተፈለገውን የብልጽግና እና የዕድገት ጉዞ ለማሳካት የሚያስችል አቅም መኖሩን የሚያሳይ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

አዲስ አበባ ፒያሳ ያስፈልጋታል፡፡ ከተማዋ እሷን የሚመጥን መሀል ፒያሳ ያስፈልጋታል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ከሚያልፍባቸው አካባቢዎች አንዷ የሆነችው ፒያሳ ውብ መሆን ይኖርባታል፡፡ የኮሪደር ልማት ሥራው ሲጀመር ትችቶች ተሰንዝረዋል፡፡ ሥራውን የሚያጣጥሉ ሃሳቦች ተነስተዋል። ፒያሳን ደብዛውን የማጥፋት ሥራ ነው ተብለው ተኮንነዋል። በሥራ ሳይሆን በወሬ የተጠመዱ፣ በተግባር ሳይሆን በአሉባልታ የነጎዱ፣ መፍረሱን እንጂ መገንባቱን፣ መውደቁን እንጂ መነሳቱን ለመናገር አይደፍሩም፡፡ ፒያሳ አዲስ አበባን መስላ የተሰራች መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰዎች ሊያይዋት የሚናፍቁ፣ ሊጎበኟት የሚጓጉላት ፒያሳ እየተገነባች ነው፤ የልማት ኮሪደር ሥራው ቀድሞ የተጠና እና ብዙ ውይይቶች ያለፉበት ሃሳብ የነበረ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ፒያሳን ለአብነት አነሳን እንጂ የመዲናዋ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ቀደም ሲል የለሙ አካባቢዎችን ካልለሙት ጋር በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር እንደ ስሟ ውብ እና ፅዱ ከተማ ለማድረግ ታስቦ የተተገበረ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህም ማማር በአንድነት፣ ውበት በኅብረት፣ ምቹነትን እና ቅልጥፍናን በማንገብ የUN-Habitatን ጽንሰ-ሃሳብ አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡

የኮሪደር ልማት ሥራው መነሻ እና መድረሻ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር የተዋሃደ ነው። ከሕዝብ ጋር የተቆራኘ መሰረት አለው። የአዲስ አበባ መልክ ሲያምር፣ በነዋሪዎቿ ፊት ላይ የሚነበብ እርጋታን ይፈጥራል። የመዲናዋ ምቹነት የማኅበረሰቡን ድሎት የሚወስን ነው። የከተማዋ ጽዳት እና ውበት የነዋሪው አካላዊ እና አዕምሯዊ ጤና እንዲጠበቅ የሚያስችል ነው። የአዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻነት የማኅበረሰቡን የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚያሻሽል ቅመም ይሆናል። አዲስ አበባ ስትደምቅ፤ ነዋሪዎቿም አብረው ይደምቃሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም