ቀጥታ፡

ባህልና ቋንቋዎች አብሮነትን እንዲያጠናክሩና ለሀገር ግንባታ እንዲውሉ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል - የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

አዳማ ፤ ነሐሴ 2/2016 (ኢዜአ)፡-  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ቋንቋዎች አብሮነትን እንዲያጠናክሩና ለሀገር ግንባታ እንዲውሉ የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

''አብሮነታችን ለሀገር ግንባታ'' በሚል መሪ ሃሳብ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማና የ2017 የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የፌዴራልና የክልሎች የባህልና ስፖርት ዘርፍ ጉባኤ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለፁት፤ ባህልና ቋንቋን ለሀገር ግንባታ ለማዋል የሚያስችል የ10 ዓመት ስትራቴጂ ተቀርጾ እየተተገበረ ይገኛል።

በስትራቴጂው መሰረት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ቋንቋዎች አብሮነትን እንዲያጠናክሩና ለሀገር ግንባታ እንዲውሉ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ የባህል፣ የኪነ-ጥበብና እደ-ጥበብ ስራዎች ህብረብሔራዊ አንድነትን ማጽናት እንዲችሉ የተለያዩ ተግባራት መከናወኑንም ነው የተናገሩት።

መድረኩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ አበረታች ተግባራትን ለማስቀጠልና የታዩ ጉድለቶችን ለማስተካከል እንደሚያግዝም አስረድተዋል።

በስፖርት ዘርፉም በግንባታ ላይ የሚገኙ ስታዲየሞችና የስፖርት አካዳሚዎች ፈጥነው እንዲጠናቀቁ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው በተያዘው በጀት ዓመትም ግንባታዎቹ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ አቶ እንድሪስ አብዱ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሪፖርትን ባቀረቡበት ወቅት፣ የብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ቋንቋዎች ለአብሮነትና ለሀገር ግንባታ አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

የስፖርት አካዳሚዎች ግንባታዎች እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው የጤና ስፖርት እንዲጎለብት በትምህርት ቤቶች፣ በመንግሥታዊ ተቋማትና ህዝባዊ ቦታዎች የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለፊልም፣ ለኪነ-ጥበብና ለእደ-ጥበብ የማበረታቻ አሰራር ያለመኖር፣ የእደ ጥበብ ስራዎችን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የበቃ የሰው ኃይል ያለመኖር፣ የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች የበጀት ዓመቱ ማነቆዎች ነበሩ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም