የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት ተመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት ተመረቁ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ በስነ ልቦና ግንባታ፣ በሀገር ፍቅር ስሜትና በአካል ብቃት ሥልጠና የወሰዱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት ተመረቁ።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ 2ኛ ዙር የዕጩ መኮንን ሰልጣኞች የትከሻ ምልክት የማልበስ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በሥነ-ሥርዓቱ የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ኦፕሬሽን ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ለገሠ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያደቻን ጨምሮ የሁለቱ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ተመራቂ የአየር መንገድ የተቋም ደኅንነት አባላቱ በንድፈ-ሃሳብና በተግባር መሠረታዊ ውትድርና እና የአካል ብቃት ሥልጠና የወሰዱ መሆናቸውም ተገልጿል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ ለማ ያደቻ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከምስረታው ጀምሮ ብቁና ውጤታማ ተቋም እንዲሆን የቀድሞ የኢትዮጵያ ኃይል አመራሮች የነበራቸውን አይተኬ ሚና አስታውሰዋል።
አሁንም ቢሆን እገዛና ትብብሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው፤ ሁለቱ ተቋማት የቆየ ታሪካዊ ትስስር ያላቸውና የሀገር ኩራትም ናቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ሰልጥነው በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት በንድፈ-ሃሳብና በተግባር ሥልጠና የወሰዱ ናቸው ብለዋል።
ከዚህ በፊት በአየር ኃይል አካዳሚ 248 አብራሪ ካዴቶች፣ 303 የአውሮፕላን ጥገና ሠራተኞች መሰልጠናቸውን አስታውሰው፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ የደኅንነት ጥበቃ አባላት ተመርቀዋል ብለዋል።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አካዳሚ ላደረገው የላቀ አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ኦፕሬሽን ብርጋዴር ጄኔራል ተስፋዬ ለገሠ፤ በፈጣን ሪፎርም ላይ የሚገኘው አየር ኃይል ከራሱ አልፎ ለሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማትም ተከታታይ ሥልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁት የትከሻ ምልክት ያደረጉ ዕጩ መኮንን ሰልጣኞችም ሆነ ተመራቂ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋም ደኅንነት ጥበቃ አባላት በቀጣይ ለላቀ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዲዘጋጁ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአየር መንገድ ጋር ያለውን አብሮነትና ትብብር አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።