ቀጥታ፡

በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት ድጋፍ ተደረገ   

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 2/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በድርቅና በግጭት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት የህክምና ቁሳቁስና የመድሃኒት ድጋፍ አደረገ።

የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፉ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተጎዱ 32 ጤና ተቋማት የሚከፋፈል ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ተጠባባቂ ዋና ፀሐፊ አበራ ዱሜሳ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ፣ ማህበሩ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውሰዋል።


 

ማህበሩ ባለፈው ዓመት ከብሪታንያ መንግስት ባገኘው የ14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ እገዛ በአራት ክልሎች አደጋን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ማህበረሰብ ለመገንባት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ማድረጉን ተናግረዋል።

በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ትግራይና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች መተግበር በጀመረው ፕሮጀክት በግጭትና በድርቅ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት የመደገፍ ስራ በትኩረት ተሰርቷል ብለዋል።

በፕሮጀክቱ በጤና ተቋማቱ ተቋርጦ የነበረውን የውሃ አገልግሎት መልሶ ማስጀመር፣ የጤና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ፣ የህክምና ቁሳቁሶችና የመድሃኒት ድጋፍ በዋነኝነት እየተተገበሩ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።

የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁሱ ከ58 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበትና በግዥ ሂደቱ  የብሪታኒያ ቀይ መስቀል ማህበር ድጋፍ ማድረጉንም ገልፀዋል።

ድጋፉን የአማራ፣ ትግራይ ፣ ኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች ተረክበዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ላለፋት 80 ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰቱ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም