የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሐረሪ ክልል ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ያካሂዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሐረሪ ክልል ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ያካሂዳል
ሐረር ፤ነሐሴ 02/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሐረሪ ክልል ከነሐሴ 04 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ እንደሚያካሂድ አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ዲሪር ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ከአሁን በፊት በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮችን አስመርጦ አዘጋጅቷል።
በዚህም መሠረት ከነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ተከታተይ ቀናት በክልሉ የአጀንዳ ማሰባሰብ የውይይት መድረክ እንደሚያካሄድ ገልጸዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰቡ መድረክ ላይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ ተሳታፊዎችን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የመንግስት አካላት፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ባዘጋጀው በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ላይ ከአንድ ሺህ በላይ ተወካዮች እንደሚሳተፉም አመልክተዋል።
መድረኩ የክልሉ ባለድርሻ አካላት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋል የሚሏቸውን መሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች በህዝባዊ ውይይት የሚሰበስቡበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው ሲሉም ገልፀዋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ተገኝወርቅ ጌቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የክልሉ ነዋሪዎች በመጪዎቹ ቀናት የሚደረገው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ለአገር ያለውን ፋይዳ በመረዳት ዝግጅት እንድታደርጉና በንቃት እንድትሳተፉ በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል።