ቀጥታ፡

በ3000 ሜትር መሰናክል የኢትዮጵያ አትሌቶች ሜዳሊያ ውስጥ መግባት አልቻሉም

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2016(ኢዜአ)፦ በፓሪስ ኦሊምፒክ በወንዶች የ3000 ሜትር መሰናክል የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል አልቀናቸውም፡፡

በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ የተሳተፈው አትሌት ሳሙኤል ፍሬው 8 ደቂቃ ከ08 ሴኮንድ ከ87 ማይክሮ ሴኮንድ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

አትሌት ጌትነት ዋለ 8 ደቂቃ ከ12 ሴኮንድ ከ33 ማይክሮ ሴኮንድ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።

በውድድሩ ተጠብቆ የነበረው ለሜቻ ግርማ በመጨረሻው ዙር ላይ ከመሰናክል ጋር ተጋጭቶ በመውደቁ ምክንያት ውድድሩን ሳይጨርስ ቀርቷል። ለሜቻ ከወደቀ በኋላ ያጋጠመውን ጉዳት ተከትሎ በሕክምና ባለሙያዎች ክትትል እየተደረገለት ይገኛል።

ለሜቻ በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርቀቱ የብር ሜዳሊያ አግኝቶ ነበር።

በተጨማሪም ለሜቻ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ነው።

ሞሮኮዋዊው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ 8 ደቂቃ ከ06 ሴኮንድ ከ05 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። በርቀቱ የራሱን የዓመቱን ፈጣን ሰዓት አስመዝግቧል።

ኤል ባካሊ በ32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ የሚታወስ ነው።

አሜሪካዊው ኬኔት ሮክስ 8 ደቂቃ ከ06 ሴኮንድ ከ41 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥቷል።

ኬንያዊው አትሌት አብርሃም ኪቢዮት 8 ደቂቃ ከ06 ሴኮንድ ከ47 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። ኪቢዮት በርቀቱ የራሱን የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።

ኢትዮጵያ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስካሁን ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት 57ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

አሜሪካ፣ቻይና፣አውስትራሊያ፣ፈረንሳይና ታላቋ ብሪታንያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም