የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጡ ለ50 ዓመታት የዘለቀውን የኢኮኖሚ መዛባትን የሚያስተካክል ነው- ዶክተር እዮብ ተካልኝ - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጡ ለ50 ዓመታት የዘለቀውን የኢኮኖሚ መዛባትን የሚያስተካክል ነው- ዶክተር እዮብ ተካልኝ
አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 1/2016(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው ለ50 ዓመታት የዘለቀውን የኢኮኖሚ መዛባት የሚያስተካክል ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካለኝ (ዶ/ር) ከብሉምበርግ ድረ ገጽ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ያደረገችው ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ በተቀመጠው የማህበራዊ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ሪፎርምን ታሳቢ በማድረግ ነው።
ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለግሉ ዘርፍ ክፍት ከመሆናቸውም ባሻገር የፋይናንስ ዘርፉን ከዲጂታል ሥርዓቱ ጋር በማስተዋወቅ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስቻሉ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
ገንዘብን በሚመለከትም የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲመጣ በሂደትም የምጣኔ ሃብት አወቃቀሩ እንዲቀየር ተከታታይ ስራዎች ተግባራዊ ሲደረጉ መቆየታቸውንና ላለፉት 50 ዓመታት በኢኮኖሚው ዘርፍ ይስተዋል የነበረው መዛባት እንዲስተካከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
እዮብ (ዶ/ር) አያይዘውም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ መርካቶ በሚባለው የሃገሪቱ ትልቁ የገበያ ስፍራ ዶላር በባንኮች እና በትይዩ መንገድ በብር ሲመነዘር የነበረው ሰፊ ልዩነት ይዞ መቆየቱን ጠቅሰው፤ የተወሰደው እርምጃም ሁለቱን ገበያዎች ለማቀራረብ እንደሆነም ገልጸዋል።
ላለፉት ሶስት ወራት የውጭ ምንዛሬ ለውጥ ሊኖር ይችላል በሚል ግምት እዛም እዚህም ዶላር የማሸሽ እና ያልተገቡ የንግድ ተግባራት የመፈጸም አዝማሚያዎች በሰፋት እንደነበሩ በአንስተዋል።
ከእርምጃው በኋላ ግን ሁለቱ የውጭ ምንዛሬ ገበያዎች አቻ ሲሆኑ የምርቶች ዋጋ ሊረጋጋና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም ወደ መደበኛው መንገድ ሊገባ እንደሚችል ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።
ለውጡን ተከትሎ ትርጉም ያለው ገንዘብም በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት እንደሚላክ ይጠበቃል ያሉት እዮብ (ዶ/ር) ይህ ገንዘብ ወደ ገበያው ሲገባ ገበያው ይረጋጋል ብለዋል።
በገንዘብ የማሻሻያ ለውጥ ሲደረግ በተወሰነ ደረጃ ጉዳዩን ያለመረዳት ችግር ሊያግጥም እንደሚችል የሚጠበቅ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለውጡ የብዙሃኑን ማህበረሰብ አኗኗር እንዳይጎዳና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የዋጋ ግሽበት እንዳያስከትል ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት መንግሥት ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ለመንግሥት ሰራተኞች የተዘጋጀውን የደመወዝ ጭማሪ እና በቅርቡ ከተመደበው ተጨማሪ ከ550 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ውስጥ እንደ ነዳጅና ማዳበሪያ ለመሳሰሉ አስፈላጊ አቅርቦቶች ድጎማ መዘጋጀቱን በማሳያነት አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ያለባትን ብድር ለመክፈል የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎች ሲሰሩና ከሁሉም አበዳሪዎች ጋር የብድር አከፋፈል ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ድርድሮች ሲካሄዱ መቆየታቸውን እዮብ (ዶ/ር) አሰታውሰው፤ ድርድሮቹ በመሳካታቸው ኢትዮጵያ ለጀመረችው ሀገራዊ ለውጥ ስኬት የሚያግዛት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የእዳ ክፍያ እፎይታ ማግኘት ችላለች ብለዋል።
የአገር ውስጥ ብድርን በተመለከትም ለአገሪቱ የጡረታ ፈንዶች ከፍ ያሉ የቦንድ ጥያቄዎችን በማቅረብ የአገር ውስጥ የብድር ጫናን ለመቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ባላት ጥቅል አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) በስፋቷና በህዝብ ብዛቷ በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካ ባስመዘገበችው ትልቅ የኢኮኖሚ ዕድገት በአገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎቱ ላላቸው የውጭ ባለሃብቶች ተመራጭ መዳረሻ እንደሚያደርጋት አስረድተዋል።
ይህ የለውጥ መንግሥት ባለፉት አምስት እና ስድስት ዓመታት ተከታታይ እርምጃዎችን በመውሰድ ኢኮኖሚው ላለፉት 50 ዓመታት ከታሰረበት ተፈቶ ተወዳዳሪና ከጊዜው ጋር እንዲሄድ አድርጎታል ብለዋል።
ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) አክለውም ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው የለውጥ መንግሥት የዓለም ባንክና አይኤም ኤፍ እና አሜሪካንን ጨምሮ ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሳይ ከጣሊያንና ከሌሎች አገራት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ የኢንደስትሪያል ፓርኮች ምርቶች መዳረሻቸው አሜሪካ በመሆኑ ኢትዮጵያ ጉዳችን መልሳ እየገመገመች ስለሆነ ወደ አጎዋ ማእቀፍ የማትመለስበት ምክንያት እንደማይታያቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አጎዋ ማእቀፍ ተመልሳ መግባቷ በኢንደስትሪ ፓርኮቹ ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ ባለሃብቶችን እና አብዛኞቹ ሴቶች የሆኑበት በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የፓርኮቹን ሠራተኞችን ተስፋ የሚያለመልም መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የብልፅግና መልህቅ ስለሆነች ለውጡ አገሪቱን ዋነኛ የቱሪዝም እና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚደርጋት ያስረዱት እዮብ (ዶ/ር) ፤ ኢትዮጵያ በትውልዶች መካከል መዋቅራዊ ሽግግር እንዴት እንደሚሳካ የማሳየት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም በአጽንኦት መናገራቸውን በመረጃው ተጠቅሷል።
ሚኒስትር ዴኤታው ይሄ ጉዳይ ዜጎችን በተለያየ ደረጃ ለጊዜው ቢገዳደርም ኢትዮጵያውያን ዘመናትን ያስቆጠረ የአገር ግንባታ ታሪክ ያላቸው በመሆኑ፤ አሁን እየተደረገ ያለው የብሄራዊ ምክክር ሂደትም ለዚህ መስፈንጠሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል ሲሉም አስረድተዋል።