የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ወር እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን ካሳሁን(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ፈቃድ መስጠት የሚያስችል መመሪያ በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ወደ ትግበራ እንዲገባ ከሳምንታት በፊት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
በመሆኑም የአገር በቀል ምጣኔ ኃብት ማሻሻያ አካል የሆነው ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያን ለመጀመር ያለውን ዝግጅት ማጠናቀቁ ታውቋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን ካሳሁን(ዶ/ር)፤ ከካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ ለማግኘት የገንዘብ ማሰባሰብና ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ባለሥልጣኑ ባወጣው መመሪያ መሠረት 500 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ገልፀዋል።
በካፒታል ገበያ መሳተፍ የሚፈልጉ የግል ገንዘብ ተቋማትና ከገንዘብ ተቋማት ውጭ የሆኑ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ለሥራው የሚያስፈልግ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ግብዓቶችም መሟላታቸውን ጠቅሰው፤ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያው በጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም የሚጀምር መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ (ስቶክ) ገበያ እውን ለማድረግ የካፒታል ገበያን በማቋቋም፣አዋጅ በማውጣትና ሌሎች ሁኔታዎችን በማሟላት መንግሥት አስቻይ ሥነ-ምኅዳር መፍጠሩን አድንቀዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የምጣኔ ኃብትና የፋይናንስ ፍላጎት ጥሩ አማራጭ ይሆናል ብለዋል።
የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን፣ ግብርናን ለማስፋፋትና የምጣኔ ኃብት እድገትን ለማፋጠንም የላቀ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሰነደ መዋለ ንዋይ ገበያ (Ethiopian Securities Exchange - ESX) በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 መሠረት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ትብብር በአክሲዮን ኩባንያነት እና በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንደሚቋቋም ተደንግጓል።
የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ሽያጭ፣ ግዥ እና ልውውጥ በቋሚነት የሚደረግበት ሲሆን ለመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የገንዘብ ምንጭ በመሆን ለምጣኔ ኃብት እድገት ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳለው ይነገራል።