ወጣቶች ለሰላምና አብሮነት የሚተጉና በሥነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ የበኩላችንን ሚና እየተወጣን ነው- የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ለሰላምና አብሮነት የሚተጉና በሥነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ የበኩላችንን ሚና እየተወጣን ነው- የኃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 1/2016 (ኢዜአ)፦ወጣቶች ለሰላምና አብሮነት የሚተጉና በሥነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ የበኩላችንን ሚና ለመወጣት እየሰሩ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የኃይማኖት አባቶች ገለጹ።
ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ዜጎች የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲወጡ ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት፡፡
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኃይማኖት አባቶች፤ በተያዘው የክረምት ወቅት ወጣቶችና ህፃናትን ከአልባሌ ቦታ ርቀው በሥ-ምግባር እንዲታነጹ እያስተማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የኃይማኖት አባት መላዕከ ብርሃን ሙላት ክበቤ፤ የዕምነት ተቋማት መልካም ሥነ-ምግባር የተላበሱ ዜጎች መፍለቂያ ናቸው ብለዋል።
በዚህም ቤተክርስትያኗ ባላት መዋቅር ሁሉ ወጣቶችና ህፃናትን በሰላም፣ አብሮነትና በግብረ-ገብነት አስተምህሮ በመስጠት በስነምግባር የታነጹ ዜጎች እንዲሆኑ እየሰራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በተያዘው የክረምት ወቅትም ወጣቶችንና ህፃናትን በሰንበት ትምህርት ቤትና በሰርክ ጉባኤ ከሃይማኖት ትምህርት ባሻገር ስለ አብሮነት የሀገር ፍቅር ስሜትን የሚያጎለብት ትምህርት እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የእስልምና ሃይማኖት መምህር ሀጂ አህመድ ሀሩን፤ በክረምቱ ወቅት ወጣቶች ወላጅና ታላላቆቻቸውን በማክበር ሀገር ወዳድና መልካም ሥነ-ምግባርን የተላበሱ ዜጎች እንዲሆኑ የማስተማር ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አባት አባ ኃይለገብርኤል መለቁ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው ወጣቶች ከኢትዮጵያ ህዝብ ከፍተኛውን ደርሻ የሚይዙ በመሆናቸው የሀገር መሰረት ናቸው ብለዋል።
ከዚህ አኳያ በክረምት ወራት ለወጣቶችና ህፃናት የመልካም ስብዕና ግንባታ ኃይማኖታዊ ትምህርት በመስጠት በበጎ ፈቃድ ስራ ላይ በንቃት የሚሳተፍ በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ እንዲኖር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ሀገራዊ የምክክሩ ኢትዮጵያዊያን ችግሮቻቸውን በሰለጠነ የውይይት መድረክ መፍትሔ በመስጠት ለሀገር ሰላምና ደህንነት በጋራ እንዲሰሩ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ስኬታማነት ዜጎች የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲጫዎቱ ለማድረግ የሃይማኖት አባቶች የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም አረጋግጠዋል፡፡