ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት በቀጣዩ ዓመት ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት በቀጣዩ ዓመት ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የዜጎች የኑሮ ሁኔታን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ መስጠት የሚያስችል ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት በ2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ለብሄራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት 600 ለሚጠጉ መረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች ለአንድ ወር የሚሰጠውን ስልጠና ዛሬ አስጀምሯል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር)፤ ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት የሀገር ምጣኔ ሀብትና የዜጎች የኑሮ ሁኔታ ያለበትን ደረጃ የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
የቤተሰብ ፍጆታ፣ የሰው ሃይል ስምሪት፣ የህዝብ ፍልሰትና የማህበራዊ ደህንነት አሰጣጥን በተመለከተ ትክክለኛ መረጃ መስጠት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ጥናቱ በ2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ስልጠናው መረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች በእውቀት ላይ ተመስርተው መረጃ እንዲሰበስቡ ያግዛል ብለዋል፡፡
ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚካሄድ ጠቅሰው፤ በጥናቱ የሚሳተፉ ባለሙያዎች በአጠረ ጊዜና ወጭ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት ለሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች ግብዓት ጥራት ያለው መረጃ የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ጥናቱን ለዜጎች የኑሮ ሁኔታ መሻሻልና ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ገንቢ አብርክቶ እንዲኖረው ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን በጠበቀና በተቀናጀ መንገድ ይከናወናል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የኢኮኖሚ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን ቀሬ፤ ጥናቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
የጥናቱ ውጤት ለአምስት ዓመት እንዲያገለግል ታስቦ እንደሚካሄድ ገልጸው፤ ውሳኔ ሰጪዎች እውቀትና መረጃን መሰረት አድርገው ውሳኔ እንዲያሳልፉ እድል ይሰጣል ብለዋል፡፡
አገልግሎቱ ውጤታማ ብሔራዊ የተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት ማካሄድ እንዲችል ዜጎች በመረጃ አሰባሰብ ወቅት ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡