ቀጥታ፡

በደሴ ከተማ  ምርት በደበቁና ዋጋ በጨመሩ  ህገወጦች ላይ  እርምጃ እየተወሰደ ነው

ደሴ፤ ነሐሴ 1/2016(ኢዜአ)፦በደሴ ከተማ አስተዳደር  ያለአግባብ ምርት በደበቁና ዋጋ በጨመሩ  ህገ ወጦች ላይ  እርምጃ መወሰዱን የከተማው አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ተወካይ ወይዘሮ እየሩሳሌም መድፉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤የማክሮ ኢኮኖሚውን ማሻሻያው ተከትሎ በከተማው በምርት ላይ ዋጋ የመጨመርና የመደበቅ አዝማሚያ ተስተውሏል።

ይህን ለማስተካከል ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ጠቅሰው፤ ግብረ ሃይሉ ነጋዴውን በማወያየት ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ህገ ወጥነትን በመቆጣጠር ገበያውን የማረጋጋት ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በተደረገው ክትትል ያለ አግባብ ምርት የደበቁ፣ ያከማቹና ዋጋ የጨመሩ 124 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል።

የተወሰደው እርምጃም  ድርጅቶችን ከማሸግ ባለፈ ያካማቹትን ምርት በመደበኛ ዋጋው ለህዝብ እንዲቀርቡ መደረጉን  ጠቅሰዋል።

ተከማችቶ ከነበረው ምርት ውስጥ  የምግብ ዘይት፣ ፓስታና ማካሮኒ እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ ምርቶቹ በየክፍለ ከተሞች ጊዜያዊ ገበያ ማዕከል ተቋቁሞ ጭምር ቀድሞ በነበረው መደበኛ ዋጋ መሸጣቸውን ገልጸዋል።

''አሁንም ገና ያልተከፈቱ መጋዝኖችና በህገ ወጥ የተያዙ ምርቶች በመኖራቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማከፋፈል እየተሰራ ነው'' ብለዋል።

ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠትና በማጋለጥ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አመልክተው፤ ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ገበያው እየተረጋጋ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም 5 ሊትር የታሸገ የምግብ ዘይት አንድ ሺህ 500 ብር ደርሶ እንደነበረና መልሶ ወደ ዘጠኝ መቶ 80 ብር ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል።


 

የአራዳ ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ስነወርቅ ዳኜ በበኩላቸው፤ ክፍለ ከተማው ዋና የንግድ ማዕከል በመሆኑ የተጠናከረ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የ78 ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ድርጅት በማሸግ ያካማቹት የተለያዩ ምርቶች ጊዜያዊ ገበያ ተቋቁሞ በመደበኛው ዋጋ እንዲሸጥ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

አሁንም ለንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ክትትልና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

በከተማው በምርት ላይ ከፍተኛ ዋጋ ተጨምሮ ነበር ያሉት ደግሞ በከተማው የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አሚናት ዳውድ ናቸው።

አስተዳደሩ  ባደረገው ብርቱ ክትትልና ቁጥጥር ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ በመሆኑ  የገበያው መረጋጋት እያሳየ መሆኑን  ተናግረዋል።

በዚህም አንድ ሺህ 500 ብር መሸጥ ተጀምሮ የነበረውን 5 ሊትር ዘይት በተመቻቸው ጊዜያዊ ገበያ በ980 ብር መግዛታቸውን ጠቅሰዋል።

የአገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በዘላቂነት ለማሳደግ መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲን ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ይታወሳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም