ቀጥታ፡

አዲስ አበባ የጎብኝዎችን ቀልብ የምትገዛ ማራኪና ውብ ከተማ እየሆነች ነው - የውጭ አገራት ጎብኝዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2016(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ የጎብኝዎችን ቀልብ የምትገዛ ማራኪና ውብ ከተማ እየሆነች ነው ሲሉ የተለያዩ  የውጭ አገራት ጎብኝዎች ተናገሩ።

በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግስት በ1879 ዓ.ም የተቆረቆረችው አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የአፍሪካ መዲና የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት፡፡

ከተማዋ ከ100 ዓመት በላይ በዘለቀው ታሪኳ የዘመናዊ ከተሜነት መልክ እንዲኖራት በዕቅድ ባለመሰራቱ በተለይም ቀደምት የከተማዋ ሰፈሮች ለዕይታ የማይስቡና ጎስቋላ ሆነው ይታያሉ።

የቤቶች ጥግግት፣ የጎዳናዎች ጥበት፣ የኤሌክትሪክና ቴሌኮም መሰረተ ልማት ዘፈቀዳዊ ዝርጋታና የፍሳሽ አወጋገድ ለከተማዋ ውስብስብ ችግሮችን ፈጥረዋል።

በመሆኑም በመዲናዋ በዕቅድ በተገነቡ ቤቶች፣ ሰፋፊና ሳቢ መንገዶች፣ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት የምትከትል ከተማ ለማድረግ የኮሪደር ልማት መርሀ ግብር ገቢራዊ እየተደረገ ነው።

በአዲስ አበባ በተለይም የኮሪደር ልማት በተከናወነባቸው አካባቢዎች መሰረተ ልማት እየተሟላላቸው የዘመናዊ ከተማ መገለጫና ሳቢ እይታ እንዲኖራቸው ማድረግ ተችሏል።


 

በዚህም የአዲስ አበባ መልካም ውበት እየጎላ ገጽታዋም እየተለወጠ መሆኑን ከነዋሪዎቿም በተጨማሪ በቀድሞ ገጽታዋ የሚያውቋት የውጭ ሀገር ዜጎች ይናገራሉ።

የሰው ዘር አመጣጥ ከፍተኛ ተመራማሪው ስፔይናዊው ኢግናሲዮ ላሳጋባስተር (ዶ/ር)፤ አዲስ አበባን የሚያውቋት 10 ዓመታት በፊት እንደነበር ያስታውሳሉ።

በወቅቱ ብዙም መሰረተ ልማት የሌላት የገጠር ገፅታ ነበራት የሚሉት ተመራማሪው አሁን ላይ አምራና ተውባ ቀልብ የምትገዛ ከተማ ሆና አገኘኋት ይላሉ።

በተለይም የኮሪደር ልማት የተከናወነባቸው የከተማዋ አካባቢዎች በመሰረተ ልማት፣ ለእንቅስቃሴ በመመቸትና በዘመናዊነት አስደናቂ ስራዎችን ተመልክቻለሁ ብለዋል።


 

ታንዛኒያዊቷ የሰው ዘር አመጣጥ አጥኝ ሜሪየም ቡንዳላ (ዶ/ር)፤ አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙት ከሰባት ዓመታት በፊት እንደነበር አስታውሰዋል።


 

በመሆኑም የአዲስ አበባ የድሮ እና ዘንድሮ ገፅታ የተለየና አሁን ላይ ብዙ አስደናቂ ለውጦችን የተመለከትኩበት ነው ብለዋል።

በታንዛኒያም መሰል የከተማ ልማት ስራዎችን ለማከናወን አዲስ አበባ ጥሩ ማሳያ ልትሆን ትችላለችም ነው ያሉት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም